Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ለኢትዮጵያ አንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር የማቅረብ ፍላጎት አለን››

አቶ አድማሱ ይልማ፣ የኮሜሳ የንግድና የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት  

አቶ አድማሱ ይልማ ታደሰ የኢኮኖሚ ባለሙያ ብቻ ሳይሆኑ፣ በአፍሪካ ከፍተኛ ተቀባይነት ካገኙ የባንክ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች መካከል የሚመደቡ ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ከዚህ ቀደም የደቡብና ምሥራቃዊ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ ባንክ (ፒቲኤ ባንክ) እየተባለ የሚጠራውን ተቋም፣ ወደ ኮሜሳ ንግድና ልማት ባንክ እንዲለወጥ አድርገዋል፡፡ አቶ አድማሱ በፕሬዚዳንትነትና በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩትና ስሙን የቀየረው የንግድና የልማት ባንክ፣ ከቀድሞ አካሄዱ በርካታ ለውጦችን በማከል መደበኛ የኢንቨስትመንት ባንክ አቋም እንዲኖረው፣ ከመንግሥታዊ አሠራርና ቢሮክራሲ ጫናዎች በመጠኑም ቢሆን እንዲላቀቅና ዘመናዊነትን እንዲላበስ ያደረጉ ባለሙያ ስለመሆናቸውም አብረዋቸው የሚሠሩ ሰዎች ይናገሩላቸዋል፡፡ ከለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፖሊቲካል ሳይንስ ዊትስ ቢዝነስ ስኩል የመጀመርያ ዲግሪያቸውን፣ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዌስተርን ኦንታሪዮ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ አድማሱ፣ በሃርቫርድ ቢዝነስ ስኩል፣ ኢንሲድ በተባለው የፈረንሣይ ታዋቂ የድኅረ ምረቃ የቢዝነስ ትምህርት ቤትም እንዲሁ ትምርታቸውን ተከታትለው ተመርቀዋል፡፡ የሚመሩት ተቋም በ30 ዓመታት ውስጥ ካስመዘገበው ይልቅ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ያሳየው ከፍተኛ አፈጻጸም በኮሜሳ አባል አገሮች ዘንድ አቶ አድማሱን ተመራጭ ኃላፊ እንዲሆኑ ከማድረጉም ባሻገር፣ ለተጨማሪ አምስት ዓመታት ባንኩን እየመሩ እንዲቀጥሉ አብቅቷቸዋል፡፡ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር የተነሳው የባንኩ ጠቅላላ ሀብት በአሁኑ ወቅት ወደ አሥር ቢሊዮን ዶላር አሻቅቧል፡፡ እንዲህ ያሉ በርካታ ለውጦችን ያስመዘገበው ባንክ፣ በመጪዎቹ ዓመታት ውስጥም የ100 ሚሊዮን ዶላር የተከፈለ ካፒታሉን ከፍ የማድረግ ዕቅድ ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ የ28 ሚሊዮን ዶላር የአክሲዮን ድርሻ ያላት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ስለሚመለከተውና አገሪቱ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር ከባንኩ ማግኘት ስለምትችልበት ዕድል ብርሃኑ ፈቃደ ከአቶ አድማሱ ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ካለፈው ጥር ወር ወዲህ ማለትም ባንኩን ከቀድሞው ፒቲኤ ባንክ ወደ የንግድና የልማት ባንክ እንዲለወጥና ብራንዱ እንዲሻሻል ካደረጋችሁበት ጊዜ ጀምሮ የባንኩ አዳዲስ ለውጦች ምንድን ናቸው?

አቶ አድማሱ፡- አዎን ባንኩን ሪብራንድ ወይም እንደ አዲስ በማሻሻል ሥራ የጀመርነው የባንኩ ስትራቴጂ አንዱ አካል በመሆኑ ነው፡፡ የባንኩን የሥራ አድማስ ከማስፋት ባሻገር የባንኩን ዓላማዎችና ተግባራት በደንብ ግልጽና የተብራሩ እንዲሆኑ ማድረግ በማስፈለጉም ጭምር ነው፣ ባንኩን እንደ አዲስ ከስያሜው ጀምሮ ለውጥ ተደርጎበት እንዲንቀሳቀስ የተፈለገው፡፡ ባንኩ በአብዛኛው የንግድና የልማት ሥራዎች ላይ የሚሳተፍ እንደ መሆኑ መጠን፣ የቀድሞው ፒቲኤ የሚለው ስያሜው ይህንን የባንኩን የሥራ ዘርፍ በሚገባና በግልጽ አያመላክትም ነበር፡፡ የንግድ ድጋፍ ስለሚሰጥበት ወይም ‹‹ፕሪፈረንሺያል ትሬድ›› ጉዳይ ነበር የሚገልጸው፡፡ ባንኮች ግን በአብዛኛው ስለሚያከናውኑት ተግባር፣ ዓላማና ተልዕኮ በይፋ በማሳወቅ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመሆኑም ለውጥ እንደሚያስፈልግ ያቀረብነው ሐሳብ ተቀባይት ያገኘው እ.ኤ.አ. በ2013 ነበር፡፡ ለውጡን ወደ ተግባር ለመተግበር የተስማማነው ግን እ.ኤ.አ. በ2016/17 ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ በአብዛኛው የባንኩን ሥራዎች ዳግመኛ በማሻሻል ጠንካራ አቅም እንዲላበስ የማድረግና የባንኩን ማንነት እንደ አዲስ የመገንባት ሥራ ነበር፡፡ እንደ ሞዛምቢክ፣ ስዋዚላንድ፣ ደቡብ ሱዳን ያሉ የኮሜሳ አባል ያልሆኑ አገሮችም በአባልነት እየተቀላቀሉ ስለመጡ ለባንኩ አዲስ ማንነት በመፍጠር፣ ገለልተኛ፣ ቢዝነስ ተኮርና ቀጣናው ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ የሚያደርግ የንግድና የልማት ባንክ እናድርገው የሚል ተልዕኮ ስለነበረ ነው ባንኩን እንደ አዲስ ማሻሻል ያስፈለገው፡፡

ከማሻሻያው በኋላ የባንኩ እንቅስቃሴ ነቃ ብሏል፡፡ የባንኩ አባላትና አጋሮቻችን በተሠራው ሥራ ደስተኞች ናቸው፡፡ በርካታ ዘመናዊ አሠራርን የሚከተሉ ተግባራትንም አምጥተናል፡፡ በብድር ትንተና ረገድም ባንኩ ብዙ ለውጦችን ማስመዝገቡ ታይቷል፡፡ ባንኩ ከብድር አኳያ ያካበተው ሀብት በየዓመቱ 11 በመቶ እያደገ መጥቷል፡፡ እንደ ኬንያና ኡጋንዳ ባሉ አገሮች ውስጥ በርካታ አዳዲስ የንግድ ዘርፎች ላይ ድጋፍ አድርገናል፡፡ በሌሎችም ባላዳረስናቸው አገሮች ውስጥ የንግድና የልማት ሥራዎችን የመደገፍ ተግባራችንን እናስፋፋለን፡፡ ለሞሪሺየስ የምንሰጣቸው ብድሮች አሉ፡፡ በሞዛምቢክም በርካታ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ስምምነቶችን አድርገናል፡፡ በኢትዮጵያም ለበርካታ ፕሮጀክቶች ብድር እንዲለቀቅ አድርገናል፡፡ ለአኮር ሆቴል ፕሮጀክት የሚለቀቀውን ጨምሮ ለጋቴፕሮ ብረታ ብረት ፋብሪካም ብድር መልቀቅ እንጀምራለን፡፡ የረዥም ጊዜ ደንበኛችን ለሆነው ለኢትዮጵያ አየር መንገድም የምንሰጠው ድጋፍ እንደቀጠለ ሲሆን፣ በዚሁ ዓመት የሚለቀቅለት ብድር ይኖረዋል፡፡    

ሪፖርተር፡- ለአየር መንገዱ የሚለቀቀው ከዚህ ቀደም የጠቀሱት የ100 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማለት ነው?

አቶ አድማሱ፡- አዎን፡፡ እርግጥ 100 ሚሊዮን ዶላር የተለያዩ ፋሲሊቲዎች ድምር ነው፡፡ ከእነሱ ጋር ሁሌም በመነጋገርና ብድር በጠየቁ ጊዜም በማቅረብ ላይ የተመሠረተ የረጅም ጊዜ ግንኙነት አለ፡፡ ለእነሱ ሁሌም ክፍት የተደረገ በር አለን፡፡ ሁሌም እንደሚያስፈልጋቸው መጠን መበደር ይችላሉ፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሻገር ግን ሌሎችም በርካታ ድርድር ሲደረግባቸው የቆዩ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ጥቂት ጊዜ የወሰዱ ቢሆኑም በርከት ያሉ ፕሮጀክቶች አሉን፡፡ እርግጥ አሁንም ስማቸውን ለመጥቀስ ጊዜው ገና ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣ የንግድና የልማት እንቅስቃሴ መኖሩን መናገር እችላለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- ባለፈው ጥር ወር ስንገናኝ ከላይ ለጠቀስናቸው ሦስቱ ተቋማት የሚለቀቀው የብድር መጠን በጠቅላላው 60 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሆን ገልጸውልኝ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ገንዘብ ለኩባንያዎቹ መለቀቁ ተረጋግጧል ማለት ነው፡፡

አቶ አድማሱ፡- አዎን በትክክል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ከማምራታችን በፊት ባንኩ የልማት ባንክ እንደ መሆኑ መጠን በንግድ ፋይናንስና በልማት ፋይናንስ መካከል ያለውን ሚዛን እንዴት ነው የምታስጠብቁት? ለንግድ ሥራዎች የሚሰጠው ብድር ከልማት ብድር እንዳይበልጥ ወይም የንግድ ፋይናንስ ከልማት ፋይናንስ ይልቅ ከፍተኛ እንዳይሆን የምታደርጉበት አሠራር ምንድነው? ሚዛኑን እንዴት ነው የምታስጠብቁት?

አቶ አድማሱ፡- ይህ ጉዳይ የውይይት ርዕስ በመሆን ለተወሰነ ጊዜ መነጋሪያ ነበር፡፡ በንግድ መስክ በርካታ ክፍተቶች አሉ፡፡ በኢንቨስትመንት መስክ በተለይ በመሠረተ ልማት አውታሮች በኩልም በርካታ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ በአነስተኛና በመካከለኛ ድርጅቶች ፋይናንስ አቅርቦት ላይ ትልቅ ክፍተቶች አሉ፡፡ ልክ እንደዚህ ሁሉ ለኢንዱስትሪዎች ለሚቀርበው ፋይናንስ ካለው ፍላጎት አኳያ ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ በግብርናውም እንዲሁ ነው፡፡ ጠቅላላውን የልማት እንቅስቃሴና የፋይናንስ ድጋፍ ካየን፣ በአብዛኛው በርካታ ክፍተቶችና ጉድለቶች የሚታዩበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስንቋቋም የንግድና የልማት ባንክ ሆነን ነው፡፡ ልማት ሲባልም ሰፊ ትርጓሜ የሚይዝ እንደ መሆኑ መጠን ለመሥራት የሚያስችሉን በርካታ መስኮች አሉ፡፡ ይሁንና የረዥም ጊዜ ብድር ለመስጠት የሚያስችል ገንዘብ ማሰባሰብ ግን እንደ አጭር ጊዜ ብድር ቀላል አይደለም፡፡ የንግዱ ዓለም የአጭር ጊዜ ብድር ቢቀርብለት ይስማማዋል፡፡ የረጅም ጊዜ ብድር እናቅርብለት ብንል ግን ዘርፉ አይመቸውም፡፡ እኛ ተቀማጭ አናሰባስብም፡፡ በዚህ መንገድ የምንንቀሳቀስ አይደለንም፡፡ ይልቁንም ለብድር የምናውለውን ገንዘብ የምናሰባስበው ከቦንድ ሽያጭ አሊያም በልዩ የብድር አቅርቦት መስክ የሚውል ገንዘብ የምናገኘው ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከቻይና ልማት ባንክ፣ ከአውሮፓ ኅብረት ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ከጀርመን ኬኤፍደብሊው ባንክ ከመሳሰሉት አጋሮቻችን ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በካፒታል ገበያው ውስጥ የራሳችንን ቦንድ በመሸጥ ገንዘብ እናሰባስባለን፡፡ ይህንኑ ለብድር እናውላለን፡፡ በመሆኑም አብዛኛው ለብድር የምናውለው ፈንድ የአጭር ጊዜ ነው፡፡ እርግጥ የረዥም ጊዜ ብድርም እንሰጣለን፡፡ የፕሮጀክቶችና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ በማድረግ ረገድ የረዥም ጊዜ ልምድ አለን፡፡ የፋይናንስ ሪፖርታችንም ይኼው የብድር ዘርፍ እያደገ እንደመጣ ያሳያል፡፡ ሆኖም ግን ለአጭር ጊዜ ብድር የምንሰጠውን ያህል ለረዥም ጊዜ ብድር የሚውል ገንዘብ እንደምንፈልገው መጠን አናገኝም፡፡ ስለዚህ ለአጭር ጊዜ ብድር የሚውል ገንዘብ ማግኘት በጣም ቀላል ነው፡፡ በርካታ አባል አገሮችም ስትራቴጂካዊ የሆኑ የንግድ ፋሲሊቲዎች ተከፍተውላቸው ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን ፋይናንስ የሚያደርጉበት ገንዘብ ይፈልጋሉ፡፡ በጣም አስፈላጊ የሚባሉ እንደ ነዳጅ፣ ምግብ፣ የመድኃኒት ምርቶችን ማስገባት ይፈልጋሉ፡፡ ይህ እንግዲህ የኢነርጂ፣ የምግብ፣ እንዲሁም የጤና ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመደገፍ የ360 ቀናት፣ የ180 ቀናት፣ አንዳንዴም ከዚህ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ የአጭር ጊዜ ብድር እናመቻችላቸዋለን፡፡ እንደ ባንክ ጥሩ የሚባለው የልማት ብድር የረዥም ጊዜ ብድር እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ይህ በጣም ከባድ ቢሆንም መውሰድ እስከምንችለው ድረስ በዚህ ረገድ እንንቀሳቀሳለን፡፡ ይህ የብድር ዓይነት ቁጥብ ሀብት የሚቀርብበት፣ የተወሰነ እንደ መሆኑ መጠን ለልማት የሚውለውን ገንዘብ ካመቻቸን በኋላ ግን ቀጣዩን የንግድ ፋይናንስ እንመለከታለን፡፡ ለእኛም ብቻ ሳይሆን ለአባል አገሮችም ብዙ ፍላጎት ያለውና በብዛትም ለአገሮቹ የሚቀርበውን ብድር እንመለከታለን፡፡

ለአጭር ጊዜ ብድር የሚሆን ገንዘብ ማግኘት እስከቻልነው ድረስ እንቀበላለን፡፡ የረዥም ጊዜም ሆነ የአጭር ጊዜ ብድሮች ዋጋ አላቸው፡፡ ነገር አንዱ የሌላው ጠላት መሆን የለበትም፡፡ የረዥም ጊዜው ከአጭር ጊዜው ፋይናንስ የተሻለ ነው፡፡ የአጭር ጊዜውም ግን ጥሩ ነው፡፡ ስለዚህ በሁለቱ መካከል ያለውን አቅርቦት ማጣጣም ከቻልን እሰየው እንላለን፡፡ ሆኖም የአጭር ጊዜ ብድር ለማቅረብ ብዙ ዕድልና ፍላጎት ስላለ እንደ ምግብ፣ ኢነርጂ፣ መድኃኒት ያሉትን ለማሟላት ሲያስፈልግ እኛ ማገዝ ይጠበቅብናል፡፡ ስለዚህ በአጭርና በረዥም ጊዜ ብድር መካከል የግድ የማቻቻል ሥራ ማከናወን ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም የየራቸው የተገደበ የፋይናንስ መጠን ስለሚፈልጉ ነው፡፡ አንዳንዴ ለንግድ የሚቀርበው 70 ወይም 60 በመቶ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴ የረዥም ጊዜ ብድር ሊወጣ ይችላል፡፡ ለእኛም ቢሆን የተሻለ ዋጋ የሚያስገኝልን የረጅም ጊዜ ብድር በመሆኑ በተቻለን መጠን ትኩረት በመስጠት የሚፈለገውን ፋይናንስ ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡     

ሪፖርተር፡- ምንም እንኳ ተቀማጭ የማይሰበሰብ ባንክ ቢሆንም፣ ከአባል አገሮች ማዕከላዊ ባንኮች (እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያሉ) ተቀማጭ ይሰበስባል፡፡ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንዲህ ያለውን ተቀማጭ ታገኛላችሁ? ካልሆነስ ብሔራዊ ባንኩ ገንዘብ ማስቀመጥ ቢፈልግ ዕድሉን ማግኘት ይችላል?

አቶ አድማሱ፡- የብድር ገንዘብ የምናገኘው ከካፒታል ገበያዎች ነው፡፡ ሌሎች ኢንቨስተሮች የሚያቀርቧቸውንና ለብድር የሚውሉ የቦንድ ሰነዶችን (ፕራይቬት ፕሌስመንትስ) ከተቀማጭ ጋር ተመሳሳይ በመሆናቸው እነሱንም እንቀበላለን፡፡ ከተቋማት ኢንቨስተሮችና ከማዕከላዊ ባንኮች የሚመጡ ተቀማጮችንም ከዚህ ቀደም ስንሰበስብ ቆይተናል፡፡ አሁንም ይህንን በማድረግ ወደፊትም እየሠራንበት እንቀጥላለን፡፡ ይኼው አሠራራችን ለአባል አገሮች ቀርቦላቸው እንዲነጋገሩበትም ተደርጓል፡፡ ሌሎችንም መስኮች በመመልከት ለብድር የምናውላቸውን ገንዘቦች የምናስፋፋበትን መንገድ እናፈላልጋለን፡፡   

ሪፖርተር፡- በባንካችሁ ‹‹ክላስ ቢ›› የሚባሉ ባለአክሲዮኖችና ኢንቨስተሮች አሉ፡፡ እንደ ሞሪሸስ ያሉ አገሮች በዚህ ረገድ ብሔራዊ የጡረታ ፈንድ አላቸው፡፡ ይህንን ገንዘብ በባንኩ ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡ በኢትዮጵያ ይህ የጡረታ ፈንድ ቢኖርም፣ እንደ እናንተ ባለው ባንክ ውስጥ ኢንቨስት አልተደረገም፡፡ ምናልባት ስለዚህ ጉዳይ ከብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግራችሁ ከሆነ ምንድነው ምላሻቸው? 

አቶ አድማሱ፡- አዎን በጡረታ ፈንድ ረገድ ያቀረብነው የኢንቨስትመንት ዕድል ሁሉም አባል አገሮች እንዲሳተፉበት ጭምር ነው፡፡ የትኛውንም በኢትዮጵያ የሚገኝ ተቋም በባንካችን ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርግ ፍላጎት አለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባለድርሻዎች ባንካችን ስለሚሰጣቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች ግንዛቤው እንዳላቸው እናውቃለን፡፡ ሆኖም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ግን አብዛኞቹ ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚችሉ ተቋማት የዶላር ተቀማጭ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ይልቅ ተቀማጫቸው በብር የሚደረግ ነው፡፡ ወደ ብሔራዊ ባንክ ሄደው ዶላር ገዝተው በእኛ ባንክ ውስጥ አክሲዮን መግዛት እንፈልጋለን የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡ፣ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በቀላሉ የሚግባቡ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ካለው የዶላር እጥረት አኳያ እንዲህ ያለው ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው የውጭ ኢንቨስትመንት ለመንግሥት አንገብጋቢ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ አቅጣጫ በእርግጥም ተገቢ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ ወደፊት ከባንካችን ለአገሮች ከሚቀርበው የአክሰዮን ድርሻ ውጪ ባለው ረድፍ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉ፣ አክሲዮን መግዛት የሚፈልጉ ተቋማት ካሉ ግን በራችን ክፍት መሆኑን ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር ውስጥ የመገበያያ ገንዘብ ላይ ስለተመረኮዘው አገልግሎታችሁ ምን ማለት ይቻላል? ለምሳሌ ብርን መሠረት ያደረገ አገልግሎት ለመንግሥትም ይሁን ለሌሎች ተቋማት እንዴት ልታቀርቡ ትችላላችሁ?

አቶ አድማሱ፡- ይህ በጣም አስደሳች ከሚባሉት የባንኩ አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሒደቶቹ ላላ ተደርገዋል፡፡ በዚህ መስክ የሊዝ ፋይናንስ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሊኖሩ የሚችሉ ዕድሎችን ለመጠቀም እንፈልጋለን፡፡ ጥናቶችን አካሄደናል፡፡ ጥሩ ገበያ እንደሚኖር አውቀናል፡፡ ነገር ግን በጣም ትልቅ የሚባል የሰዎች ስብስብ ያለው ባንክ ስላልሆነ፣ በሊዝ ፋይናንስ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ እኛ እንደ ጅምላ ንግድ የምንንቀሳቀስ ባንክ በመሆናችን በአነስተኛ ግብይት ውስጥ ብዙም አንሳተፍም፡፡ ሆኖም በሊዝ ፋይናንስ ረገድ በመጠኑ ለመግባት እንፈልጋለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት የመጪዎቹን የአምስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች የተመለከተው ውይይት ይገኝበታል፡፡ አገሮች በባንኩ ያላቸውን የአክሲዮን ድርሻ እንዲያሳድጉ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል መጠን እንዲጨምር ለአባላቱ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

አቶ አድማሱ፡- በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ለማሰባሰብ ያቀድነው ዝቅተኛው የካፒታል መጠን 100 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ሆኖም ይህ ገንዘብ እንደሚኖረው ዓለም አቀፍ ሁኔታ አኳያ ከፍ ሊደረግ የሚችል እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ለአካባቢያችን ያለው ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ፣ በእኛ ባንክ ላይ ያለው ፍላጎትም ታክሎበት የተጠየቀው ገንዘብ ከዚህም በላይ መሆን ይችል እንደነበር እናስባለን፡፡ በዚህ ዓመትና በሚቀጥለውም ጭምር በርካታ አክሲዮን የመግዛት ፍላጎት እንዳለና እንደሚኖር ስለሚጠበቅ፣ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደሚመጣ እንጠብቃለን፡፡   

ሪፖርተር፡- የአባል አገሮች ሚና ምንድነው? የአክሲዮን ድርሻቸውን ያሳድጋሉ ወይስ ምንድነው የሚጠበቀው?

አቶ አድማሱ፡- እ.ኤ.አ. በ2019 የባንኩን የካፒታል መጠን ማሳደግን በተመለከተ የሚቀርብ አጀንዳ ይኖራል፡፡ ይህ አጀንዳም በባለአክሲዮኖች ምክክር ከተደረገበት በኋላ ምን መደረግ እንዳለበት ይወሰናል፡፡ ጉባዔው በመጪው ዓመት በኡጋንዳ ካምፓላ ይካሄዳል፡፡ የ2019 ጠቅላላ ጉባዔ ደግሞ በዛምቢያ ስለሚካሄድ በዚያ ወቅት የባንኩ የካፒታል መጠንና ሌሎችም አጀንዳዎች ውሳኔ ይሰጥባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የእያንዳንዱ አክሲዮን ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ብጠይቅዎ ቅር የሚልዎ አይመስለኝም፡፡ ባለአክሲዮኖች ድርሻ ሲገዙ በቅድሚያ የ20 በመቶ ክፍያ ይፈጽማሉ፡፡ ቀሪው ግን ቀስ በቀስ የሚከፈል እንደሆነ ከባንኩ ሰነዶች ተረድቻለሁ፡፡ በአባል አገሮችና በሌሎች ባለአክሲዮኖች መካከል ያለው የአክሲዮን ድርሻና አከፋፈል ምን ይመስላል?

አቶ አድማሱ፡- ባንኩ ሁለት ዓይነት የአክሲዮን ሽያጮችን ያካሂዳል፡፡ አንደኛው ‹‹ምድብ ሀ›› ወይም ‹‹ክላስ ኤ›› አክሲዮኖችን የሚወክል ሲሆን፣ ሌላኛው ‹‹ክላስ ቢ›› ወይም ‹‹ምድብ ለ›› ልንለው የምንችለው የአክሲዮን ዓይነት የሚወክል ነው፡፡ ‹‹ክላስ ኤ›› የሚባለውን የአክሲዮን ዓይነት መግዛት የሚችሉት አባል አገሮችና ሌሎች ሉዓላዊ አገሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም 20 በመቶውን አክሲዮን በገዙበት ወቅት በቅድሚያ ይከፍሉና ቀሪውን 80 በመቶ ድርሻ ቀስ በቀስ እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ ‹‹ክላስ ቢ›› የሚባሉት ባለአክሰዮኖች ግን የገዙትን አክሲዮን በሙሉ ወዲያኑ ሲከፈሉ ነው አባል የሚሆኑት፡፡ በዚህ መንገድ የሚመደቡ አክሲዮኖችን ባንኩ ያቀርባል፡፡ ‹‹ክላስ ኤ›› ባለአክሲዮኖች የትርፍ ድርሻ (ዲቪደንድ) በአብዛኛው የሚታሰብላቸው እዚያው በባንኩ ውስጥ እየተጠራቀመ አክሲዮናቸውን ለማሳደግ እንዲያውሉት በሚደረግበት አሠራር ነው፡፡ ‹‹ክላስ ቢ›› ባለአክሲዮኖች በአብዛኛው ተቋማት ሲሆኑ፣ የትርፍ ድርሻ በገንዘብም በአክሲዮን ድርሻም ማሳደጊያነት የማዋል ምርጫው አላቸው፡፡ ይሁንና አብዛኞቹ ባለአክሲዮኖች በባንኩ እንዲጠራቀምላቸው የሚጠይቁ በመሆናቸው የአክሲዮን ድርሻቸውን ለማሳደግ ያውሉታል፡፡ ይህም የባንኩን ካፒታል በማሳደግ ረገድ ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በባንኩ የኢትዮጵያ የአክሲዮን ድርሻ 7.15 በመቶ እንደሆነና በገንዘብ ሲቀየር ወደ 28.7 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሆን ከባንኩ ሪፖርት ያየሁ ይመስለኛል፡፡ አገሪቱ ያላት ድርሻ ይኼው ነው ወይስ ለውጥ ተደርጎበታል?

አቶ አድማሱ፡- እርግጥ ቁጥሮቹን አላየኋቸውም፡፡ በሪፖርት ሰነዱ ውስጥ የተካተተ በመሆኑ ዝርዝሩን እዚያ ውስጥ ማግኘት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የአምስት ዓመቱ የባንኩ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አምስት ወይም ስድስት አንኳር ዓላማዎችን አካቷል፡፡ ዕቅዱ ለኢትዮጵያ ብሎም ለሌሎች አገሮች ምን ያስገኝላቸዋል? ለአብነት ያህል ባለፈው ጊዜ ለኢትዮጵያ በአንድ ጊዜ እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብድር ማቅረብ እንደሚችል ገልጸው ነበር፡፡ በአዲሱ ዕቅድ ይህ መጠን ያድጋል ማለት ይቻላል?

አቶ አድማሱ፡- እንደማስበው ባንኩ ሲያድግ የሚያቀርበው የብድር መጠን ልክም አብሮ ያድጋል፡፡ ለአሁኑ ለኢትዮጵያ የገባነው የብድር መጠን በ200 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ የሚገመት ነው፡፡ አብዛኛው የብድር መጠን የአጭር ጊዜ ሲሆን፣ የሥራ ማስኬጃ ብድር የተሰጣቸው ደንበኞችም አሉን፡፡ እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ተጨማሪ ገንዘብም በመጪው አንድ ወይም ሁለት ዓመት ውስጥ ለማቅረብ ዝግጁ ነን፡፡ ፍላጎቱ እስካለ ድረስ ማለት ነው፡፡ ለዚህ የሚሆን አቅም አለ፡፡ ወደፊት የባንኩ የመስፋፋትና የማደግ ዕቅድ ይበልጥ ተግባራዊ እየሆነ ሲሄድ ግን ብዙ አማራጭ ያላቸው መስኮች ለኢትዮጵያ አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማቅረብ የምንችልበት ዕድል አለ፡፡ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ለኢትዮጵያ አንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር የማቅረብ ፍላጎት አለን፡፡ ይሁንና ይህንን የብድር መጠን ለማቅረብ ተስማሚና የሚቀርቡ መጠይቆችን የሚያሟሉ ፕሮጀክቶች መቅረብ አለባቸው፡፡ አንደኛው መጠይቅ የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት የሚችሉ ዘርፎች ላይ የሚሰማሩ እንዲሆኑ የሚጠይቀው ነው፡፡ የምናበድረው በዶላር እንደ መሆኑ መጠን ስንቀበልም በዶላር ነው፡፡ በብር እናበድር ብንል የምንጨምረው እሴት አይኖርም፡፡ የአገር ውስጥ ባንኮች በብር የማበደር ድርሻቸው ስለሚጎላ እነሱን ለማገዝ እንጂ ከእነሱ ጋር መወዳደር አንሻም፡፡ በዚያም ላይ ብሔራዊ ባንክ የሚጠይቀው ዶላር የሚያመነጩ ፕሮጀክቶች በዶላር እንዲበደሩ በመሆኑ፣ ከዚህ አኳያም ቢሆን ብድር ልናቀርብላቸው የሚገቡት ፕሮጀክቶች የዶላር ምንጭ ያላቸው ወይም ወደ ውጭ ምርቶቻቸውን የሚልኩ፣ አሊያም ዶላር በሚያስገኝ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙት አዋጭ ፕሮጀክቶች ናቸው ማለት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የባንኩ የብድር አመላለስ ሒደት ምን ይመስላል? ተመላሽ የማይደረግ የብድር መጠን ምን ያህል ነው? የትኛው አገር፣ ቀጣና ወይም የትኛው ኢንቨስተር ነው ብድር ወስዶ ባለመመለሱ በጥቁር መዝገብ ውስጥ የሠፈረው?

አቶ አድማሱ፡- አገሮችን ጥቁር መዝገብ ውስጥ አናስገባም፡፡ ሆኖም የተበላሸ የብድር ክምችት ያለባቸው አገሮች ግን አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለት አገሮች በርከት ያለ የተበላሸ የብድር ዕዳ እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ ከፍተኛውን የተበላሸ የብድር ዕዳ የያዙት ዛምቢያና ሱዳን ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የብድር ዕዳውን መክፈል ያልቻሉት በምን ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል?

አቶ አድማሱ፡- የዛምቢያው ውስብስብ ታሪክ ያለው ነው፡፡ ብድር የተሰጠበት ፕሮጀክት በጣም ጥሩና አዋጭ ነበር፡፡ ሆኖም የፍርድ ቤት ጉዳይ ስለተነሳበት የብድር ዕዳውን ከመክፈል በመዘግየቱ እንጂ ፕሮጀክቱ በጣም የሚያጓጓ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም የሚጠቅሷቸውና አዋጭ የሚባሉ ዘርፎች እንዳሉ ሆነው፣ ወደፊት በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች ውስጥ በየትኞቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ ኢንቨስት የማድረግና ብድር የማቅረብ ሐሳብ አላችሁ?

አቶ አድማሱ፡- እንደማስበው በርካታ መስኮች አሉ፡፡ አገሮች የየራሳቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሏቸው፡፡ ኢትዮጵያን ካየን በወጪ ንግድ ዘርፍ ብዙ መሥራት ትፈልጋለች፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ ነው፡፡ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ድጋፍ መስጠት አንዱ ፍላጎታችን ነው፡፡ ሌሎች ተስፋ የሚሰጡ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው፡፡ ሌላው እንደ ስኳር ልማት ያለውን መስክ የሚመለከት ድጋፍ የመስጠት ፍላጎት አለን፡፡ ኢትዮጵያ በስኳር ልማት ረገድ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እየገነባች ቢሆንም፣ ተግባራዊነታቸው ላይ ግን ትንሽ ችግር ያለበት ሆኖ ይታያል፡፡ አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች የተጓተቱ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም የስኳር ዘርፍ ተስፋ የሚጣልበት በመሆኑ ወደፊት በዚህ ዘርፍ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ የምንችልበት ዕድል ያለ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ተስፋ የሚደረገው የማዕድን ዘርፍ ነው፡፡ በማዕድን ዘርፍ በተለይ የፖታሽ ፕሮጀክቱ ትልቅ ተስፋ የሚታይበት በመሆኑ ለእኛ ተስማሚ ነው፡፡ ቱሪዝምም እንደዚሁ ብዙ ዕድል አለው፡፡ እነዚህ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ በመሆናቸው ጭምር ብድር ልናቀርብላቸው እንፈልጋለን፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍም ቢሆን ትልቅ አቅም ያለው ነው፡፡ እነዚህ በአብዛኛው ልማት ተኮር በመሆናቸው ትልቅ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ዶላር ስናበድር ዶላር በሚያመነጩ መስኮች ላይ ቢሆን እንደሚመረጥ ባለድርሻዎቻችን ስለሚመክሩን በአብዛኛው እንዲህ ባሉት ላይ እናተኩራለን እንጂ፣ የገቢ ንግድን በመተካት ረገድም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ ትልቅ አቅም ያላቸው ፕሮጀክቶች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...