Sunday, December 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየኦሮሚያና የሶማሌ ግጭት በወጪና በገቢ ንግድ መተላለፊያ መስመር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሩ...

  የኦሮሚያና የሶማሌ ግጭት በወጪና በገቢ ንግድ መተላለፊያ መስመር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሩ ተገለጸ

  ቀን:

  በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት፣ በወጪና በገቢ ንግድ መተላለፊያ መስመር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሩን፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

  ኃላፊው ይህን ያስታወቁት ማክሰኞ ጥቅምት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

  ችግሩን ለመፍታት ንግድ ሚኒስቴርና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሁለቱ ክልሎች አካላት እየተነጋገሩ ቢሆንም፣ ከመሀል አገር ወደ ሶማሌ ወይም ከሶማሌ ወደ መሀል አገር በሚገቡ ጭነቶች ላይ የሚደርሰው ጫና አሁንም መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡

  ‹‹በተለይም ደግሞ በምሥራቁ የአገራችን ክፍል በፍራፍሬና በጫት ምርት ንግድ ላይ ኑሮአቸውን የመሠረቱ አርሶ አደሮችም በዚህ መንገድ ላይ በሚደረገው መስተጓጎል ምክንያት ሕይወታቸው ችግር ላይ ወድቋል፤›› ብለዋል፡፡

  ይህ ግጭት የአርሶ አደሮቹን ሕይወት እየጎዳ እንደሆነ፣ በአካባቢዎቹ የሚመረቱ ምርቶች በሚፈለገው ደረጃ ወደ ውጭ ገበያ እንዳይቀርቡ የሚደረጉ ክልከላዎች መኖራቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

  በተለይ እንደ ጫት ያሉትን የወጪ ንግድ ምርቶች በማምረትና በመሸጥ በሚተዳደሩ አርሶ አደሮችና ላኪዎች ላይ ከደረሰው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በተጨማሪ፣ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ ጫና እያደረሰ እንደሆነና ይህን ችግር ለማስቆምም የፌዴራል መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

  በግጭቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ቀደም ሲል ሲገለጽ ከነበረበት አሥር ሺዎች ወደ መቶ ሺዎች ከፍ ማለቱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

  በአሁኑ ጊዜ በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበት ሁኔታ በጣም አሳዛኝ እንደሆነ ጠቁመው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ዋጋው ምን ያህል ውድ እንደሆነ የሚረዳበት ጉዳት ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በቀረበው ሪፖርት መሠረት አጥፊዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋሉ ሥራ መጀመሩን የጠቀሱ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ምን ያህል ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡፡

  በተለይ በኦሮሚያ ክልል አወዳይ አካባቢ ከባድ ሰብዓዊ ጉዳት በማድረስ ወይም ግድያ በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦች፣ በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

  ምንም እንኳን በኦሮሚያ ክልል ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ቢውሉም፣ በሶማሌ ክልል በዜጎች ላይ ከባድ ሰብዓዊ ጉዳት በማድረስ ወይም ግድያ በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በክልሉ በኩል የተወሰደው ዕርምጃ አጥጋቢ አለመሆኑን፣ የቀረበው የፌዴራል ፖሊስ ሪፖርት እንደሚያመለክት ጠቁመዋል፡፡

  በመሆኑም የፌዴራል ፖሊስ አስፈላጊውን መረጃ እያደራጀና ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

  በቅርቡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው የፌዴራልና የክልል ልዑካን ቡድን በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ በአማሬሳና በባቢሌ ከተሞች በመጠለያ ካምፖች የሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎችን መጎብኘቱን ያስታወቁት ሚኒስትሩ፣ በተፈናቃዮቹ ላይ የደረሰው ጉዳት መጠን ከፍተኛ መሆኑን ተጠቂዎችን በማነጋገር መገንዘቡን አስረድተዋል፡፡

  በዚህም መሠረት ወላጆቻቸው የት እንዳሉ የማያውቁ ሕፃናትና ልጆቻቸው የት እንዳሉ የማያውቁ ወላጆች መኖራቸውን፣ ልዩ ልዩ አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች መኖራቸውን፣ በመጠለያ ካምፖች ለመውለድ የተገደዱ በድሬዳዋና በሐረር ብቻ 106 አራሾች እንዳሉ ልዑካኑ ማረጋገጥ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

  የትኛውም አካል በማንኛውም ሰው ላይ በብሔሩ ወይም በሃይማኖቱ ምክንያት የሚያደርሰውን ጉዳት የመከላከል ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...