Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበጋብቻ ላይ ጋብቻ ለሚመሠርቱ ሴቶች ከሁለተኛው ጋብቻ ንብረት እንዲካፈሉ የሚፈቅድ የሕግ ሰነድ...

በጋብቻ ላይ ጋብቻ ለሚመሠርቱ ሴቶች ከሁለተኛው ጋብቻ ንብረት እንዲካፈሉ የሚፈቅድ የሕግ ሰነድ ቀረበ

ቀን:

በጋብቻ ላይ ጋብቻ የሚመሠርቱ ሴቶችን መብቶች ለማስጠበቅ ሲባል፣ ከሁለተኛው ወይም በላይ ከሚመሠረተው ጋብቻ ሴቶች የንብረት ተካፋይ እንዲሆኑ የሚፈቅድ ረቂቅ የሆነ ሰነድ ለፓርላማ ቀረበ፡፡

የአገሪቱ የወንጀል ሕግ በአንቀጽ 650 ላይ በጋብቻ ላይ ጋብቻን መፈጸም የሚከለክል መሆኑን በመጠቆም አንዳንድ የፓርላማ አባላት ረቂቁ ላይ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ ሕጉን ከዚህ አንፃር እንዲመረምረው ጠይቀዋል፡፡

በማከልም ይኸው ረቂቅ የሕግ ሰነድ በ2006 ዓ.ም. ለፓርላማ ቀርቦ በዚህ ምክንያት (ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 650 ጋር የሚጋጭ ነው በሚል) እንዲመለስ መደረጉን በማስታወስ፣ ማስተካከያ ሳይደረግበት እንዴት ተመልሶ ሊመጣ ቻለ ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

- Advertisement -

ጥቅምት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፓርላማው የቀረበው ይህ ረቂቅ አዋጅ፣ ‹‹የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ስምምነት የአፍሪካ ሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ›› የተሰኘ ነው፡፡

የፓርላማው አንዳንድ ሴት አባላት ፕሮቶኮሉ ከኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ጋር እንደሚቃረንና በዚሁ ምክንያትም ይኸው ፕሮቶኮል በ2006 ዓ.ም. ለፓርላማ ቀርቦ እንዲመለስ እንደተደረገ ቢገልጹም፣ ለረቂቅ የፕሮቶከሉ ማፅደቂያ አባሪ የተደረገው ማብራሪያ ግን ከወንጀል ሕጉ ጋር ይኖረዋል ስለተባለው ግጭት ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ በአንቀጽ 650 ላይ በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈጸም ወንጀል መሆኑን በመደንገግ ቅጣት ቢያስቀምጥም፣ የዚሁ አንቀጽ ተከታይ አንቀጽ 651 ግን በልዩ ሁኔታ ባህል ወይም ሃይማኖት በሚያዘው መሠረት የሚከናወን በጋብቻ ላይ ጋብቻ በአንቀጽ 650 ሥር ሊወድቅ እንደማይችል በማብራራት የክርክር መሠረቱን ይጥላል፡፡

በማከልም የቤተሰብ ሕጉ በጋብቻ ላይ ጋብቻ ተፈጽሞ ሲገኝ በሁለተኛው ጋብቻ ውስጥ የሚኖረው የንብረት ክፍፍል ምን እንዲመስል የሚያስቀምጠው ነገር ባለመኖሩ፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻ ቢፈጸም የሚያስከትለው በፍትሐ ብሔር ውጤት አለመመለሱን ይገልጻል፡፡

ይሁን እንጂ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 50469 በጋብቻ ላይ ጋብቻ የተከለከለ ቢሆንም በማኅበረሰቡ እየተተገበረ ያለ ልምድ እንደሆነ፣ ነገር ግን ሕጉ የተጋቢ ሴቶችን መብት በሚያስጠብቅ አኳኋን መተርጎም እንዳለበት መወሰኑን ያስረዳል፡፡

በዚሁ  መሠረትም በሁለተኛ ጋብቻ ውስጥ ያለችው ሴት የወንዱን ድርሻ እኩል መካፈል እንዳለባት ሰበር ሰሚ ችሎቱ መወሰኑን ያስረዳል፡፡

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጁን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(4) ከላይ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ገዥ የሕግ ትርጉም (ወይም እንደ ሕግ የሚቆጠር) ያለው እንደሆነ በመደንገጉ፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻን አስመልክቶ የሰጠው ውሳኔ በጋብቻ ላይ ጋብቻ የፈጸሙ ሴቶችን ጥቅም የሚያስጠብቅ የሕግ ሥርዓት እንዲፈጠር ማድረጉን ይገልጻል፡፡

በዚህም መሠረት በፕሮቶኮሉ ላይ በጋብቻ ላይ ጋብቻ የፈጸሙ ሴቶች ከሁለተኛው ጋብቻ ንብረት ተካፋይነታቸው በኢትዮጵያ ሕግ እንደሚፈጸም የሚገልጽ መግለጫ በማስገባት፣ ፕሮቶኮሉን መንግሥት እንደተቀበለው ይገልጻል፡፡

በፕሮቶኮሉ አንቀጽ 6 (D) ላይ የጋብቻ ምዝገባን እንደ ሕጋዊ ጋብቻ መሥፈርት የሚያስምጥ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን ለዚህ አንቀጽ ተገዥ እንደማይሆን ተገልጿል፡፡

ለዚህ የተሰጠው ምክንያትም በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ በባህልና በሃይማኖት የፈጸሙ ጋብቻዎች መመዝገብ እንዳለባቸው ቢደነግግም፣ በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ጋብቻ መመዝብ እንዳለበት ቢደነግም፣ በእነዚህ ሕጎች የጋብቻ አለመመዝገብ ጋብቻውን ሕጋዊ እንዳይሆን የማያደርገው መሆኑ ነው፡፡

የፕሮቶኮሉ አንቀጽ 4 (2) (A) ላይ በጋብቻ ውስጥ የሚፈጸም አስገድዶ መድፈርን የመቅጣት ግዴታ ፈራሚ አገሮች ላይ ይጥላል፡፡ ኢትዮጵያ ተአቅቦ በማድረግ እንዳልተቀበለችው የተገለጸ ሲሆን፣ አስገድዶ መድፈርን የተመለከተው የፕሮቶኮሉ አንቀጽ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት እንደሚፈጸም በማብራሪያው ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው የፕሮቶኮሉ አንቀጾች መካከል የሴቶችን በራሳቸውና  በቤተሰባቸው ላይ የመወሰን አቅም ማሳደግን የተመለከተ፣ የልጃገረዶችን ትምህርት የማሳደግ፣ የሕፃናት ጋብቻንና ግርዛትን መግታት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ረቂቁ ለሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት ተመርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...