Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ያጣ የነጣው የስኳር ፈላጊ ድምፅ!

 ዛሬም ስለስኳር እጥረት ልናወራ ነው፡፡ የስኳር ገበያ መላ ቅጡን እያጣ ነው፡፡ የመፍትሔ ያለ ያልተባለበት ጊዜ ግን የለም፡፡ ዛሬም ችግሩ ብሶበታልና የመፍትሔ ያለ የሚል ድምፅ ማሰማት ተገቢ ነው፡፡ ስኳር የተረጋጋ ገበያ ኖሮት ሸማቹ ያለ አቅርቦትና ያለ ዋጋ ችግር የተገበያየበትን ወቅት ማሰብ ከባድ እየሆነ ነው፡፡

ዛሬ ከድህነት ወለል በታች ይኖራል ከሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል ጀምሮ እንደልብ ገንዘብ በሚመነዝሩት ሰዎች ቤት ውስጥ ሳይቀር ስኳር በብርቱ ይፈለጋል፡፡ ግን አይገኝም፡፡ ከ60 ዓመታት በፊት እባካችሁ ተላመዱ ተብሎ በሽልማት ማበረታቻ ጭምር ሲታደል እንደነበር የሚወራለት ስኳር፣ ዛሬ ብርቅ ሆኗል፡፡ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል መሠረታዊ ፍላጎት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

ተፈላጊው በጠፋ ቁጥር ፈላጊው እየበዛ፣ በየዓመቱ የአገሪቱ ፍጆታ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ደሃውም ሀብታሙም ስኳር በሚያሳድድበት በዚህ ወቅት፣ አጠቃላይ ግብይቱ ፍላጎቱን በሚመጥን አኳኋን አምርቶ በአግባቡ ለኅብረተሰቡ ማዳረስ አልተቻለም፡፡ የስኳር አስፈላጊነት ታምኖበት መሠረታዊ ሸቀጥ መሆኑ ከታወጀ ቀይቷል፡፡ ይህ በመሆኑም አጠቃላይ ግብይቱ በመንግሥት በኩል እንዲሆን የተፈለገበት ምክንያት በየቤቱ የሚፈለግ በመሆኑ ብቻም ሳይሆን፣ ግብይቱን መስመር ለማስያዝ ጭምር ታስቦ ነው፡፡

የስኳር ምርትን በሽበሽ ለማድረግ እንዲሁም ከአገር አልፎ ባህር ማዶ በመላክ የዶላር ጥማታችንን ለማስታገስ ያግዛል ተብሎ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ተመድቦ ከአሥር ያላነሱ የስኳር ፋብሪካዎች እዚህም እዚያም እንዲቆሙ ለማድረግ ሩጫ የተጀመረው፣ የአገሪቱ የስኳር ፍጆታ በመጨመሩ ነው፡፡ ነገር ግን የታሰቡት ግንባታዎች በታሰበው ጊዜ ከመጠናቀቅ ይልቅ ጉዟቸው የኤሊ ሆኗል፡፡ በምርት ያንበሸብሹናል የተባሉት ፋብሪካዎች በአስፈጻሚና በፈጻሚ አቅም ዕጦት ከጅምር ሥራ ብዙም ፈቅ አላሉም፡፡ ተጠናቀቁ የተባሉት ግንባታዎችም ቢሆኑ አሁንም ድረስ መቋጫ ሳያገኙ፣ ምርት ሳይጀምሩ በመንገታገት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለአገሬው የሚሆነውን ፍላጎት መሸፈን ስላልተቻለም ከውጭ በገፍ እየገዙ ማስገባት ግድ ሆኗል፡፡ እንኳንስ ለውጭ ገበያ ከአገር ውስጥ ፍጆታ የታሰበውን ምርት በአገር ውስጥ ማግኘት ጭንቅ ሆኗል፡፡

ከውጭ የሚገባውንና ከአገር ውስጥ የሚገኘውን ምርት አዳምሮ ያለ ችግር ለኅብረተሰቡ በማቅረብ የአቅርቦት ውጥረትን ለመፍታት መንግሥት ቃል ገብቶ ሳለ፣ በየጊዜው ግን እንከን እየተፈጠረ ሰበብ ከማቅረብ በቀር ችግሩ ሲፈታ ማየት ዘበት ሆኗል፡፡፡ በቂ የስኳር ምርት አለ እየተባለ ይለፈፋል፡፡ ገበያው ግን ጭንቅ ጥብብ ሲለው ይታያል፡፡

እጥረቱ ከዚህ በኋላ አይከሰትም እየተባለ ይደሰኮራል፡፡ ከዚህ በኃላ እንዲህ ዓይነት ችግር አይፈጠርም እየተባለ በተስፋ የተሞላ ፉከራ ይደመጣል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ስኳር ሊያመጣ ቀርቶ ዝብርቅርቅ የስኳር ገበያ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ የሰሞኑ የስኳር እጥረትም ከዚህ ቀደም መፍትሔ ሳይበጅለት በመቅረቱ ወይም እሳት የማጥፋት ሥራ ብቻ ሲሠራ እንደተከረመ ያሳብቃል፡፡ ለዘላቂ መፍትሔው በአግባቡ እንዳልታሰበ ይናገራል፡፡ ተጠቃሚዎችን ያንገሸገሸው ደግሞ የለም እየተባለ መጉላላት የሚፈጠርበት ስኳር በጥቁር ገበያው ውስጥ በውድ ዋጋ ሲቸበቸብ መታየቱ ነው፡፡ መንግሥት በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ለነዋሪዎች አዳርሳለሁ በሚልበት ከተማ ውስጥ፣ ስኳር የሚሸጠው በደላላ ጭምር እየታገዘ በኪሎ 40 እና 50 ብር ድረስ ነው፡፡ በመሠረቱ ስኳር የሚሸጥበት የተደነገገ ዋጋ በኪሎ 16 ብር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም መንግሥት መቋቋም ወዳልቻው አስከፊ አዝማሚያ እያመራን መሆናችንን ያሳየ አጋጣሚ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ከውጭ ከሚገባው ስኳር ጀምሮ በአገር ውስጥ የሚመረተውም ተጨምሮበት፣ በየመጋዘኑ በኩል እንዲሠራጭ የሚደረገው በመንግሥት መዋቅር በኩል ሆኖ ሳለ፣ ያውም እግር በእግር በሚቆጣጠራቸው የቀበሌና የክፍለ ከተማ ተቋማት በኩል ከሆነ፣ የገበያ ቀውሱ እንደምን ሊፈጠር ቻለ? እንግዲህ የስኳር ሙስና የጣፈጣቸው በዝተዋል አሊያም ሆን ተብሎ የሚፈጸም የገበያ ጡዘት አለ ለማለት ያነሳሳል፡፡ ለዘብተኛ ምክንያታዊነትን እንከተል ከተባለ ግን አገሪቱ የምትገኝበት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያሳደረው ጫናም የችግሩ አንዱ መገለጫ ሊሆን ይችላል፡፡

ይህ ይባል እንጂ የሸማቾች ማኅበራት በኮታ የሚሰጣቸውን ስኳር እንዲቸረችሩ ኃላፊነት ተሰጧቸው ሳለ ስኳር አልቋል በማለት ሸማቹን ከበር ይመልሳሉ፡፡ ነገር ግን ከገበያ ዋጋ በላይ በየመንደሩና በየገበያው የሚሸጠው ስኳር ከየት መጣ? ምንጩ ከወዴት ነው? ለሚለው ጥያቄ በቂ መልስ ማቅረብ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ከሸማቹ በተጨማሪ ስኳርን እንደ ግብዓት የሚጠቀሙ  የለስላሳ መጠጥ አምራቾች  በኮታ የሚደርሳቸው ስኳር አቅርቦቱ ተቋርጦ የምርት ሒደታቸው ሲስተጓጎል እየታየ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ከአቅርቦት እጥረቱ ባሻገር ግብይቱንና ሥርጭቱን በአግባቡ ባለመምራት ምክንያትም የተፈጠረ ችግር ነው፡፡

ስኳር መንግሥት ያቀርብላቸዋል የተባሉት ፋብሪካዎች ሥራ ለማቆም እየተገደዱ፣ ማምረት ከሚጠበቅባቸው በታች ለማምረት ሲገደዱ፣ ጉዳቱ ለመንግሥትም ይተርፋል፡፡ ይኸው እየታወቀ ግን ለዓመታት የዘለቀውን ችግር ሊፈታ ባለመቻሉ ተደራራቢ ኪሳራ ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ የለስላሳ መጠጦችን የፕላስቲክ ማሸጊያዎችን የሚያቀርቡ አምራቾች፣ የለስላሳ መጠጦች ባለመመረታቸው ምክንያት ማሸጊያዎችን አምርተው ማቅረብ ያልቻሉት የስኳር እጥረት በፈጠረው ችግር መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ ሰሞኑን የፕላስቲክ ማሸጊያዎችን አምርተው የሚገዛቸው በመጥፋቱ ለማከማቸት የተገደዱ አምራቾች እንዳሉ ታይቷል፡፡ ስኳር እስኪገኝ በማለት እጃቸውን አጣጥፈው የተቀመጡት የለስላሳ መጠጥ ፋብሪካዎች ጉዳይ መዘዙ እየበዛ መምጣቱን ያሳያል፡፡

የእነዚህ ፋብሪካዎች ሥራ ማቆም ፋብሪካዎቹን ብቻ ሳይሆን ምርቶቻቸውን ተቀብለው በሚያከፋፍሉና በሚቸረችሩ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ጭምር ችግር እየፈጠረ የሠርቶ አዳሪዎችን ገቢ እያሳጣ ይገኛል፡፡ ከዚህም በላይ ግን እጥረት በተፈጠረ ቁጥር ደንታ ቢስ ነጋዴዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው ላልተገባ ብዝበዛ ቢላቸውን እየሞረዱ የዋጋ ቁልል እንዲከምሩ በማድረግም፣ ግብይቱን ሲነቀንቁ መክረማቸውን የሚገታ መንግሥት አለመታየቱ ያስተዛዝባል፡፡ የስኳሩ ነገር መፍትሔ ይፈለግለት የሚለው ድምፅ ማስተጋባቱን ቀጥሏል፡፡     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት