ቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የሶማሌላንድ መንግሥት ጉዳይ ፈጻሚ ጽሕፈት ቤትን በማቃጠል ወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡
ተጠርጣሪው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለውና በቅርቡ ከሶማሌላንድ ዋና ከተማ ሐርጌሳ ተፈናቅሎ እንደመጣ ለፖሊስ ማስረዳቱን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የፖሊስ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ተጠርጣሪው በቅርቡ ከሐርጌሳ ተፈናቅሎ እንደመጣና ወንጀሉንም በበቀል ተነሳስቶ እንደፈጸመው ለፖሊስ መናገሩ ተሰምቷል፡፡
ጉዳዩን እየመረመረው የሚገኘው የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ሲሆን፣ ተጠርጣሪው ወንጀሉን እንደፈጸመ በራሱ ማመኑን ማወቅ ተችሏል፡፡
መስከረም 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓት የሶማሌላንድ ጉዳይ ፈጻሚ ጽሕፈት ቤት በሚገኝበት ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ወንጀሉ እንደተፈጸመ፣ ተጠርጣሪውም አጥር ዘሎ በመግባት ወንጀሉን መፈጸሙን እንደተናገረ የፖሊስ ምንጮች አስረድተዋል፡፡
ቃጠሎው የጽሕፈት ቤቱ የእንግዳ መቀበያ ክፍል ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ በድርጊቱ መቀመጫዎችና የተለያዩ ቁሳቁሶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ተመልክቷል፡፡
ቃጠሎው በደረሰበት ዕለት ከምሽቱ 3፡12 ላይ የተደወለለት የከተማው የእሳት አደጋ መከላከል ኤጀንሲ ሰባት ባለሙያዎችንና አንድ የእሳት አደጋ መከላከያ መኪና አሰማርቷል፡፡
እሳቱንም ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር 46 ደቂቃ እንደፈጀ የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሰለሞን መኮንን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የጉዳቱ መጠን 100 ሺሕ ብር እንደተገመተ አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡ ተጠርጣሪው አደጋው እንደ ደረሰ ለፖሊስ በፈቃደኝነት እጁን እንደ ሰጠ የፖሊስ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
አደጋው ከተከሰተ በኋላ ጽሕፈት ቤቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለጉዳዩ ሪፖርት ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ ጉዳዩም እየተጣራ እንደሚገኝና ውጤቱ በቅርቡ እንደሚገለጽ አመልክተዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሶማሌላንድ ጉዳይ ፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓሊ ሁሴን፣ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡