Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርፕሬዚዳንት ግርማ ምነው በጃገማ ኬሎ ብቻ ተወሰኑ?

ፕሬዚዳንት ግርማ ምነው በጃገማ ኬሎ ብቻ ተወሰኑ?

ቀን:

ከወራቶች በፊት የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባስተላለፈው ዝግጅት፣ ለታዋቂው  የ‹‹በጋው መብረቅ›› ለጄኔራል ጃገማ ኬሎ ሐውልት እንዲቆምላቸው የሚያስተባበር ኮሚቴ መቋቋሙን ሰምቻለሁ፡፡ የኮሚቴው አስተባባሪ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ሲሆኑ፣ ጄኔራል ዋስይሁን ገበየሁም አባል መሆናቸው ተዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንት ግርማ በንጉሡና በደርግ ዘመን በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ተመድበው መሥራታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ታዋቂነትም ያተረፉ እንደመሆናቸው መጠን በተለይ በንጉሡ ዘመን በዕውቀታቸውና በአመራር ብቃታቸው ዓለም እውቅና ከሰጣቸው የቀድሞ ባለሥልጣናት ጋር በቅርበትም ሆነ በርቀት አብረው ሠርተዋል፤ ከዚህም ውስጥ፡-

 

 1. አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣
 2. መኰንን ሀብተ ወልድ፣
 3. ወልደጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣
 4. አስፍሃ ወልደ ሚካኤል፣
 5. ሎሬንሶ ትዕዛዝ፣
 6. ይድነቃቸው ተሰማ፣
 7. ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም፣
 8. ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ፣
 9. ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ፣
 10. ግርማሜ ነዋይ፣
 11. ተስፋዬ ተገኝ፣
 12. በዓሉ ግርማ፣

 

- Advertisement -

ከላይ የቀረቡት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ስማቸውን ስለጠቀስኳቸው የኢትዮጵያ ኩራቶች ለእርስዎ መንገር የድፍረት ያህል ቢሆንብኝም፣ በጊዜ መርዘም ምክንያት ተረስተውና አስታዋሽ አጥተው በመቅረታቸው ሐዘኔን ብርቱ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ‹‹ኤርትራ አትገነጠልም፤ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ አትሆንም፤›› በማለት የተዋጉና በመጨረሻም የገዛ ሽጉጣቸው እየጠጡ የወደቁ ጀግኖች የደርግ ወታደር እየተባሉ ሲላገጥባቸው መስማት ሕሊና የሚያደማ ቢሆንም፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ወደፊት ታሪካቸው እንደሚዘከር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ የኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ፣ የጄኔራል ተሾመ ተሰማ፣ የጄኔራል ተመስገን ገመቹ፣ የኮሎኔል ካሳ ገብረ ማርያምና የሻለቃ ማሞ ተምትሜ ገድልም ሊወሳ የሚገባው ነው፡፡

ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ጄኔራል ጃገማ ኬሎን ጨምሮ ኢትዮጵያን አስከብረው ራሳቸውም ተከብረው ያለፉ ከፍተኛ ባለሟሎች በአንድ ላይ የሚታወሱበት፣ ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ የታሪክ ማጣቀሻ የሚሆን ሐውልት በማቆሙ በኩል በሰዎች ተሰሚነትና የታሪክ ቀረቤታ ስላለዎ፣ ከመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር የስኬት ዘመንዎን ያደምቁ ዘንድ አሳስብዎታለሁ፡፡

(ውብሸት ተክሌ፣ ከአዲስ አበባ)

***

የቦታ ይዞታ ልኬት በሳይንስ ላይ የተመሠረተ አይደለም ወይ?

በአዲስ አበባ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የሽሽግር ጊዜ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት አማካይነት ግንባታቸው ለተጠናቀቁ ቤቶች በሚሰጠው የባለይዞታነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የቦታ ልኬት መሠረት 196 ካሬ ሜትር የነበረው ቦታ በመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የተሰጠው ግን 206 ካሬ ሜትር የሚል ነው፡፡ ልኬት ሳይንስ ላይ የተመሠረተ እስከሆነ ድረስ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ከየት መጣ? በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥስ ሁለት ዓይነት ልኬት እንዴት ይኖራል?

እንዲሁም የሽግግር ጊዜ አገልግሎቱ ጽሕፈት ቤት የምስክር ወረቀት ግንባታቸው ለተጠናቀቀ የሚሰጥ ይበል እንጂ፣ ለሊዝ  ይዞታዎች በዕጣ መሠረት የሚሰጠው የምስክር ወረቀት፣ በይዞታው ውስጥ የግንባታ ፈቃድ ያላቸውንና የተጠናቀቁትን ሁሉ  ግንባታዎች የሚያካትት አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር በይዞታው ውስጥ የተካተቱት ግንባታዎችና ይዞታዎች ልኬት በመሬት ላይ ያለውን ትክክለኛ ሁኔታ የሚያሳይ አይደለም፡፡ ይኼም በተሰጠው የምስክር ወረቅት ላይ ዕምነት እንድናጣ አድርጎናል፡፡

ለምን አልተካተቱም ተብሎ ሲጠየቅም የሚሰጠው መልስ ‹‹ችግር የለውም›› የሚል እየሆነ ተቸግረናል፡፡ ሕጋዊ እንደሚሆን የሚጠበቅበት የምስክር ወረቀት ላይ እንዴት ችግር የለውም ይባላል ሲባሉም ምላሻቸው ‹‹የምስክር ወረቀቱ ሁሉንም የተጠናቀቁ ግንባታዎች እንዲያካትት አይጠበቅበትም፤›› የሚል ነው፡፡ ጠንከር ሲል ደግሞ ‹‹በ1997 ዓ.ም. ከአየር ላይ በተነሳው ፎቶግራፍ መሠረት ግንባታዎቹ በይዞታ ውስጥ ስላልነበሩ ነው፤›› ይላሉ፡፡

ምንአልባት እንደዛ ቢሆን እንኳ በ13 ዓመት ውስጥ ቆሞ የሚቀር፣ አሊያም እንደነበር የሚቆይ ነገር ስለማይኖር፣ ሁሉም ግንባታዎች የተጠናቀቁት ሊዝ በተገባበት ይዞታ ውስጥ መሆኑንና ግንባታዎቹም በዚህ ይዞታ ውስጥ ፈቃድ ያላቸውና ሕጋዊ ስለመሆናቸው ቢመለከቱም፣ ከፋይል ውስጥ በማውጣት ለማረጋገጥ ፍላጎቱም ተነሳሽነቱም የላቸውም፡፡ ልብ በሉ ለዚህ አገልግሎት ተብሎ በሽግግር ጽሕፈት ቤቱ ይጠየቅ የነበረው የምህንድስና አገልግሎት ክፍያ አለ፡፡ ለባለሙያዎቹን ለማጓጓዝ የሚከፈል የትራንስፖርት ወጪና ሌሎችንም እንዲህ ያሉትን ወጪዎች ሳይጨምር ነው ይህ እየተጠየቀ ያለው፡፡

የሽግግር ጽሕፈት ቤቱ ልኬቱን በወሰደበት መንገድ እኛም ለክተን ያገኘነው መጠን ከመረጃው ኤጀንሲ ልኬት ጋር የተጣጣመ ሲሆን፣ ይኼም ከሽግግሩ ጽሕፈት ቤቱ ይልቅ የኤጀንሲው ልኬት በመሬት ላይ ያለውን የይዞታ መጠን በትክክል እንደሚገልጸው ነው፡፡ ይኼም ሆኖ አዲስ የሊዝ ውል የተፈረመው የሊዝ ክፍያውም በዚሁ በመሬት ላይ በሌለና በቀነሰ ሽግግሩ ጽሕፈት ቤት ልኬት መሠረት ነው፡፡

ይኼ ሁኔታ በመንግሥት ገቢ ላይ ያለውን አንድምታ ትተን፣ የቦታን ልኬት መረጃ በተመለከተ ከመረጃ ኤጀንሲ ውጪ ሕጋዊ ኃላፊነት ያለው ባለሥልጣን ማን ነው ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡ የመረጃ ኤጀንሲው መረጃ ተቀባይነት ከሌለው፣ የምዝገባውና የመረጃው ኤጀንሲ ፋይዳ ታዲያ ምንድን ነው? ኤጀንሲው የይዞታ ልኬቶችን የሚያከናውነው በመሣሪያዎች እየተረዳ እንደሆነና ትክክለኛ ስለመሆናቸውም በተመሳሳይ መሣሪያ በከፍተኛ ባለሙያዎች እንደሚረጋገጥ የኤጀንሲው ባለሙያዎች ግን ይናገራሉ፡፡

የሽግግሩ ጽሕፈት ቤት ለምንድን ነው ከመረጃ ኤጀንሲው የሚቀርብለትን ልኬት የማይቀበለው? ቢቀበለው ኑሮ እንደገና ለማስላካት (እጅግ ተራ ለሆነ ልኬት) መሀንዲሱን ለማጓጓዝ የሚወጣውን ወጪ፣ የሚባክነውን ጊዜና መጉላላትን ማስቀረት በተቻለ ነበር፡፡ መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ገቢም እንዲያገኝ ባስቻለው ነበር፡፡

(አምሃ አድማሱ፣ ከአዲስ አበባ)

***

ማስተካከያ

መስከረም 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ‹‹የኦሮሚያና የሶማሌ ግጭት ሙሉ በሙሉ እንዳልቆመ መንግሥት አስታወቀ›› በሚል ርዕስ ባወጣነው ዘገባ ‹‹…በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት መጥፋት ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት አስተላለፉ፤›› የሚለው ሐረግ፣ ‹‹…በሺዎች የሚቆጠሩ ከቀያቸው መፈናቀላቸው ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት አስተላለፉ፤›› በሚል ተስተካክሎ እንዲነበብ  እንጠይቃለን፡፡ ለተፈጠረው ስህተት አንባቢያንን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

ዝግጅት ክፍሉ

 

 

 

              

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...