- ስለምስክሮች ጥበቃ የወጣው አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ ጋር አይጋጭም ተባለ
በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ወንጀል በመፈጸም፣ የሐሰት ወሬ በማውራትና በወቅቱ ተደንግጎ የነበረን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመተላለፍ ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት ሰጡ፡፡
ዶ/ር መረራ፣ ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምኩም፣ ጥፋተኛ አይደለሁም፤›› በማለት የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምስክሮች ለማወቅ ሕገ መንግሥታዊ መብትና ከምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ጋር በተገናኘ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ነው፡፡
ዶ/ር መረራ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) መሠረት ዓቃቤ ሕግ የቆጠረባቸውን ምስክሮች ዝርዝር ሊሰጣቸው ወይም ሊያሳውቃቸው እንደሚገባ ሲያመለክቱ፣ ከሳሻቸው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ በምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ይፋ እንዲያደርግ እንደማይገደድ በመግለጽ ተቃውሞውን ለፍርድ ቤት አመልክቶ ነበር፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የሁለቱን ወገኖች ክርክር ከሰማ በኋላ፣ ዶ/ር መረራ አዋጁ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ ሊሽር (ሊበልጥ) ስለማይችል የዓቃቤ ሕግ መከራከሪያ ሐሳብ ውድቅ ተደርጎ የምስክሮቹ ዝርዝር ሊሰጣቸው እንደሚገባ በመከራከራቸው፣ ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም ሊሰጥበት ይገባል፤›› በማለት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ልኮት ነበር፡፡
ምክር ቤቱ በሰጠው ውሳኔ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ጋር የሚጋጭ ወይም የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሚቃረን ነገር እንደሌለው በመግለጽ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልገውም በማለት የዶ/ር መረራን አቤቱታን ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ዶ/ር መረራ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡
ሌላው ዶ/ር መረራ በዕድሜያቸው መግፋትና የስኳር ሕመምተኛ በመሆናቸው በካቴና ታስረው ሲቀርቡ፣ በእጃቸው ላይ መፋፋቅ ቢያጋጥማቸው አደጋ ሊያደርስባቸው ስለሚችል እንዳይታሰሩ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው በጠበቆቻቸው አማካይነት ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም ዶ/ር መረራን ለመጠየቅ ወደ ማረሚያ ቤት የሚሄዱ ሰዎች ብዙ ቢሆኑም፣ ገብተው እንዲጠይቁ የሚፈቀድላቸው ግን በጣም ጥቂት በመሆናቸው፣ ሊጠይቃቸው የሚሄዱ ሰዎች እንዲፈቀድላቸውም ጠበቆቹ ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን ከሰማ በኋላ ጥያቄያቸውን በጽሑፍ በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያቀርቡ በመንገር፣ ዓቃቤ ሕግ በዶ/ር መረራ ላይ የቆጠራቸውን ምስክሮች ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. አቅርቦ እንዲያሰማ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡