በ2004 እና በ2005 በጀት ዓመት መከፈል የነበረበትን ግብር ሳይከፍሉ በመቅረታቸው አራት ሚሊዮን ብር ይከፍላሉ ከተባሉ ግብር ከፋይ 400 ሺሕ ብር ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል የተባሉ፣ ሁለት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. የቀረቡት ተጠርጣሪዎች፣ የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ታክስ ኦዲተር አቶ ገመቹ አያኖና የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ታክስ ኦዲተር ቡድን አስተባባሪ ወ/ሪት ምሕረት መርሻዬ ናቸው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ አቶ አበበ ሙሉጌታ የተባሉ ግብር ከፋይን የ2004 እና የ2005 በጀት ዓመት ግብር ሒሳብ ኦዲት ሲያደርጉ፣ ብዙ የግብር ስወራ መኖሩን እንደ ነገሯቸው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በግምት ለመንግሥት የሚከፈል አራት ሚሊዮን ብር እንዳለባቸውም እንዳሳወቋቸው አክሏል፡፡
ግብር ከፋዩ የግብር ዘመኑ ከማለፉ በፊት መክፈል እንዳለባቸው ተጠርጣሪዎቹ ከነገሯቸው በኋላ፣ አንድ ሚሊዮን ብር ብቻ እንዲከፍሉ እንደሚያደርጉላቸው በመግለጽ መደራደራቸውንና መስማማታቸውን ፖሊስ ገልጿል፡፡
ፖሊስ ጥቆማ ደርሶት ሲከታተል ከቆየ በኋላ ጥቅምት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ከምሽቱ 12፡45 ሰዓት ላይ አቶ ገመቹ 400 ሺሕ ብር ከግብር ከፋዩ ሲቀበሉ ብሥራተ ገብርኤል አካባቢ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን አስረድቷል፡፡ እጅ ከፍንጅ ሲያዙ ገንዘቡም በኤግዚቢትነት መያዙንና የአቶ ገመቹን ቃል መቀበሉን ጠቅሶ፣ የሌላኛዋን ተጠርጣሪ ቃል መቀበል፣ ሰነዶችን መሰብሰብና ከኢትዮ ቴሌኮም የስልክ ልውውጥ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ የሦስት ምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው በመግለጽ፣ 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸው አማካይነት እጅ ከፍንጅ ተያዙ ከተባለ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊጠየቅ አይገባም በማለት ተከራክረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ሰምቶ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ የሰባት ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዶ፣ ለጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡