- በፌዴራል ደረጃ ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም 123.9 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን ነዋሪዎች ለማቋቋም የጀመረውን ፕሮግራም፣ ቀደም ሲል ከያዘው 123 ሺሕ በተጨማሪ 200 ሺሕ ነዋሪዎችን አካተተ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሥር ክፍላተ ከተሞች 116 ወረዳዎች አሏቸው፡፡ የከተማው አስተዳደር ከመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በ35 ወረዳዎች የሚገኙ 123 ሺሕ ‹‹የደሃ ደሃ›› የሚባሉ ነዋሪዎች ያለባቸውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታት፣ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወን ጀምሮ ነበር፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የአገር ውስጥ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና የዳያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ካሳ ወልደ ሰንበት እንደገለጹት፣ ይህ ፕሮግራም ውጤታማ ሆኗል፡፡
‹‹ከሌሎች ክልሎች አንፃር አዲስ አበባ ዘግይቶ ቢጀምርም፣ የፕሮግራሙ የፋይናንስ ምንጭ የሆነው የዓለም ባንክ ተወካዮች ከሳምንት በፊት ፕሮግራሙ ያለበትን ደረጃ ከተመለከቱ በኋላ ውጤታማ መሆኑን ለከንቲባ ድሪባ ኩማ ገልጸውላቸዋል፤›› ሲሉ አቶ ካሳ ፕሮግራሙ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሠረት አስተዳደሩ የጀመረውን የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በዚህ ዓመት ይበልጥ በማስፋት፣ 55 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 200 ሺሕ ዜጎችን ያካተቱ መሆኑን አቶ ካሳ አስረድተዋል፡፡
ይህ አዲስ አበባ ከተማ የጀመረው ፕሮግራም የፌዴራል መንግሥት በ927 ከተሞች የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ያልቻሉ 4.7 ሚሊዮን ዜጎች ለማቋቋም የያዘው ግዙፍ ዕቅድ አካል ነው፡፡
መንግሥት ከዚህ ውስጥ 3.5 ሚሊዮን ዜጎች በተለያዩ የሥራ መስኮች ለማሰማራት፣ 1.3 ሚሊዮን ዜጎችን ደግሞ በቀጥታ በሥራ ሊሰማሩ የማይችሉ በመሆናቸው ቀጥታ ድጋፍ እንዲያገኙ ዕቅድ አውጥቷል፡፡
ፕሮግራሙ በአገር አቀፍ ደረጃ ለአሥር ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 123.9 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ያወጣው ሰነድ ያመለክታል፡፡