የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከሦስት ዓመታት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ዛሬ ጥቅምት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠዋት ከዝዋይ እስር ቤት ተፈታ፡፡
የዛሬ ሦስት ዓመት ጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. የታሰረው ተመስገን የተከሰሰው ለአመጽ የሚያነሳሱ ጽሑፎችን በመጻፍና የባለሥልጣናትን ስም በማጥፋት ነበር፡፡ ተመስገን እስሩን የጨረሰው ከትናንት በስቲያ ጥቅምት 3 ቀን 2010 ቢሆንም ባልታወቀ ምክንያት ማረሚያ ቤቱ ታራሚውን ሊፈታው ፈቃደኛ አልነበረም፡፡
በዚህም የተነሳ ተመስገን የረሀብ አድማ ጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ጠዋት ላይ ግን እንዲፈታ ተደርጓል፡፡
የጋዜጠኛ ተመስገን ክስ የተጀመተው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከመሞታቸው በፊት ቢሆንም፣ እርሳቸው ሲሞቱ ክሱ ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ነበር፡፡ ሆኖም ዓቃቤ ሕግ ክሱን በድጋሚ አስነስቶት ነው ተመስገን የሦስት ዓመት እስር የተፈረደበት፡፡