Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በኢትዮጵያ የግብርና ኤክስቴንሽን መስክ ፈር ቀዳጁ ሳሳካዋ ግሎባል

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በጃፓናዊው ምግባረ ሰናይ ዮኢሺ ሳሳካዋ አማካይነት የተመሠረተው ሳሳካዋ አፍሪካ አሶሲዬሽን እንዲሁም በሥሩ የሚተዳደሩ ሳሳካዋ ግሎባል 2000 እየተባሉ በየአገሮቹ የሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በመመሥረት በአፍሪካ መንቀሳቀስ ከጀመረ 30 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ተቋሙ ወደ አፍሪካ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው በምሥራቅ አፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያና በሱዳን የተከሰተው ድርቅና ያስከተለው የረሀብ ቸነፈር እንደነበር ይጠቀሳል፡፡

  ለአፍሪካ የረሀብ ተጎጂዎች ለዕለት ደራሽ የሚውል ዕርዳታ ለመስጠት በመጡበት ወቅት አንደኛቸውን ዘላቂ ዕገዛ መስጠጥ የሚችሉበትን ሐሳብ እንደጠነሰሱ የሚነገርላቸው ሚ/ር ሳሳካዋ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ15 አገሮች ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ድጋፍ የሚሰጥ የበጎ አድራጎት ድርጅት አስፋፍተው መሥራት እንደጀመሩ ከታሪካቸው ይጠቀስላቸዋል፡፡

  በዚህ ወቅት ከታዋቂው የአረንጓዴ አብዮት ጠንሳሽ ኖርማን ቦርሎግ ጋር ሊገናኙ እንደቻሉና ከእኚሁ ምሁር ጋር ጥምረት በመፍጠር፣ በላቲን አሜሪካና በእስያ የተገኘውን የአረጓዴ አብዮት ውጤት በአፍሪካም ዕውን ለማድረግ መሥራት ጀምረው እንደነበርም በታሪካቸው ተመዝግቧል፡፡ ይሁንና በግብርናው መስክ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀም፣ የተለያዩ ግብዓቶችን በማካተት ብዙ ምርት ማፍራትና ውጤታማ መሆን የሚለው የአብዮቱ መርኅ ግን ሊሰምር አልቻለም፡፡ በርካታ ምክንያቶች ለዚህ ቢቀርቡም፣ ሳሳካዋ ግሎባል 2000 በተለይ በኢትዮጵያ ስኬታማ ከሆነባቸው መስኮች መካከል የኤክስቴንሽን አገልግሎት ተጠቃሽ ነው፡፡

  በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በኡጋንዳ፣ በማሊ እንዲሁም በናይጄሪያ ውስጥ ብቻ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ሳሳካዋ ግሎባል፣ ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት የሚመራበትን ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፏል፡፡ በአፍሪካ 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አካቶ፣ በኢትዮጵያ ቆይታውም 24ኛ ዓመቱን አስታኮ በአዳማ ከተማ መጋቢት 21 እና 22 ቀን 2009 ዓ.ም. የሁለት ቀናት ዓውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

  የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር)፣ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊው አቶ ስለሺ ጌታሁን የታደሙበት ዓውደ ጥናት ላይ የሳሳካዋ በኢትዮጵያ አጀማመርና አሁን የሚገኝበት ደረጃ ተወስቷል፡፡ ሁለቱ ኃላፊዎች እንደገለጹት ሳሳካዋ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በአገሪቱ ተከስቶ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ያለቀበት ድርቅ መገባደጃው ሰሞን ነበር፡፡ ይህ ወቅት አገሪቱ የግብርና ዘርፍ ዝቅተኛውን የምርት ውጤት እያስመዘገበ የነበረበት እንደነበር አውስተዋል፡፡

  የሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አበራ ደበሎ (ዶ/ር) እንዳስታወሱት፣ በወቅቱ በሄክታር አንድ ቶን ያህል ምርት የሚገኝበት ወቅት አሁን ላይ በአምስት እጥፍ ሊጨምር ችሏል፡፡ የሳሳካዋ ግሎባል ትልቅ አስተዋጽኦ ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል በተለይ በአገሪቱ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ማስፋፋት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ የሠርቶ ማሳያ ጣቢያዎችን በማስፋፋት፣ የግብርና ባለሙያዎችንና አምራች ገበሬዎችን በማሰልጠን ውጤታማ ሥራዎች እንዲስፋፉ ዕገዛ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

  የመጀመሪያው ምዕራፍ በጀመረ በሁለት ዓመት ውስጥ ለውጦችን ማስመዝገብ የቻለው ሳሳካዋ፣ በተለይ በሁለተኛው ምዕራፍ እንቅስቃሴው ማለትም እ.ኤ.አ. ከ1995 እስከ 2003 ባለው ጊዜ ውስጥ በተመዘገበው ለውጥ አማካይነት ባሳየው ለውጥ ምክንያት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የተዘዋዋሪ ፈንድ መንግሥት በመመደብ ለገበሬዎች ምርጥ ዘር ተገዝቶ እንዲያሰራጭ ያነሳሳ አካሄድ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ከመሆኑ ቀድሞ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋባዥነት በኢትዮጵያ የኤክስቴንሽን አገልግሎትን እንዲያስተዋውቁ የተጋበዙት ሚ/ር ሳሳከዋ፣ በኢትዮጵያ መሠረቱን የዘረጋ ተቋም እንዲመሠረት አድርገዋል፡፡

  በሁለተኛው ምዕራፍ የሳሳካዋ ግሎባል እንቅስቃሴ ከዝቅተኛ የምርት መጠን ወደ ከፍተኛ የምርት ዕድገት አገሪቱ መሸጋገር በመጀመሯ፣ ሌሎች ስጋቶች እየተፈጠሩ መምጣታቸውን አቶ አበራ አስታውሰዋል፡፡ ይህም ድኅረ ምርት አሰባሰብ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች ስጋት መፍጠራቸው ነው፡፡ የምርት ማካማቻዎች እንደልብ አለመኖራቸው ምርት እንዲባክን ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ይሁንና በወቅቱ የነበሩ የተቋሙ ኃላፊዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት የምርት ማከማቻዎችና ሌሎችም ምርት ሳይበላሽ እንዲቆይ የሚያስችሉ አሠራሮችን ማስተዋወቅና ማስፋፋት ጀምረው ነበር፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት የሚታየው የድኅረ ምርት አሰባሰብ ብክነት በአማካይ እስከ 30 በመቶ ይገመታል፡፡

  ከዚህ ባሻገር የአገሪቱ አነስተኛ ገበሬዎች በአማካይ የሚያርሱት መሬት አንድ ሔክታርና ከዚያ በታች በመሆኑ እንደ ሜካናይዜሽን፣ እንደ የተሻሻሉ ግብዓቶችን የመጠቀም፣ ዘመናዊ ማረሻዎች፣ የምርት መሰብሰቢያዎች፣ መውቂያና ማበጠሪያዎች የመሳሰሉትን በማስተዋወቅ እንዲተገበሩ ማድረጉ ለአነስተኛው ገበሬ ካለው የመሬት ይዞታ አኳያ አዋጭነቱ እንዴት ይታያል ለሚለው ምላሽ የሰጡት አቶ አበራ፣ እንዲህ ያሉት ግብዓቶች በገበሬው አቅምና ችሎታ ጋር ተመጣጥነው በፍላጎቱ ላይ ተመሥርተው ይቀርባሉ የሚል ነው፡፡

  ከዚህም ባሻገር ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲተገበር የቆየና በአነስተኛ የገንዘብ አቅራቢ ድርጅቶች አማካይነት ለገበሬ ማኅበራት ኅብረት ሥራ የኒየን አባላት በብድር መልክ የሚሰጥ የተዘዋዋሪ ፈንድ መድቦ እያንቀሳቀሰ የሚገኝበት ሥራ ለሳሳካዋ ግሎባል 2000 ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል የሚመደብ ነው፡፡ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ በሬቻ ቱሪ ለሪፖርተር እንዳብራሩት በነፍስ ወከፍ እስከ 70 ሺሕ ብር ለአንድ ዩኒየን የሚዳረስበትን የአሥር ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ እያገዘ ይገኛል፡፡ ይህ በመሆኑም በስምንት ክልሎች ውስጥ በ149 ወረዳዎች በኩል ገንዘቡ እንዲዳረስ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ አብዛኞቹ ገበሬ ማኅበሮች በሁለት ዓመት ውስጥ የወሰዱትን ብድር መመለስ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ እንደ ሥራቸው ውጤትና ክብደት እየታዩም ወደ ሦስት ዓመት የተራዘመላቸው እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ በጉራጌ ዞን የወሰዱትን ብድር ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ከመለለስ አልፈው የምርት ማከማቻ መጋዘን በመገንባት ለውጥ ያሳዩ ገበሬዎችን ዋቢ ያደረጉት አቶ በሬቻ ፈንዱ በዚህ መልኩ እየተዘዋወረ፣ በዚያው አነስተኛ ገበሬዎች እየተጠቀሙበት የሚቀር እንደሚሆን እንጂ ሳሳካዋ መልሶ የማይወስደው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

  በተለይ የግብርና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ረገድ ትልቅ ድርሻ የሚወጣው ሳሳካዋ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ፈንድ (ሴፍ) የሚባለው ተቋም በአሁኑ ወቅት ከዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ማለትም ከሀሮማያ፣ ከጅማ፣ ከአዳማ፣ ከሰመራ፣ ከጂግጂጋ፣ ከባህር ዳር፣ ከሐዋሳ፣ ከመቐለ እንዲሁም ከወሎ ዩኒቨርሲተዎች ጋር በመስማማት የሁለት ዓመት ተኩል ሥልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ በተለይ ለአርብቶ አደር አከባቢዎች የሚስማሙ ሥልጠናዎችን ለመስጠት በማሰብ ከጂግጂጋና ከሠመራ ዩኒቨርሲዎች ጋር በመተባበር አርብቶ አደር ተኮር ሥርዓተ ትምህርት መዘርጋቱን አስታውቋል፡፡

  ይህ ሁሉ ቢጠቀስም የአገሪቱ የግብርና ዘርፍ ግን ሕዝቡን በበቂ መመገብ አላስቻለም፡፡ ይልቁንም ባለፈው ዓመት በተከሰተው ድርቅ 10.2 ሚሊዮን ሕዝብ ለዕለት ደራሽ ምግብ ዕርዳታ ተዳርጎ ነበር፡፡ በዚህም ዓመት በቆላማ አገሪቱ ክፍሎች በተከሰተው ድርቅ 5.6 ሚሊዮን በምግብ ዕርዳታ ተዳርጓል፡፡ ይህም ቢባል ግን አገሪቱ ሌላው ቢቀር ከውጭ ዕርዳታ ይልቅ የራሷን ችግር በራሷ አቅም ለመመከት የምትችልበት ደረጃ ላይ መድረሷም ቸል የማይባል ለውጥ እንደሆ አቶ አበራ ያሳስባሉ፡፡

  የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒኒስትሩ በበኩላቸው ግብርናው በብዙ ችግሮች የተውተበተበ በመሆኑ እግሩ ጸንቶ በሚገባ ለመቆም እንደ ሳሳካዋ ግሎባል ያሉ አጋሮቹ ሊያግዙት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ገበሬዎች ግብዓት ለማግኘት የሚያዩት ውጣ ውረድ፣ ደካማ የገበያ ትስስር፣ የክህሎት ማነስ፣ ተደጋጋሚና አሳሳቢ የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት እጥረት እና ሌሎችም አገሪቱን የሚፈታተኑ ችግሮች እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

  ይህ ሁሉ ችግር ቢኖርም የአገሪቱ ምርት አሁን ካለበት ከ270 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 400 ሚሊዮን ኩንታል ማደግ እንደሚጠበቅበት፣ በተለይ የዋና ዋና ሰብሎች ምርት በ52 በመቶ ማደግ እንደሚያስፈልገው፣ የኤክስቴንሽን አገልግሎትም በያመቱ የስምንት በመቶ ዕድገት ማሳየት እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ለማሟላት ደግሞ እንደ ሳሳካዋ ያሉ ድርጅቶች የሚደርጉት አስተዋጽኦ ይጠበቃል ብልዋል፡፡

  መንግሥት የሚማራባቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተንተርሶ የሚንቀሳቀሰው ሳሳካዋ ግሎባል ከመንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት መነሳቱንና እ.ኤ.ኤ 2017 ጀምሮ እስከ 2021 ድረስ የሚመራበትን አዲስ ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ አድርጓል፡፡ በዕቅዱ መሠረትም ኢትዮጵያን ጨምሮ በሚንቀሳቀስባቸው አራት አገሮች ውስት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ሥራዎችም ለይቷል፡፡  

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች