Monday, April 15, 2024

የፌዴራል መንግሥቱ ፈተናዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹እኛ አጥብበን በመንደር ታጥረን የምናስብ ሰዎች አይደለንም፡፡ ለመላው የአገራችን ሕዝቦች ብልጽግናና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የምናስብ ሰዎች ነን፡፡ የአገራችንን ዕድገት ለማፋጠን የእኛ ሚና ወሳኝ እንደሆነ በአግባቡ እንገነዘባለን፡፡ ከጥልቅ ተሃድሶው መጀመር ወዲህ ከመሬት፣ ከማዕድን፣ ከኮንትሮባንድና ከመሳሰሉት ጉዳዮች ጋር ተያይዘው በሚስተዋሉ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት ላይ ዕርምጃ መውሰድ ጀምረናል፡፡ በኪራይ ሰብሳቢነት ተሰማርተው ያላግባብ ሲዘርፉ የነበሩ ግለሰቦች በክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና በክልሉ ሕዝብ ላይ የተቀነባበረ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፍተዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉት የክልሉ መንግሥት ትናንሽ ዕርምጃዎችን መውሰድ ስለጀመረ ነው፡፡ ገና ወደ ወሳኙ ምዕራፍ አልገባንም፡፡ ዕርምጃ መውሰድ በመጀመራችን የክልሉን አመራር እንደ ጠባብ ብሔርተኛ፣ የአገራችንን ብሔር ብሔረሰቦች እንደ ጠላት የሚያይ፣ በአጎራባች ክልል የሚኖሩ ወንድሞቻችንን ለማጥፋት የተነሳን ጠብ አጫሪ አስመስለው እኛን ለማቅረብ ላይ ታች እያሉ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብም በአገራችን ሕዝቦች ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታይና እንዲጠላ፣ ለዚህች አገር አንድነት የማይጨነቅ አስመስለው ፕሮፓጋንዳ እየነዙ ነው፡፡ እኛ እንደዚህ ዓይነት ህልም ፈጽሞ የለንም፡፡ ሕዝቦችን ለመለያየት፣ የሕዝቦች አብሮነትን ለማሰናከል ፈጽሞ አስበን አናውቅም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በአብሮነት መኖር ዛሬ የሚጀምር ሕዝብ አይደለም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ከማንም ጋር መኖር የሚያውቅ ሕዝብ ነው፡፡ በዚህች አገር ለዘመናት የቆየውን የሕዝቦች አብሮነትና አንድነት እንዲናጋ የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ የክልሉ መንግሥት በፍጹም አይፈልጉትም፡፡ እኛ የምንለፋው ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አንድነት ነው፡፡ አንድነት ብቻ ሳይሆን እኩልነት እንዲሰፍን፣ ለስም አብሮ መኖር ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ነው፡፡ አንዱ ጠግቦ እየበላ ሌላው እየተራበ፣ አንዱ አግኝቶ ሌላው እንዲያጣ፣ አንዱ በልፅጎ ሌላው ደህይቶ የምንኖርበት አገር እንዲኖር አንፈልግም፡፡››     

ይህ ንግግር መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ከኦሮሚያ ክልል ሁሉም ዞኖች የተውጣጡ አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች በተሳተፉበት የሰላም ኮንፈረንስ ላይ፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ ነው፡፡ አቶ ለማ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ እየተፈጠረ ያለው የአንድነትና የመተባበር መንፈስ የአገራችን ኢትዮጵያን አንድነት ያጠናክራል፡፡ ከጥልቅ ተሃድሶው መጀመር ወዲህ የክልሉ መንግሥት ወደ ሕዝብ መመለስ፣ የሕዝቡን ችግር አድምጦ መፍትሔ መስጠት፣ ሕዝቡ የሚፈልገውን መሥራት መጀመሩ ጠቀሜታው ለኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን ለአገራችንም ጭምር እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ …. እንደ ክልልም ሆነ እንደ አገር አመራር ላይ ያለን ሰዎች የሕዝቡን ቃልና ፍላጎት ቸል ብለን ለመሄድ የምንሞክር ከሆነ አንድም ቀን ማደር እንደማንችል ሕዝባችን በግልጽ እየነገረን ነው….›› ሲሉም አክለዋል፡፡

አቶ ለማ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ይህን መሰል ስሜት ቀስቃሽና ሸንቋጭ የሆኑ በተለያዩ መድረኮች ያደረጓቸው ንግግሮችና የወሰዷቸው ዕርምጃዎች በብዙ የአገሪቱ ዜጎች በተለይም ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በሰፊው ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ ይሁንና የአቶ ለማ አመጣጥ ጊዜን፣ ያልተለመደ የአመራር ዘይቤና ለ26 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየውና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት ላይ በብቸኝነት ሲወስን ከነበረው ኢሕአዴግ ባህልና አሠራር ጋር በከፊል አብረው የማይሄዱ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ልሂቃን በእሳቸው ዙሪያ በዋነኛነት ለሁለት ተከፍለዋል፡፡

ለጥቂቶች አቶ ለማ ኢሕአዴግን ከገባበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ለማውጣትና ኦሕዴድ ያጣውን ሕዝባዊ ተቀባይነት ለመመለስ ማዕከላዊው መንግሥት የሰጣቸውን የረጅም ጊዜ የቤት ሥራ በአግባቡ እየተወጡ ያሉ ጥሩ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ ለብዙዎች ግን በወረቀት ተገድቦ የነበረውን የፌዴራል ሥርዓት ከነተግዳሮቶቹና ከነተስፋዎቹ ወደ ተግባር ለማምጣት እየተጣጣሩ ነው፡፡ ይህ ንቅናቄም በአንዳንድ በፌዴራሉና በክልሉ መንግሥታት መዋቅር ውስጥ በሚገኙና የግል ዘርፉን ጨምሮ በውጫዊ አካላትና ግለሰቦች ጥርስ እንዲነከስባቸው እንዳደረገም በሰፊው ሲነገር ሰንብቷል፡፡

አቶ ለማ ይህን ንግግር ካደረጉ ከጥቂት ቀናት በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን መስከረም 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በማግሥቱ መስከረም 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ግን ራሳቸው አቶ አባዱላ ጉዳዩን ለአገር ውስጥ ሚዲያዎች ይፋ ሲያደርጉ፣ ‹‹አሁን በደረስኩበት ደረጃ በዚህ ኃላፊነት ለመቀጠል የማያስችሉኝ ሁኔታዎች ስላሉና ፍላጎቱም ስለሌለኝ፣ ለመልቀቅ ድርጅቴንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጠይቄያለሁ፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አባዱላን ‹‹ለመቀጠል የማያስችሉኝ ሁኔታዎች›› ምን እንደሆኑ እስካሁን ለሕዝብ በይፋ አልተገለጸም፡፡ ይሁንና ከወቅታዊው የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በማያያዝ አስተያየት ሰጪዎች የተለያዩ መላምቶች መስጠታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ጎልቶ የወጣው የፌዴራሉ መንግሥት በኦሮሚያ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ አስመልክቶ የያዘው አቋምና የኦሮሚያ ክልል በቅርቡ ከሶማሌ ክልል ጋር በነበረው ግጭት የፌዴራሉ መንግሥት በሰጠው ውሳኔ ላይ አቶ አባዱላ ደስተኛ አለመሆናቸው ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መሆናቸውን ባወጁ አገሮች እንደ አቶ አባዱላ ያሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መልቀቃቸው የተለመደ የፖለቲካ ተግባር ስለሆነ ብዙ የሚወራለት ጉዳይ አይደለም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የአቶ አባዱላ መልቀቅ ለአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት አዲስ ምዕራፍ ከመክፈት እስከ ፌዴሬሽኑ መፍረስ የዘለቁ በርካታ ትርጉሞች እየተሰጡት ግለቱ ሳይበርድ ዜጎችን ማከራከሩን ቀጥሏል፡፡

የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መሥራችና የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው ግን የመንግሥት ግልጽ አለመሆን እነዚህን መላምቶች እንደጋበዘ ይተቻሉ፡፡ ‹‹የሥርዓቱ ባህሪ ግልጽ አይደለም፡፡ በሌላ አገር ቢሆን አንድ አፈ ጉባዔ ሥልጣን ቢለቅ ጋዜጠኞቹ በትክክል የለቀቀበትን ምክንያት እስካሁን አያቆዩትም፡፡ አሁን አቶ አባዱላ የለቀቁት በፖለቲካ ጥያቄ ይሁን በሙስና ምክንያት አናውቅም፡፡ የሚለቁት በራሳቸው በጎ ፈቃድ ነው ወይስ ከጀርባ ባለ ግዳጅ ነው? የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ለተለያዩ መላምቶች በር የሚከፍተውም ይኼ ነው፡፡ ስለዚህ መልቀቃቸው ከፌዴራል ሥርዓቱ ጋር የሚገናኝ ስለመሆኑ ለመናገር ግልጽ መረጃ ስለሚያስፈልግ መጠበቅ ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡

የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ ጉዳዩ በዚህ መጠን ያነጋገረው ብሔር ተኮር ፖለቲካው ጤናማ ደረጃ ላይ የማይገኝ በመሆኑ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹የማንነትና የብሔር ፖለቲካው በጣም ስለጦዘ አቶ አባዱላ እንደ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን አልታዩም፡፡ አቶ አባዱላ ኦሮሞ መሆናቸው ላይ ነው ትኩረት የተደረገው፡፡ አንዱ የፌዴሬሽኑ ችግር ይኼ ነው፡፡ ጉዳዩ የፓርቲ ፖለቲካ ማሳያም አይደለም፡፡ ለኢሕአዴግ የፓርቲ ፖለቲካው በማንነት ፖለቲካው ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ጉዳዩ ከሚገባው በላይ እየተራገበ ያለው ከብሔር አንፃር ስለተቃኘ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከአቶ አባዱላ በላይ ሥልጣን የነበራቸው ፖለቲከኞች በፈቃዳቸው፣ ተገደው፣ ጡረታ በመውጣት የወጡ አሉ፡፡ በዚያ ላይ እሳቸው ፓርቲያቸው ውስጥና ፓርላማው ውስጥ እቆያለሁ ብለዋል፤›› ነው ያሉት፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የነበረው ግጭት መነሻ ምን እንደነበር፣ የደረሰው የጉዳት መጠን ምን ያህል እንደሆነ፣ ጥፋተኛ የተባሉ አካላት ላይ ምን ዓይነት ዕርምጃ እንደተወሰደ፣ እንዲሁም ግጭቱ ዳግም እንዳያገረሽ ለማድረግ ስለተሰጠው መፍትሔ በግልጽ የተነገረ ነገር የለም፡፡

ይሁንና የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ልዩነት ወደ አደባባይ መምጣቱ ከዚህ ቀደም ያልተለመደ ነው፡፡ የአማራና ትግራይ ክልሎች አመራሮች መሠረታዊ ልዩነት እንዳላቸው በሰፊው የተነገረ ቢሆንም፣ ቢያንስ በአደባባይ ሲጨቃጨቁና መግለጫ በማውጣት ሲወጋገዙ አልታዩም፡፡ በተለይ የሶማሌ ክልል አመራሮች የኦሮሚያ ክልል አመራሮችን በኦነግነት ሲፈርጁ መታየታቸው ፍጹም ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በዚህ አቋም እንዳዘኑም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሪፖርተር መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የአገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት እንደ አሀዳዊ መንግሥት የሚሠራና ከማዕከል የሚሰጡ ውሳኔዎች ከላይ ወደ ታች በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ አማካይነት ወጥ በሆነ መንገድ የሚተገበሩ በመሆናቸው፣ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ የክልሎችና የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብቶች ተግባራዊ አልሆኑም የሚል ቅሬታ ከተለያዩ አካላት ሲቀርብ ቆይቷል፡፡

ከዚህ አንፃር ልክም ሆኑ ስህተት ክልሎች በፌዴራል መንግሥቱ ውሳኔዎች ላይ ጥያቄዎች ማንሳት መጀመራቸው በጎ ጅምር መሆኑን የሚገልጹ አስተያየት ሰጭዎች አሉ፡፡ አቶ ሙሉጌታ ግን ማዕከሉ ወይም ፌዴራል መንግሥቱ በመዳከሙ ክልሎች እንዳሻቸው የመሆን አዝማሚያ እያሳዩ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ‹‹አሁን ባለንበት ሁኔታ የምንቀጥል ከሆነ ፌዴሬሽኑ ሊበታተን ይችላል፡፡ በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ካረፉ በኋላ የምናየው ማዕከሉ እየተዳከመና ክልሎች እየተጠናከሩ ሲመጡ ነው፡፡ ክልሎቹ እንደ ክልልነት ያላቸው ስሜት ፌዴሬሽኑን ወይም ማዕከሉን እስከ መርሳት እየደረሱ ነው የሚመስለኝ፡፡ ፌዴሬሽኑ ወይም ማዕከሉ ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ከዚያ በኋላ ሕገ መንግሥቱ የእውነት ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድ ላይ ከክልሎች ጋር መደራደር ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

አልፎ አልፎ የሚታየው የአንዳንድ ክልሎች እንቅስቃሴ አንድ ማኅበረሰብ መፍጠር የሚለውን የሕገ መንግሥቱን መርህ የሚቃረንና የአንድነት ገጽታውን ገሸሽ ያደረገ እንደሆነ አቶ ሙሉጌታ ይወቅሳሉ፡፡ ‹‹ለዚህ መንግሥትም አስተዋጽኦ ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ሰውነትንና ዜግነትን በመርሳት ሰዎች በማንነታቸው ላይ በጣም እንዲያተኩሩ ሲደረጉ ነው የነበረው፡፡ የዴሞክራሲ ግንባታ ሒደቱና ተቃዋሚዎች እየተዳከሙና መንግሥት እየጠነከረ ነው የመጣው፡፡ ዴሞክራሲው ገና ባልዳበረበት አገር የብሔርተኝነት ስሜቱ ግን በጣም እየተለጠጠና እየተጋጋለ ሄዷል፤›› ብለዋል፡፡

ክልሎች ሲጠይቁ ወይም ሳይጠይቁ የፌዴራል መንግሥቱ በቀጥታ ወደ ክልሎች መግባት የሚችልባቸው በሕገ መንግሥቱና በዝርዝር ሕጎች የተቀመጡ ሦስት መንገዶች እንዳሉ ያስታወሱት አቶ ሙሉጌታ፣ እነዚህን መንገዶች በመጠቀም ፌዴራል መንግሥቱ ግጭቱን ቶሎ ማቆም ይገባው እንደነበር ተከራክረዋል፡፡ ‹‹በክልሎችና በፌዴራል መንግሥቱ ግንኙነት ላይ ችግር የፈጠረው የአንድ ፓርቲ ሥርዓቱ ነው፡፡ ፌዴራሊዝም የመንግሥታት ግንኙነት ሆኖ እያለ በተግባር ግን የፓርቲ ፌዴራሊዝም ሆነ፡፡ ፓርቲው መጀመርያ አካባቢ በጣም ጠንካራ ስለነበር፣ በአራቱ አባላት መካከል የነበረው ግንኙነትም ጠንካራ ስለነበር ችግሩ አይታይም ነበር፡፡ የክልሎች ሕገ መንግሥቶች ከፌዴራሉ ሕገ መንግሥት የተገለበጡ ናቸው፡፡ ክልሎች በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ሥልጣን ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም፡፡ የወንጀል ሕግ እንኳን ማውጣት አልቻሉም፡፡ አሀዳዊ መንግሥት እስኪባል ድረስ ማዕከሉ እስከ 2004 ድረስ በጣም ኃይለኛ ነበር፡፡ አቶ መለስን የሚተካ ሰው ሲጠፋ እርስ በርስ ሁሉ መጨቃጨቅ  ጀመሩ፡፡ ይህን ጎንደር ላይ በብአዴንና በሕወሓት መካከል አይተናል፡፡ ማዕከሉ እየተዳከመ ሲመጣ ክልሎች እያፈነገጡ መምጣት ጀምረዋል፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

አቶ ልደቱ ግን የክልል ገዥ ፓርቲዎች ይፋዊ በሆነ መንገድ የፌዴራል መንግሥቱን ውሳኔዎች ሲቃወሙ ወይም በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ ሥልጣኖቻቸውን ተግባራዊ ለማድረግ አዲስ መስመር ሲከተሉ እንዳልተመለከቱ ይገልጻሉ፡፡ ይልቁንም የተለየ ጥያቄ እያቀረበ ያለው በክልሎቹ የሚኖረው ኅብረተሰብ ነው፡፡ ‹‹ክልሎቹን እንደ ክልላዊ መንግሥትና በዙሪያቸው ያለውን ኅብረተሰብ ለይቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ይፋዊ በሆነ መንገድ ክልሎቹ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን መብታቸውንና ነፃነታቸውን ሲያስጠብቁ አይታዩም፡፡ ጥያቄውና ጫናው የሚመጣው ከኅብረተሰቡ ነው፡፡ የክልል ገዥ ፓርቲዎች የኢሕአዴግ አባል አልያም አጋር በመሆናቸው ብዙውን ጊዜ ገዥው ግንባር ከሚለው ውጭ አይወጡም፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ግጭት የክልሉ ባለሥልጣናት ተሳትፈዋል በሚል በመንግሥት ሲነገር ተሰምቷል፡፡ ነገር ግን ይኼ በይፋ አልተገለጸም፡፡ ከክልል የሚነሱ ጥያቄዎች ሕጉና ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሠረት እየቀረቡ አይደለም፡፡ በአመፅና በግጭት ነው እየቀረቡ ያሉት፡፡ ክልሎቹም ጥያቄዎቹን የሚያስተናግዱበት መንገድ ግልጽነት የለውም፡፡ መንግሥት እየነገረን ስላልሆነ ዝርዝሩን በግልጽ ማወቅ አንችልም፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ለሁሉም መሬት ላይ ላሉ ችግሮች ሁሉ ሕገ መንግሥቱ መልሶታል በማለት መመለስ የማይሰለቻቸው ኢሕአዴጎች ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል የሚለውን ጥያቄ እንደ ጦር ይፈሩታል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው ብሔርን መሠረት ያደረገው የፌዴራል ሥርዓት በአገሪቱ ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ብዙዎች ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹የሙከራ ሕገ መንግሥት ብዬ ነው እኔ የምወስደው፤›› ያሉት አቶ ሙሉጌታ፣  ሕገ መንግሥቱ በተግባር እየተፈተነና ችግር እየፈጠረ፣ ብሔር ተኮር ገጽታው በጣም እያየለና ግጭቶች እየበዙ በመሆናቸው ሥርዓቱ በድጋሚ ሊጤን እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ ይሁንና ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ቀላል እንዳልሆነ ይቀበላሉ፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱን የጻፈውና ያጸደቀው ኢሕአዴግ ነው፡፡ ከኢሕአዴግ የፖለቲካ ጥቅም ጋር የተያያዘ ሕገ መንግሥት ነው ያለን፡፡ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል በጣም ከባድ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኢሕአዴግ በእኔ መቃብር ነው ሕገ መንግሥቱ የሚቀየረው ይል ነበር፡፡ ይህ የሚያሳይህ ሕገ መንግሥቱ ሰው ሠራሽና ሰዎችን የሚገዛ ሰነድ ሳይሆን የኢሕአዴግን ፍላጎት በአብዛኛው የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ነው፡፡ የተጋነነና መለኮታዊነት የተላበሰ ሁሉ ነው፡፡ ለዚህም ነው በ23 ዓመት ውስጥ አንድም ማሻሻያ ተደርጎበት የማያውቀው፤›› በማለትም አብራርተዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ጀምሮ ከጽንሰ ሐሳብ አንፃር ብሔር ተኮር የፌዴራል ሥርዓት ግጭት ያባብሳል የሚል ፍርኃት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሙሉጌታ፣ አሁን ግን ማንነትን መሠረት ያደረጉ በርካታ ግጭቶች እየተፈጠሩ በመሆኑ በትክክል ይኼ ይኼ መደረግ አለበት ለማለት ቢያዳግትም ሥርዓቱ እንደገና መመርመር፣ መጠናትና መፈተሽ እንደሚገባው የሚያስገድድ በቂ እውነታ እንዳለ ግን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የ2010 በጀት ዓመት የመክፈቻ ንግግራቸው፣ ‹‹እያበበ በመሄድ ላይ በሚገኘው የፌዴራል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን›› በማለት ሥርዓቱ ችግር ላይ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ባሳለፍነው ዓመት ያገኘናቸውን ጅምር ድሎችና መልካም ተሞክሮዎችን በምናሰፋበት፣ እንዲሁም አጋጥመውን የነበሩትን ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች በሚቀረፉበትና የሕዝባችን የላቀ ተጠቃሚነት በሚረጋገጥባቸው ጉዳዮች ላይ ግልጽና ሰፊ ምክክር ማድረግ  ይገባል፤›› ያሉት ዶ/ር ሙላቱ፣ ‹‹አዲሱን የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ከጀመርንም ጊዜ አንስቶ በነበሩት የመጀመርያዎቹ አሥር ዓመታት በአማካይ የ10.5 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ በዓለም ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ አገሮች ተርታ በግንባር ቀደም ሥፍራ ላይ እንገኛለን፡፡ የአዲሱን ሚሊኒየም ሁለተኛውን አሥር ዓመት በተመሳሳይ የዕድገት ፍጥነት ከቀጠልንም መካከለኛ ገቢ ያላት አገር እንደምትኖረን እርግጠኛ መሆን ይቻላል፤›› በማለት ከአገሪቱ ተግዳሮቶች ይልቅ ተስፋዎች ላይ ማተኮርን መርጠዋል፡፡

‹‹በ2009 ዓ.ም. የተሃድሶ እንቅስቃሴያችን ይበልጥ ጥልቀት እንዲኖረውና የሥርዓቱ አደጋ የሆነውን ያለውድድር የመጠቀም እንዲሁም የሙስና ዝንባሌና ተግባር ለመቆጣጠር በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ታውጆ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ የተደረገበት ዓመት ነበር፡፡ በሙስና ተግባር ላይ የተሰማሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተባባሪዎቻቸውን በሕግ እንዲጠየቁ ለማድረግ የተጀመረው ሥራም በ2010 ዓ.ም. በጥናት ላይ ተመሥርቶ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፤›› በማለትም መንግሥት ችግሮችን እንደተቆጣጠረ አመልክተዋል፡፡

ምክር ቤቱም የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲገነባ የሚያስችሉ አዋጆችንና ፖሊሲዎችን ያፀድቃል ተብሎ እንደሚገመትም አስታውቀዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ባለፈው ዓመት የምርጫ ሥርዓቱን በተመለከተ ሊደረግ የታሰበው ማሻሻያም ውይይት ሲካሄድበት መቆየቱንና ዘንድሮ ለምክር ቤት ቀርቦ በ2012 ዓ.ም. ለሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ እንዲደርስ እንደሚደረግም  ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ ለማድረግ በተጀመረው ውይይትና ድርድር ሁሉም ያገባኛል የሚሉ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ሁሌም በሩን ክፍት አድርጎ እንደሚሠራ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በዓመቱ የሚዲያ ሪፎርም ሥራ እንደሚከናወንም አስታውቀዋል፡፡

ዶ/ር ሙላቱ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ስለተፈጠረው ግጭት ሲናገሩም፣ ‹‹ከ2009 ዓ.ም. መጀመርያ ጀምሮ የተለያዩ ጥገኛ አስተሳሰቦች የወለዷቸው የፀረ ሰላም ኃይሎችም የተጠቀሙበት አለመረጋጋት በአገራችን ተፈጥሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል፡፡ የአገራችን ሰላምና ፀጥታ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ በመመለሱም አዋጁ እንዲነሳ ተደርጓል፡፡ ለግጭቶች ምክንያት የሆኑ ያልተፈቱ የድንበር ማካለል ጉዳዮችን ከሞላ ጎደል በሁሉም አካባቢ ለመፍታት የተቻለ ቢሆንም፣ አሁንም በኦሮሚያና በሶማሌ አካባቢ ቅሪት ያልተስተካከሉ አፍራሽ አመለካከቶች የወለዷቸው ግጭቶች ተከስተው የሰው ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ያለፈበትና ንብረቶች የወደሙበት ሁኔታ መኖሩ ይታወቃል፡፡ ይህ ሁኔታ በፍፁም መወገዝ ያለበትና መንግሥት ፀጥታውን ከማስከበር ባሻገር አጥፊዎችን ወደ ሕግ ለማቅረብ ሳይታክት እየሠራ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

በዶ/ር ሙላቱ ንግግር ከፍተኛ ሐዘን እንደተሰማቸው የተናገሩት አቶ ልደቱ፣ ‹‹ፕሬዚዳንቱ ከዚያ ሥጋት ውጪ ነን፣ የተፈጠረው ችግርም በፀረ ሰላም ኃይሎች የተፈጠረ ነው ብለው ችግሩን ውጫዊ በማድረግ ውስጣዊ እንዳልሆነ አድርገው ነው ያቀረቡት፡፡ በፕሬዚዳንቱ ንግግር በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ዋናው ቁልፍ ጥያቄ የሰላም ጉዳይ ነው፡፡ ከሰላም በላይ አሁን አሳሳቢ ነገር የለም፡፡ ብር ዲቫሉዌት የተደረገው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስለተፈጠረ ነው፡፡ ይኼ ከኢኮኖሚ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፡፡ ሰላም በመጥፋቱ ኢንቨስት የሚያደርጉ ሰዎች በሙሉ ልብ መሥራት አልቻሉም፡፡ ቱሪስቶችም በሙሉ ልብ መጥተው መጎብኘት አልቻሉም፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለዚህ ብዙም ትኩረት አልሰጡም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህ የሚያሳይህ ሥርዓቱ አሁንም ያን ችግር ተሻግሬዋለሁ ብሎ ተገቢ ያልሆነ በራስ መተማመን እንደፈጠረና በተለመደው መንገድ ለመቀጠል እየፈለገ እንደሆነ ነው፡፡ ሥርዓቱ ለውጥ ለማድረግ ዝግጁ አይደለም፤›› ያሉት አቶ ልደቱ፣ ቆም ብሎ ራስን መርምሮ ተጨባጭ የሆነ ለውጥ ለማድረግ ከዚህ በላይ አስጊ ሁኔታ በዚህ አገር መታየት እንደሌለበት ያሳስባሉ፡፡ ‹‹ከዚህ በላይ ምን እንደሚጠበቅ አይገባኝም፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘና ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀ ጀምሮ ብሔርና ቋንቋን መሠረት ያደረገው የፌዴራል አደረጃጀት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ስንገልጽ ነው የኖርነው፡፡ ግን በተግባር የታየ ነገር ስላልነበር እንደ አጉል ሥጋት ነበር ሲታይ የነበረው፡፡ አሁን ግን በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉት ግንኙነቶች ጤናማ ከመሆን ይልቅ ወደ መናቆርና ጥላቻ እያመሩ መሆኑን እያየን ነው፡፡ ስለዚህ ሥርዓቱ ችግር ውስጥ እንደሆነ በአፍ ከምንናገረው በላይ ሁኔታዎቹ በተግባር እያሳዩ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ብዙ ጊዜ ባለሥልጣናቱ ችግሩ ያለው የፌዴራል ሥርዓቱ ላይ አይደለም፣ አፈጻጸሙ ላይ ነው ይላሉ፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አንድ ፖሊሲ በአግባቡ ሊፈጸም የማይችል ከሆነ ዞሮ ዞሮ ችግሩ የፖሊሲ ነው፡፡ ፖሊሲ አፈጻጸምን ግንዛቤ ውስጥ ሊከት ይገባል፡፡ ሁለቱን ነጣጥሎ ማየት የሚቻል አይመስለኝም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በጥልቅ ተሃድሶ አማካይነት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ኢሕአዴግና መንግሥት ቃል በገቡት መሠረት ይህንኑ ለመፈጸም የተለያዩ ሥራዎችን ያከናወኑ ቢሆንም፣ ብዙዎች ለውጡን በተጨባጭ ማየት እንደተሳናቸው ይናገራሉ፡፡ አቶ ልደቱም ሆኑ አቶ ሙሉጌታ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ‹‹የተገባው ቃል ከልብ አልነበረም፡፡ የነበረውን ውጥረት ለማርገብ እንደ አንድ ቴክኒክ ነው መንግሥት የተጠቀመበት፤›› ያሉት አቶ ልደቱ፣ ‹‹የለውጥ እጦትም ይመስለኛል ችግሮቹን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያባባሰ ወደ ቀውስ ሊከተን የቻለው፡፡ ጊዜውን የጠበቀ ወቅታዊ ለውጥ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ግጭት ብዙም ቦታ አያገኝም ነበር፡፡ መንግሥት በአፈጻጸም ብቻ ሳይሆን በፖሊሲ ደረጃ የፌዴራል ሥርዓቱ ምን ችግር አለበት ብሎ በድፍረት ራሱን መገምገም አለበት፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጨምሮ ለችግሩ ወታደራዊ መፍትሔ ነው እንጂ የተሰጠው ተጨባጭ የሆነ የፖለቲካ መፍትሔ ሲሰጠው አላየንም፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ ነገሮች አሁን ያላቸው ገጽታ እጅግ አሳሳቢ ቢሆንም፣ መንግሥት ለችግሮቹ እየሰጠ ያለው ትኩረትና ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ከችግሮቹ ጋር የሚመጣጠን እንዳልሆነ ይተቻሉ፡፡ ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት መጀመር ያለበት ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ በመዋል መሆን እንዳለበትም ያሰምሩበታል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱን በተግባር ላይ ብናውለው ኖሮ ምናልባትም ከሚመጥነን በላይ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የማያሠራ ሆኖ አይደለም፡፡ በፓርቲና በአገር መካከል መኖር የሚገባው ልዩነት ስለሌለ የፖለቲካ ባሕላችን ሕገ መንግሥቱን የሚሸከም አልሆነም፡፡ ክልሎችን የሚያስተዳድሩ ፓርቲዎች ነፃነታቸው ተጠብቆ ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር መደራደር የሚችሉበት ሕይወት የላቸውም ወይም ኖሯቸው አያውቅም፡፡ አሁን ማዕከሉ እየተዳከመ ሲመጣ ክልሎች ፌዴራሊዝሙን በቁም ነገር መውሰድ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን ክልሎች ፌዴራሊዝሙ ላይ ተመሥርተው ውሳኔ መውሰድ የጀመሩት ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ አይደለም፡፡ የጋራ አመራሩና አንድነቱ ተዘንግቶ ትኩረቱ ሁሉ ልዩነቱ ላይ ሆኗል፣›› በማለትም ክልሎች ራሳቸው የችግሩ አካል የመሆን አዝማሚያ እንደታየባቸው አመልክተዋል፡፡

ለአቶ ሙሉጌታ ከሁሉም በላይ አሳሳቢው ጉዳይ የኢሕአዴግ የአመራር ብቃት እየወረደ መምጣት ነው፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ራሱ ለውጥ የሚያስፈልገው ችግር እንዳለ አምኗል፡፡ ለዚህም ነው ጥልቅ ተሃድሶ የሚል ሐሳብ ያመጣው፡፡ ከችግሩ ለመውጣት መጀመርያ ለውጥ እንዲያደርግ ለኢሕአዴግ ዕድል መስጠት አለብን ብዬ ተከራክሬ አውቃለሁ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ኢሕአዴግ ራሱ ቃል የገባውን እንኳን ለውጥ አላመጣም፡፡ ከአሁን በኋላም ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡ በአንድ በኩል ቀውሱ እያየለ ነው፡፡ በሌላ በኩል የኢሕአዴግ የአመራር ችሎታ እየቀነሰ ነው፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡  

     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -