በቻይና ከሚገኙ ግዛቶችና ከተሞች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ጎሳዎች በሚኖሩበት የዩናን ግዛት ውስጥ የምትገኘው ሊጂያግ ከተማ አብዛኛው ገጽታዋ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ተቀራራቢነት አለው፡፡ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ፣ የአየር ንብረት ሁኔታዋ በአብዛኛው ደጋና ወይናደጋዊ በመሆኑ አብዛኛው ጊዜ ዝናብ አያጣትም፡፡
ይህች ጥንታዊት ከተማ ዕድሜዋ ከ1,000 ዓመታት በላይ እንደሆነ ይነገርላታል፣ አሁንም ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ከ800 በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ድልድዮች በከተማዋ ጥንታዊው ክፍል ይታያሉ፡፡ ዩኔስኮ በቅርስነት የመዘገባት ሊጂያግ ከተማ፣ ብቸኛው መተዳደሪያዋ ቱሪዝም ነው፡፡ ያውም በአብዛኛው ከሌሎች ግዛቶችና ከተሞች በብዛት እየተመሙ በሚያጨናንቋት ቻይናውያን በብዛት ትጎበኛለች፡፡ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች በሊጂያንግ ከፍተኛውን ድርሻ ቢወስዱም፣ ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ግን የውጭ ጎብኝዎቿ ቁጥር እንደጨመረ መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡
ከ20 ዓመታት በፊት በቻይና ድንበር አዋሳኝ አካባቢ ከሚገኙ ከተሞች ውስጥ እያንቀላፋች የቆየች ከተማ በማለት ብዙዎች የሚገልጿት ሊጂያንግ ከተማ በአሁኑ ወቅት እስከ 20 ሚሊዮን የሚገመቱ ቱሪስቶች የሚጎበኟት፣ በዓመት ከ38 እስከ 50 ቢሊዮን ሬሚንቢ ወይም ከ11 ቢሊዮን እስከ 14 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ በማግኘት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢዋ ውስጥ ከ70 በመቶውን የሚሸፍን ድርሻ የሚይዘውን ይህን ገቢ ከቱሪዝም በማግኘት ትተዳደራለች፡፡
የናሺ፣ የሲኖ ቲቤትና የሌሎችም አነስተኛ ጎሳዎች መኖሪያዋ ሊጂያንግ፣ ተፈጥሮ የሰጠቻትን ገጽታ በአግባቡ በመንከባከብና በመጠበቅ፣ ባህሏ፣ የነዋሪዎቿ ጥንታዊው የኑሮ ዘይቤና ሌላውም ታክሎበት ለቱሪስቶች ተመራጭ ከሚያደጓት መካከል ከባህር ጠለል በላይ በ3,100 ሜትር ከፍታ ላይ በሚገኘውና ድራገን ስኖው ማውንቴን በተሰኘው ተራራ ሥር፣ የሚታየው ቴአትር አንዱ ነው፡፡ የሰማያዊ ጨረቃ ሸለቆ ወይም ብሉ ሙን ቫሊ በተሰኘው በዚህ ከፍታ ቦታ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የከተማ ወጣቶች የሚርመሰመሱበት፣ የከተማዋን ቀደምት ገዥዎች የፍቅር ታሪክ፣ የሕዝቡን የኑሮ ከፍታ ውድቀት አዛምደው በድራማ መልክ እየተረኩ፣ ፈረስ እየጋለቡ፣ ቅርጫት ተሸክመው ሽቅብ ቁልቁል እየባዘኑ፣ በመጠጥ እየናወዙ ሲንገላወዱ የሚታዩ አርቲስቶች የሚተርኩት የሁለት ሰዓት የአፈ ታሪክ ቴአትር የሚቀርበው ከአለት በተቦረቦረ የተራራ መድረክ ላይ ሲሆን፣ ታዳሚው ደግሞ በአምፊ ቴአትር መልክ በግማሽ ክብ ቅርፅ በተዘጋጀው መመልከቻ ቦታ ላይ ከመድረኩ የሚካሄደውን ይከታተላል፡፡ ዝናብ በሚመጣበት ወቅትም ቴአትሩን አቋርጦ መሄድ አይቻልም፡፡ ይልቁንም የዝናብ ልብስ ለብሶ መታደም እንጂ፡፡ ፈረሶችና ፈረሰኞች፣ በጥንታዊቷ እንጨት ሠራሽ ከተማ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ይላሉ፡፡ የፈረስ ጋሪዎች ለቱሪስቶች የመጓጓዣ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡
ከባህላዊው የአኗኗር ዘዴያቸው ባሻገር በዘመናዊ ረገድም የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻዎችና መዝናኛዎች አስፋፍተዋል፡፡ ከ3,100 ሜትር ከፍታ ላይ ከሚገኘው የበረዶ ተራራ ቁልቁልና ሽቅብ የሚሉ፣ የኬብል መጓጓዣዎች፣ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ባለ 18 ጉድጓድ ጎልፍ፣ በከተማዋ የግብይት ቦታዎች፣ በየካፊቴሪያውና ሬስቶራንቱ ወጣቶች ጊታር እየተጫወቱ የሚያዜሟቸው ቻይንኛ ዘፈኖች የታጀበ መስተንግዶ ለቱሪስቶች ይቀርባል፡፡
ከቻይናዋ ርዕሰ ከተማ ቤጂንግ እስከ 2,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሊጂያንግ ከተማ በቻይና የወቅቱ የኢኮኖሚ መለኪያ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የምትገኝ፣ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱት ነዋሪዎቿ ድሆች ስለመሆናቸው የሚናገሩባት ከተማ ነች፡፡
በሊጂያንግ ግብርናም ኢንዱስትሪም ያን ያህል ቦታ እንደሌላቸው ቢነገርም፣ በማዕድን የበለፀገች ስለመሆኗ ቲቤታውያኑ አስጎብኚዎች ሊነግሩዎት ይችላሉ፡፡ በጥንት ዘመን የሻይ ቅጠል ንግድ መናኸሪያና መተላለፊያ እንደነበረች የሚነገርላት፣ ከእስያ ወደ አውሮፓና አፍሪካ የሚያሳብሩ ቀደምት ነጋዴዎች እንደሚያዘወትሯት ታሪኳን የሚተርኩት አስጎብኚዎች፣ በከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ልዩ ሥፍራ ስለሚሰጠው ስለ ብር ማዕድን አብሯቸው ለሚጓዘው ጎብኚ እግረ መንገዳቸውን ሲያወሩ ሊያዳምጡ ይችላሉ፡፡
ብር ከወርቅም ይልቅ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ በየመደብሩ፣ በየገበያው በልዩ ልዩ ቅርፅና ዓይነት ይጌጣል፡፡ ከጣት ቀለበት እስከ ምግብ ማብሰያ፣ ምግብ መመገቢያ ሳህን፣ እንዲሁም የቻይኖች ባህላዊ መመገቢያ (ቾፕስቲክ)፣ እጅ መታጠቢያ፣ ወዘተ ከብር ይሠራል፡፡ ብር የንፁህነት ማሳያ፣ የጤነኛነት መፈተሻ ተደርጎ ይገለጻል፡፡ የአንገት ሀብት፣ አምባርና አልቦ ተደርጎ የሚበጀው ብር፣ ንፅህናና ጤናን ጠቋሚ እንደሆነ ሲያብራሩም፣ እንደ ጌጥ የተደረገው ብር ከጠቆረ ጌጡን የተጌጠው ሰው የጤና ችግር እንዳለበት በሊጂያን ነዋሪዎች ዘንድ ይታመናል፡፡
አፈ ታሪክ፣ ከጥንታዊ ቅርስ፣ ባህላዊ የአኗኗር ዘይቤ፣ ከዘመናዊው የተሰናሰሉባት የሊጂያንግ ከተማ፣ ለቱሪስቶች የምታቀርባቸው አገልግሎቶች እንደ ኢትዮጵያ ላሉ፣ የቱሪዝም ሀብታቸው በርካታ ሆኖ ሳለ ጥቂት በጥቂቱ እየተጠቀሙ ለሚገኙ አገሮች የሚያሰምሩት ቁም ነገር አላቸው፡፡ የከተማዋ ጎብኝዎች አስገራሚ መስህብ የተባሉትን ተፈጥሯዊ ገጽታዎች በመጎብኘት ላይ የተመሠረተ ቆይታ ያደርጋሉ፡፡ ከተራራ፣ ከወንዝና ከሌሎች መልክዓ ምድራዊ ገጽታዎች ባሻገር፣ ለጉብኝት የሚጋብዙ ጥቂት መስህቦች ያሏት ትንሿ ሊጂያንግ፣ ፈርጀ ብዙ የተፈጥሮ፣ የባህል፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች፣ የዱር እንስሳትና የሌሎችም መስህቦች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የማታገኘውን የቱሪዝም ገቢ ታስገኛለች፡፡ ትልልቅ አገሮች የማያጋብሱት ቢሊዮን ዶላር ሊጂያንግ የምታገኘው አብዛኛው ቻይናዊ ከሚጎበኘው ውጪ ጥቂት የውጭ ጎበኚዎችን በማስተናዱ መሆኑ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጥንታዊ አገሮች ካላቸው የቱሪዝምና የባህል ሀብት ምን ያህል እንዳልተጠቀሙ፣ እየተጠቀሙም እንዳልሆኑ የሚያሳብቅ ነው፡፡
በጠቅላላው ከተማዋ ያላትን ሀብት ለቱሪስቶች በሚመች መንገድ በማልማት መንገድና፣ መብራት፣ ቁልቁል ሽቅብ የሚወጡና የሚወርዱት ዘመናዊ መጓጓዣዎችን፣ ቴሌኮም፣ ሆቴልና ሌላውንም መሠረተ ልማት አሟልታ አቅርባለች፡፡ በቻይና ትልልቅ የቱሪዝም መዳረሻ ከሆኑ ከተሞችም አንዷ ለመሆን ችላለች፡፡ ተፈጥሯዊ መስህብን ከተላበሰውና ኩልል ያለ ሰማያዊ ውኃ ከተሞላው የጃድ ወንዝ፣ የበረዷማው ተራራ፣ እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከሚያቀርቡት ኅብረ ትርዒታዊ ቴአትር በቀር ይህ ነው የሚባል የቱሪስት መስህብ በማይታይባት ከተማ ውስጥ ሕዝብ እንደ ንብ ይተማል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቱሪዝምን በሚገባ ገንብተው አቅርበዋልና ነው፡፡ መኖሪያና መተዳደሪያቸውም ይኼው ብቻ ስለሆነም ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ከፍተኛ ክብካቤ የተደረገበት፣ ተገቢውን ትውውቅ ያገኘ ዘርፍ ከመገንባታቸውም በተጨማሪ፣ ሆድ የሚገባ መስተንግዶ የተመላበት መላ አገልግሎታቸው ቢሊዮን ዶላሮችን ለማጋበስ አስችሏቸዋል፡፡ ለአካባቢ የሚሰጡት ትኩረትም አጀብ የሚያሰኝ ነው፡፡