Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ለወጪ ንግድ የሰጠው ትኩረት ተጋኗል እየተባለ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሰሞኑ ዕርምጃዎች ውስጥ የአገሪቱ ባንኮች ከወጪ ንግድ ባሻገር ላሉት ዘርፎች የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ ገደብ እንደሚያስቀምጥ ማስታወቁ አንዱ ነው፡፡ ይህ አሠራር ባንኮች በዓመት ከምትሰጡት ጠቅላላ ብድር ውስጥ እንደሚወሰነው መጠን ለኢኮኖሚው ዘርፍ እንዲያውሉ የሚጠይቅ ነው ተብሏል፡፡

ዕርምጃው ግን ብዥታ መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚና የባንክ ባለሙያዎች እንዲህ ያለው ውሳኔ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን እንደሚያስከትል ገልጸዋል፡፡ ከተፅዕኖዎቹ ባሻገር ለወጪ ንግድ ዘርፍ የሚሰጠው ብድር ከፍ እንዲልና ላኪዎች እንዲበረታቱ ለማድረግ ተስቦ የሚተገበር አሠራር ነው በማለት ገዥው ባንክ የሚያስቀምጠው የብድር ጣሪያ አግባብነቱ አልታያቸውም፡፡

ምክንያታቸው ደግሞ አሁንም ቢሆን ለወጪ ንግድ ዘርፍ የሚሰጠው ብድር ከሌሎች ዘርፎች እንዳልተናነሰ የሚገልጽ ነው፡፡ እንደ አብነት የሚጠቅሱትም በ2008 ዓ.ም. ለዚህ ዘርፍ የተሰጠው ብድር 12 ቢሊዮን ብር ገደማ መሆኑን ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. ደግሞ ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ይህ ለሌሎች ዘርፎች ከተሰጠው ብድር አንፃር ሲታይ ከፍተኛ በመሆኑ፣ የወጪ ንግዱን ለማበረታታት ተብሎ አዲስ የብድር አሰጣጥ እንዲተገበር የሚደረግበት አካሄድ አላሳመናቸውም፡፡

ብሔራዊ ባንክ ለባንኮቹ ትዕዛዝ ሳይሰጥ ለወጪ ንግድ ዘርፍ ይህን ያህል ብድር እየሰጡ በሚገኙበት ወቅት በአንፃሩ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ እያሽቆለቆለ መምጣቱ ሊታሰብበት እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ በ2008 ዓ.ም. 12 ቢሊዮን ብር ብድር የተሰጠው ዘርፍ ያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. ለወጪ ንግድ ዘርፉ የተሰጠው የብድር መጠን ከእጥፍ በላይ አድጎም የተገኘው ግን 3.1 ቢሊዮን ዶላር ብቻ በመሆኑ፣ ዶላሩ የት እየገባ ነው? የሚል ጥያቄ አስከትሏል፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያለው ጉዳይ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል እንጂ፣ ዘርፉ እንዳሻው ብድር ያግኝ ብሎ መነሳት ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው የባንክ ተዋናዮች እየተናገሩ ነው፡፡ መንግሥት እንዲህ ያለ የተለየ ድጋፍ ሲያደርግ በምላሹም የተሰጠው ብድር በትክክል ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ የመከታተል ግዴታ እንደሚኖርበትም እየተገለጸ ይገኛል፡፡

የንግድ ባንኮች ከዚህ በኃላ ከኤክስፖርት ውጪ ላሉ ዘርፎች የሚሰጡት ብድር ላይ ገደብ እንደሚቀመጥበት ታውቋል፡፡ ባንኮች በሚቀመጥላቸው የብድር ጣርያ መሠረት ብድር እንዲሰጡ ከውሳኔ ላይ የተደረሰው የወጪ ንግድ እንዲሻሻል ለማበረታታት ነው ተብሏል፡፡

መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች ኃላፊዎች በሰጠው ማብራሪያ፣ ከኤክስፖርት ውጪ ላሉ ብድሮች የሚቀመጠውን የብድር ጣርያ መጠን ምን ያህል ወደፊት እንደሚገለጽላቸው ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ውሳኔ መሠረት ለገቢ ንግድ፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪና ለመሳሰሉት ዘርፎች የሚሰጠው ብድር ከጠቅላላ ብድር ውስጥ ምን ያህል ድርሻ መያዝ እንዳለበት ብሔራዊ ባንክ ያሳውቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለወጪ ንግድ የሚውለው ብድር ግን ምንም ዓይነት ገደብ እንደማይኖበት እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የ15 በመቶ የብር ምንዛሪ ለውጡንና የተቀማጭ ገንዘብ ወለድ መጠን አስመልክቶም ለባንኮቹ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ የገቢ  ዕቃዎች ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ከሚያራምዱ አገሮች አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህ በመሆኑም አሁን የተደረገው የምንዛሪ ለውጥ ጫና መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ጫናውን መቀነስ ይቻላል ያሉት ባለሙያዎቹ፣ አብዛኛው የገቢ ንግድ በባንኮች በተፈጠረው የውጭ ገንዘቦች አቅርቦት እጥረት ምክንያት፣ ለግብይት ሲቀርብ የነበረው ገንዘብ ከጥቁር ገበያ እየተገዛ ነው፡፡ ከጥቁር ገበያ ሲገዛ የነበረው ገንዘብ፣ ከመደበኛው የባንኮች ምንዛሪ ጋር ሲነፃፀር የአሁኑን ጭማሪ ያህል ልዩነት ነበረው፡፡ ስለዚህም ይህ የጥቁር ገበያው ልዩነት የአስመጪው የትርፍ ህዳግ ውስጥ ሲንጸባረቅ እንደቆየ ይታወቃል ያሉት ተንታኞቹ፣ አበዳሪ ተቋማት ወደፊት ከወጪ ንግዱ በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ልክ የባንክ መተማመኛ ሰነድ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) በተገቢው መጠን በመፍቀድና የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ ገበያው እንዲረጋጋ የማድረግ ዕርምጃ መውሰድ መፍትሔ እንደሚሆን ያብራራሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች