Monday, March 20, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለጅማ አባ ቡና የፍትሕ ጥያቄ የፌዴሬሽኑ አልሸሹም ዞር አሉ ምላሽ

ለጅማ አባ ቡና የፍትሕ ጥያቄ የፌዴሬሽኑ አልሸሹም ዞር አሉ ምላሽ

ቀን:

‹‹የፍትሕ አካሉን ውሳኔ እንጠብቃለን››

የኦሮሚያ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2009 ዓ.ም. የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍፃሜውን ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ በውድድር ዓመቱ ከተከናወኑ 30 የሊግ ግጥሚያዎች መካከል በተለይም ከመጨረሻዎቹ አንዳንዶቹ ጨዋታዎች ፌዴሬሽኑ ባስቀመጠው የውድድር ደንብ መሠረት መከናወናቸው ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አልቀረም፡፡ ለምሳሌ ያህልም በ2008 ዓ.ም. ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው የጅማ አባ ቡና እግር ኳስ ክለብ የ2009 የውድድር ዓመት ከ27ኛው የፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ጀምሮ የሚከናወኑ ጨዋታዎች በአወዳዳሪው አካል ልዩ ጥንቃቄ እንዲያደርግባቸው ተደጋጋሚ አቤቱታዎችን ለፌዴሬሽኑ ማስገባቱ ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህንኑ አስመልክቶ በደብዳቤ ቁጥር አ.ቡ.ስ/-372/2009 ሰኔ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጻፈው ደብዳቤ፤ ፌዴሬሽኑ ለቁጥጥርና ክትትል ያወጣውን መመርያ እንዲያከብርና እንዲያስፈፅም ጠይቋል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በኢትዮ ኤሌክትሪክ ቡድኖች መካከል የተደረገው ጨዋታና በአጠቃላይ እንቅስቃሴው ላይ ያለውን ሥጋት ጠቅሷል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ 30ኛ የጨዋታ መርሐ ግብር ሐዋሳ ላይ በሐዋሳ ከተማና በኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጨዋቾች መካከል ስለ ጨዋታው በስልክ ያደረጉት የመልዕክት ልውውጥ እንዳለ በመጥቀስ፤ የደረሰውን መረጃ ለፌዴሬሽኑና ለፖሊስ መስጠቱንና ጉዳዩ በፌዴሬሽኑ በኩል አስፈላጊው የዲሲፕሊን ዕርምጃ እንዲወሰድ ስለመጠየቁ ጭምር አስታውቋል፡፡

ይሁንና ተደጋጋሚ የፍትሕ ጥያቄ ያቀረበው የጅማ አባ ቡና እግር ኳስ ክለብ እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘቱን ይገልጻል፡፡ ክለቡ ይህንኑ ጉዳይ ለክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታውቆ፤ ክልሉም ተቋሙ ለሚመራበት ደንብና መመሪያ ተገዢ እንዲሆን ጠይቋል፡፡ እንዲያውም ፌዴሬሽኑ ጅማ አባ ቡና ላቀረበው የፍትሕ ጥያቄ መልስ መስጠት የማይችል ከሆነ ክልሉ በስሩ የሚገኙ ክለቦች ፌዴሬሽኑ በሚያወዳድራቸው ማናቸውም መርሐ ግብሮች እንደማይሳተፉ ለክለቦቹ ጭምር ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን ለክለቡም ሆነ ለክልሉ ጥያቄ መልስ ከመስጠት ይልቅ፤ በ2010 ዓ.ም. ለሚደረገው ፕሪሚየር ሊግ የተሳታፊ ክለቦች ማንነትና በውድድር ዓመቱ ለሚደርጉ ውድድሮች ዕጣ አውጥቷል፡፡ የፍትሕ ጥያቄ አቅራቢው ጅማ አባ ቡና ወደ ከፍተኛው ሊግ እንደወረደ ተቆጥሮ የክለቡ ተወካዮች ባልተሳተፉበት ዕጣ በከፍተኛው ሊግ ምድብ ድልድል እንዲካተት አድርጓል፡፡

 ጉዳዩን አስመልክቶ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ‹‹ፌዴሬሽኑ ያዘገየው ውሳኔ የለም›› በማለት ከሰሞኑ የጅማ አባ ቡናን ክለብ ጥያቄ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡ እንደ መግለጫው፤ ጅማ አባ ቡናም ሆነ ሌሎች ክለቦች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተመዝግበው የሚገኙ ክለቦች በሚወዳደሩበት ሊግ ለ2010 ዓ.ም. ውድድር ዝግጅት እንዲጀምሩ፤ በዚሁ መሠረትም ከነሐሴ 1 ቀን 2009 እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ዝግጅት እንዲያደርጉና እንዲመዘገቡ ነሐሴ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በደብዳቤ ቁጥር 2/አ.እ.ፌ አ.9/143 በተፃፈ ደብዳቤ ተገልፆላቸዋል፡፡

ጅማ አባ ቡና፣ ‹‹በኤሌክትሪክና በሐዋሳ ከተማ መካከል የተደረገው የመጨረሻ ጨዋታ ውጤት የማስለወጥ ተግባር ታይቶበታል›› በማለትና ከዚሁ ጋር በማያያዝ ሐዋሳ ከተማ ከኤሌክትሪክ ክለብ ጋር ያደረገው ጨዋታ ሕገወጥ መሆኑን መግለፁን ያትታል፡፡ የክለቡ አመራሮች ለድርጊቱ ተጠያቂ ያሏቸውን ግለሰቦች ስምና ማንነት ማሳወቃቸውን ጭምር ይናገራሉ፡፡

የተመዘገበውን ውጤት መለወጥ ስለሌለበት ለሁሉም ክለቦችና ለሚመለከታቸው አካላት የክለቦችን ደረጃ በሰንጠረዥ ተሠርቶ የጅማ አባ ቡና ክለብ በ14ኛ ደረጃ ውድድሩን ማጠናቀቁን ማሳወቁ ይገልፃል፡፡

ይሁንና ጅማ አባ ቡና ለፌዴሬሽኑ ተደጋጋሚ አቤቱታ አስገብቼ መልስ ማግኘት አልቻልኩም በማለት ለኦሮሚያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅሬታውን ባሳወቀው መሠረት፤ የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙት ለአዳማ ከተማና ለጅማ አባ ጅፋር ክለቦች፤ በደብዳቤ ቁጥር FKMO/00861/010 መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ‹‹የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቀረበለትን የክስ አቤተታ ተመልክቶ የብይን ውሳኔ ለመስጠት የክልላችን ክለቦች ሥጋት እየሆነ በመምጣቱ፤ በእንዲህ ዓይነት የፍትሕ መጓደል የክልላችን የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በ2010 ዓ.ም. የፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር መሳተፍ አዳጋች መሆኑ፤ የክልላችን የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የሆናችሁ አዳማ ከተማና ጅማ አባ ጅፋር ክልላችን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብይን ውሳኔ እስከሚሰጥና እልባት ላይ እስከሚደረስ ድረስ በ2010 የፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ለምዝገባም ሆነ በውድድር እንዳትሳተፉ›› በሚል ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡

ፌዴሬሽኑ የፕሪሚየር ሊግ ዕጣ ባወጣበት ዕለት የጅማ አባ ቡና ክለብ ተወካዮች እንዳልተገኙ፤ ነገር ግን ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሥነ ሥርዓቱ መገኘቱን አስታውቋል፡፡ ይህ በፌዴሬሽኑ አገላለፅ ጅማ አባ ቡና በዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ላይ አልተገኘም ማለት ውጤቱን እንደተቀበለው ይወሰዳል ብሎ ማመኑን ያሳያል፡፡

ክለቡ ‹‹ደባ ተሠርቶብኛል›› ሲል ያቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ፤ ‹‹በየደረጃው የማጣራት ሥራ አከናውነናል፡፡ ይሁንና በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ግን ምንም እንዳልተሠራና ውሳኔ ያልተሰጠው ጉዳይ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ፍፁም ስህተት ነው፡፡ ውድድሩ በተፈፀመ ማግስት የሁሉም ተወዳዳሪ ክለቦች ውጤት ተገልጧል፡፡ የሐዋሳ ከተማና የኤሌክትሪክ ክለቦች ውጤት በተላከላቸው ኮሚኒኬ አማካይነት አውቀውታል፡፡ የጅማ አባ ቡና ክለብ ምንም እንዳልደረሰው ወይም እንደማያውቅ ተደርጎ መገለፁ ትክክል ሆኖ አላገኘነውም፡፡ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች የተሠራው ሥራ ተስኗቸው ሳይሆን የራሳቸው በሆኑ አንዳንድ ምክንያቶች ትክክለኛውን እውነታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለመግለፅ አለመፈለጋቸው የፈጠረው ችግር እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጅማ አባ ቡናን አቤቱታ በጥልቀት የተመለከተው ሲሆን፣ ከሚመለከታቸው የክለቡ ኃላፊዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በተደጋጋሚ ተወያይቷል፤›› በማለት በመግለጫው አካቷል፡፡

ፌዴሬሽኑ ከዚህ በተጨማሪ ከጅማ አባ ቡና ክለብ ጋር የተፃፃፋቸውን ደብዳቤዎችም ዘርዝሯል፡፡ በዚሁ መሠረት የጅማ አባ ቡና እግር ኳስ ክለብ ከጨዋታ ውጤት ማስለወጥ ጋር ተያይዞ ላቀረበው ጥያቄ ማስረጃ እንዲያቀርብ፣ በቁጥር 2/አ.እ.ፌ.አ-9/1280 ሰኔ 14 ቀን 2009 ዓ ም በደብዳቤ ተጠይቋል፡፡

የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና የሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ማስረጃዎችን እንዲልኩ ለሁሉም ተቋማት በደብዳቤ ቁጥር  2/አ.እ.ፌ.አ-9/1328 ሐምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. [መግለጫው ሐምሌን 10ኛው ወር ብሎ ነው ያስቀመጠው] መጠየቁን ይገልፃል፡፡ በተመሳሳይም ኢትዮ ቴሌኮም ማስረጃዎቹን እንዲልክ ሐምሌ 20 ቀን 2009 እና ነሐሴ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በፃፋቸው ደብዳቤዎች መጠየቁንም ይገልፃል፡፡

በተጨማሪም አጣሪ ኮሚቴ በመሰየም የማጣራት ሥራ እንደተከናወነ፣ ሪፖርት ተጠናቅሮ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱን የሚገልፀው ፌዴሬሽኑ፣ ማስረጃዎችን በመሰብሰብና በማደራጀት ጉዳዩ በዲሲፕሊን ኮሚቴ እንዲታይ ተደርጓል፡፡ ለጅማ አባ ቡናና ለሚመለከታቸው አካላት ፌዴሬሽኑ አቤቱታውን በአግባቡ እየመረመረ ስለመሆኑ በጽሑፍና በስልክ ተደጋጋሚ መረጃ መስጠቱንም አስታውቋል፡፡ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ነሐሴ 12/12/2009 ዓ.ም. ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መሠረት በማድረግ 29 ገፅ ሰነድና አንድ ሲዲ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በ12/12/2009 ዓ.ም. ስለመላኩም አስታውቋል፡፡

ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን ወደ ፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ መላኩን ተከትሎም ተከታታይ ክትትል ከማድረግ በተጨማሪ፣ የኮሚሽነሮችና ዳኞች ሪፖርቶችና ሌሎች የጽሑፍ ማስረጃዎችን ጨምሮ 12 ምስክሮች በአካል ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ ተገቢውን ክትትልና ጥረት አድርጓል፡፡ የፖሊስ ምርመራ መጠናቀቁን ተከትሎም መዝገቡ በ24/01/2010 ዓ.ም. ለዓቃቤ ሕግ የተላከ ሲሆን፣ የፍትሕ አካል የሚሰጠውን ውሳኔ ፌዴሬሽኑ በመጠበቅ ላይ ስለመሆኑም አመልክቷል፡፡

ፌዴሬሽኑ እንዳስታወቀው፣ ማንኛውም ሰው ወንጀልም ሆነ የሚያስጠይቅ ጥፋት ሠርቶ ሲገኝ በአገሪቱ ሕግ መሠረት የሚዳኝ እንደሚሆን፣ ፌዴሬሽኑም ያሰባሰበውን መነሻ የሚሆኑ ሰነዶች ለፍትሕ አካላት ሰጥቷል፡፡ የፍትሕ አካላቱ የሚሰጡዋቸው ውሳኔዎች የሚያስጠይቁ ሆነው ከተገኙ፣ ፌዴሬሽኑ በደንቡ መሠረት ዕርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ በተገለፀው የሐዋሳ ከተማና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ውጤት ቀደም ሲል የፀደቀ ስለመሆኑም ይፋ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር ይህንኑ አስመልክቶ ያነጋገራቸው እንደ ፌዴሬሽን ምንጮች አገላለጽ ከሆነ፣ ጅማ አባ ቡና በአንድም ሆነ በሌላ ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት ቢኖረው ውሳኔው ሊሆን የሚችለው ለድርጊቱ ምክንያት ናቸው በሚባሉ ግለሰቦች ላይ የዲሲፕሊን ዕርምጃ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ክለቡ የፕሪሚየር ሊግ ቆይታውን የሚያረጋግጥ ውሳኔ ሊኖር እንደማይችል ነው የሚናገሩት፡፡      

 የኦሮሚያ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ፌዴሬሽኑ በመግለጫው እንዳካተተው ጉዳዩ ወደ ዓቃቤ ሕግ ተላልፏል፡፡ እንደ ክልል የፍትሕ አካሉ የሚሰጠውን ውሳኔ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ አቶ ፍሮምሳ ለገሰ ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የስፖርት ተቋማት በተሳተፉበት መድረክ ስለ ክልሉ የስፖርት እንቅስቃሴ የተመለከተ ግምገማ ተደርጓል፡፡ በግምገማው ወቅት ጅማ አባ ቡና ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያቀረበው የፍትሕ ጥያቄ ተገቢው መልስ እንዲያገኝ በየደረጃው የሚገኙ የእግር ኳስ ክለቦች አመራሮች ጠይቀዋል፡፡ በጉዳዩ ክልሉ የወሰደውን አቋም እንደሚደግፍ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጭምር አቶ ፍሮምሳ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ዜጎች የተፈተኑበት የኑሮ ውድነት

በኢትዮጵያ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት የበርካታ ዜጎችን አቅም...

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ተጠየቀ

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸውና በተቀናጀ መልኩ...

ወደ ኋላ የቀረው የሠራተኞች ደኅንነት አጠባበቅ

በአበበ ፍቅር ለሠራተኞች የሚሰጠው የደኅንነት ትኩረት አናሳ በመሆኑ በርካታ ዜጎች...