Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በዘገየው የጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት ያረጀው የሸንኮራ አገዳ የ7.4 ቢሊዮን ብር ኪሳራ አስከተለ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት የተተከሉ የሸንኮራ አገዳ በአብዛኛው በማርጀቱ የ7.4 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንዳስከተለ ተገለጸ፡፡ 

  የጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት በማሳው ከተከለው 13,147 ሔክታር አገዳ መካከል በ12,206.6 ሔክታሩ ላይ ያለው አገዳ አርጅቷል፡፡ አገዳው ከተተከለ ከ31 እስከ 51 ወራት ተቆጥረዋል፡፡ የስኳር ይዘቱም 10.5 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በማርጀቱ ምክንያት ይዘቱ ቀንሷል፡፡ አገዳውን ከማሳው ለማስወገድና ሁለተኛው ምርት እንዲቀጥል ለማድረግ 1.06 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግም ታውቋል፡፡

  ከአንድ ሔክታር 15,000 ኩንታል አገዳ ይገኛል፡፡ አንድ ኩንታል ስኳር በ1,400 ብር ይሸጣል ተብሎ ቢታሰብ፣ አገዳው በማርጀቱ ምክንያት የሚታጣው ገንዘብ 7.4 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡ ‹‹በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ ያለበትን ሁኔታ የጨለማ ዘመን ብሎ መግለጽ ይቻላል፤›› ያሉት ከፕሮጀክቱ አመራሮች መካከል የሆኑት አቶ ሔኖክ በለጠ ናቸው፡፡

  ይህ የተከሰተው የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የፋብሪካ ግንባታ በጊዜ ባለመጠናቀቁ መሆኑን የሚናገሩት፣ የበለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ምርምር ልማት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኪዳኔ ተስፋ ሚካኤል ናቸው፡፡ ‹‹አሁን ያለው ዕድል ማሳው ላይ እንዳለ ማቃጠል ሳይሆን ያረጀውን አገዳ አንስቶ ራሱን (ሁለተኛ የሚበቅለውን) የአገዳ ክፍል እንዲቀጥል ማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡

  የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በአገሪቱ የሚታየውን የስኳር እጥረት ለመቅረፍ ብሎም ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ እንዲያመጣ ታቅዶ የተጀመረው ከስድስት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ ያረፈው የአማራ ክልል አካል በሆነው ጃዊ ወረዳና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ሥር በሚገኘው ፓዌ ወረዳ ነው፡፡ 75,000 ሔክታር ላይ ያረፈ ሲሆን፣ በወረዳዎቹ ይኖሩ የነበሩ 1,300 ነዋሪዎች ለፕሮጀክቱ ሲባል እንዲነሱ መደረጉም ታውቋል፡፡

  የፕሮጀክቱ ዋነኛ አካል የሆኑት ሦስት የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ እስካሁን አልተጠናቀቁም፡፡ ኃላፊዎቹ የፋብሪካዎቹ ግንባታም ምን ያህል ደረጃ መድረሱን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ ተጠናቀው ወደ ሥራ ቢገቡ በዓመት 7,260,000 ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም እንዳላቸውና ለ65,000 ዜጎችም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ይነገራል፡፡

  እንደ አቶ ሔኖክ ገለጻ፣ ጣና በለስ በሰከንድ 60 ሜትር ኪዩብ ውኃ የሚለቅ ግድብ አለው፡፡ ከተረፈ ምርት 62.4 ሚሊዮን ሊትር ኢታኖል፣ 165 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመርት ታልሞ የተጀመረ ነው፡፡ ልማቱን ለማስቀጠል የመስኖ መሠረተ ልማትና የመንገድ ሥራዎች በአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅትና በአማራ መንገድ ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ ነው የተገነቡት፡፡  

  ፕሮጀክቱ ከፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር በሸንኮራ አገዳ ባልተያዙ ክፍት ቦታዎች ላይ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የተጓዳኝ ምርት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በ54 ሔክታር መሬት ላይ ፍራፍሬ እያለማ መሆኑን፣ ከሙዝ ሽያጭ ብቻ በስድስት ወራት ውስጥ 20,939 ብር ገቢ ማግኘቱ ተገልጿል፡፡

  በአኩሪ አተርና በሩዝ ምርት አበረታች ውጤት መገኘቱን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ማሳውን ጋዜጠኞች በጎበኙበት ወቅት ተገልጿል፡፡  ባለፉት ሁለት ዓመታት 2,313 ኩንታል አኩሪ አተር በማልማት 1.7 ሚሊዮን ብር ማግኘት መቻሉ ታውቋል፡፡ ከለማው 2,908 ኩንታል የሩዝ ምርት ውስጥ 380 ኩንታል ለቀጣይ ዓመት ምርት ዘመን በዘርነት እንዲቀመጥ የተደረገ ሲሆን፣ ቀሪው 2,528 ኩንታል ግን የመፈልፈያ ማሽን ባለመገኘቱ በመጋዘን ተከማችቶ እንደሚገኝ አቶ ሔኖክ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከ800 ሔክታር በላይ በሩዝ ምርት ተሸፍኗል፡፡

  ‹‹መሬቱ ሙሉ ለሙሉ በሸንኮራ እስኪሸፈን ድረስ መሬቱ ክፍት ሆኖ እንዳይቀመጥ፣ በአረም እንዳይሸፈን፣ ሠራተኛውም ሥራ እንዳይፈታ የተጀመረ የተጓዳኝ ሰብል ልማት ነው፤›› ያሉት አቶ ኪዳኔ፣ ወደ ሥራው በስፋት የተገባው አምና በተደረገው ሙከራ አበረታች ለውጥ በመገኘቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡     

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች