Saturday, December 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከአገርና ከሕዝብ በላይ ምንም ነገር የለም!

የአገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካ ትኩሳት ከአገርና ከሕዝብ ዘለቄታዊ ህልውና ጋር ሲነፃፀር፣ በግራ መጋባትና በውዥንብሮች መሞላቱ ግልጽ ነው፡፡ በተለይ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮች መካከል መቃቃር ተፈጥሯል ተብሎ በአደባባይ መሰማት ከጀመረ መሰነባበቱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በቀናት ልዩነት ውስጥ የድርጅቱ ነባር አመራሮች ከያዙት ኃላፊነት በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው መሰማቱ በድርጅቱ ታሪክ አዲስ ቢሆንም፣ በአባል ድርጅቶች መካከል የነበረው መስተጋብር ግን እንደ በፊቱ እንዳልሆነ ግን ግልጽ እየሆነ ለመምጣቱ ሌላው ማሳያ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ላለፉት 26 ዓመታት በላይ አገር እንደ መምራቱ መጠን፣ በውስጡ የሚካሄዱ ሽኩቻዎች ወይም ልዩነቶች የሕዝብንና የአገርን ሰላም ማናጋት አይኖርባቸውም፡፡ የአመራሩ ፍላጎት ከሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች አፈንግጦ በሌላ አቅጣጫ የሚነጉድ ከሆነ፣ የአገርና የሕዝብ ህልውና ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ይሆናል ተብሎ የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ህልውና፣ ከምንም ነገር በላይ እንደሚበልጥ ማመን ይገባል፡፡

ላለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች የተከሰቱ ተቃውሞዎች ደም አፋሳሽ ስለነበሩ የበርካታ ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በርካታ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የተቃውሞ ድምፆች ይሰማሉ፡፡ ለችግሮች መፍትሔ ተገኝቶላቸው ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር መሠረታዊ ለውጦችን ለማምጣት መሥራት ሲገባ፣ እንዲህ ዓይነት የተቃውሞ ድምፆች መሰማት መቀጠላቸው ያለ ነው በማለት መገላገል አይቻልም፡፡ በውስጥ ሽኩቻም ሆነ በሌላ ምክንያት የነባር አመራሮች በቃኝ ማለት ሳይሆን ዋናው ቁም ነገር በአገሪቱ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚጠቅሙ ተግባራት በአግባቡ እየተከናወኑ ነው ወይ የሚለው ነው የሚያሳስበው፡፡ የትኛውም አመራር በሆነ ጊዜ ሊበቃው ይችላል፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን፡፡ ልዩነትን አክብሮ ሁሉንም አሳታፊ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ዓውድ በመፍጠር ሕዝብን ማረጋጋት ደግሞ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ከአገርና ከሕዝብ በላይ ምንም ነገር ስለሌለ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሕዝብ ውስጥ በርካታ መረጃዎች ይሠራጫሉ፡፡ ምንጫቸው ከማይታወቅ ተራ ጉዳዮች እስከ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ድረስ የሚሠራጩት ብዙዎቹ መረጃዎች፣ እንደ አገርና እንደ ሕዝብ የመቀጠልን ተስፋ የሚያጨልሙ ናቸው፡፡ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንደሚፈጥር የሚጠበቀው ፌዴራላዊ ሥርዓትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ድርጊቶችን ማስቆም ሲገባ፣ በሥርዓቱ ላይ የሚቀርቡ ትችቶች ላይ ብቻ መንጠላጠል አይገባም፡፡ ለኢትዮጵያ ከፌዴራል ሥርዓቱ ውጪ ማሰብ እንደማይቻል ግልጽ ነው፡፡ ይህ ክርክር ጊዜ ያለፈበትም ነው፡፡ ነገር ግን የፌዴራል ሥርዓቱ ባለቤት ነን የሚሉ ወገኖች በሚፈጥሩት ችግር ሕዝብ ሲሞት፣ ጉዳት ሲደርስበትና ከቀዬው ሲፈናቀል ምክንያቱን አብጠርጥሮ የማወቅና የማስረዳት ኃላፊነት የመንግሥት ብቻ ነው፡፡ እግረ መንገዱንም በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በሰከነ መንገድ አይቶ የማስተካከል ኃላፊነትም እንዲሁ፡፡ ከአገርና ከሕዝብ በላይ ማን አለ?

የገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶችና የክልሎች አመራሮች እንደ ወትሮው እየተናበቡ መሥራት ቢያቅታቸው እንኳ፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በሠፈሩ ድንጋጌዎች አማካይነት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ለዘመናት የተጠራቀሙ የሕዝብ ብሶቶችና ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ከሕገወጥ ድርጊቶች ይልቅ ለሕግ የበላይነት መገዛት ሲቻል ነው፡፡ በተለያዩ መንገዶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰሙ ድምፆች መኖራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ድምፆች ሲሰሙ ሊኖር የሚገባው ፈጣንና አስተማማኝ የሆነ መረጃ ነው፡፡ ሕዝብ በየጊዜው በሚደርሱት መረጃዎች ሳቢያ የወደፊት ዕጣ ፈንታው ሲያሳስበው፣ በጠንካራ ቁመና ላይ የሚገኝና አስተማማኝ መረጃ የሚሰጥ መንግሥታዊ አካል መኖር አለበት፡፡ የእዚህ አካል ፋይዳው ሕዝብን ለማረጋጋት ብቻ ሳይሆን፣ የአገርን ውሎና አዳር በአግባቡ ለማወቅ ይጠቅማል፡፡ አሉ የሚባሉት የአመራሮች ክፍተቶችና መቃቃሮች ደረጃም ይታወቃል፡፡ ይህ ለምን ይጠየቃል? ምክንያቱም የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ መሆን እንዳለበትና ተጠያቂነቱም በዚያው ልክ መሆኑን ስለደነገገ ነው፡፡ ሕግ ደግሞ መከበር አለበት፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያስተሳሰረው የሰላም፣ የአንድነትና የፍቅር ገመድ እንዳይበጠስ ምን መደረግ አለበት መባል ይኖርበታል፡፡ ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ ከሚጠቀሱለት የጋራ እሴቶች መካከል ዋነኛው ለአገሩ ያለው ጥልቅ ፍቅር ነው፡፡ ይህ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ የዘመናት እሴት ሊከበር ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለው የጀግኖችና የጨዋ ኢትዮጵያውያን አገር ለዘመናት ወራሪዎች ቢፈትኗትም አልተሳካላቸውም፡፡ ይህች ታሪካዊ የጀግኖች አገር ህልውናዋ አስተማማኝ ሆኖ መቀጠል አለበት፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ፍላጎት ወይም ጥቅም ከአገር በላይ አይደለም፡፡ ሆኖም አያውቅም፡፡ አስተዋዩና ጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ የሚያሳስበው የአገሩ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ሕዝብ ማክበር ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱን ጉዳይ ፖለቲካዊ ገጽታ በማላበስ ከተወሰኑ በድኖች ዕይታ አንፃር ብቻ ማንገዋለል ለአገር አይበጅም፡፡ ግለሰቦች ያልፋሉ፣ አገር ግን አታልፍም፡፡ ይልቁንም የትውልድና የታሪክ ተጠያቂ ላለመሆን ጥረት ማድረግ ይበጃል፡፡ ከአገርና ከሕዝብ በላይ ምንም ስለሌለ፡፡

ሁሌም እንደምንለው መንግሥት ሕዝብን ማዳመጥ አለበት፡፡ ሀቁን ብንነጋገር ሕዝብ የመንግሥት ቀጣሪ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ከፌዴራል መንግሥቱ በተጨማሪ ክልሎችን ይመለከታል፡፡ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ሕዝብን ያክብሩ፡፡ ለሕዝብ ፍላጎት ይገዙ፡፡ ሕዝብን አለማዳመጥ ነው ብዙ ችግሮችን የወለደው፡፡ በተለያዩ ጎራዎች የተሠለፉ የፖለቲካ ኃይሎችም ለሕዝብ ፍላጎት ራሳቸውን ማስገዛት አለባቸው፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተሰማሩም ቢሆኑ ይህ ኃላፊነት ይመለከታቸዋል፡፡ አገር የምታድገውና የምትበለፅገው ሰላም ሲኖራት ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ንፁኃን ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ አገር ትተራመሳለች፡፡ በዚህ መንገድ ደግሞ መቼም ቢሆን አገር መምራትም ሆነ፣ እንደምንም ብሎ ሥልጣን ላይ መውጣትም አይቻልም፡፡ በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ውይይትና ክርክር ማድረግ ሲገባ፣ ያንን የተለመደ ጨፍጋጋና ጨለምተኛ መወነጃጀል ማስቀጠል ለማንም አይጠቅምም፡፡ ከዚህ በፊት ያፈራው ፍሬም የለም፡፡ አሁን መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላይ ማሰብ ያለበት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላም፣ በአንድነትና በፍቅር ለመኖር የሚያስችለውን አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ዓውድ ስለመፍጠር ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ያሉ ድርጊቶች ለአገር አይበጁም፡፡ ከሕዝብና ከአገር በላይ ምንም ነገር የለም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...