Tuesday, February 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ለውጡን በመንተራስ ዋጋ በሚያንሩ ላይ ዕርምጃ እወስዳለሁ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብር የምንዛሪ ተመን በ15 በመቶ እንዲቀንስ ካደረገ በኋላ የአገር ውስጥ ገበያ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየታየበት በመሆኑ፣ ይህንን ያልተገባ ድርጊት በሚፈጽሙት ላይ መንግሥት ዕርምጃ እወስዳለሁ አለ፡፡

በገበያ ውስጥ ብረትና እንጨትን ጨምሮ በተለያዩ የካፒታል ዕቃዎች፣ በተሽከርካሪዎች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በጥራጥሬና በቅባት እህሎችና በመሠረታዊ አቅርቦቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እየታየ ነው፡፡

የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ይፋ በተደረገ በማግሥቱ ከጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ መሆኑን መረጃዎች እንደደረሱት ለሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንደገለጸው፣ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር በዕቃዎችና በአገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በምንዛሪ ለውጡ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሸቀጦችን የሚደብቁና የሚያከማቹ ሕገወጥ ነጋዴዎች መኖራቸውን ከደረሰው ጥቆማና ከዚህ ቀደም ከነበሩ ልምዶች መረዳቱን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

በተለይ የውጭ ምንዛሪ ተመኑ ይፋ ከመደረጉ በፊት አገር ውስጥ በገቡ ምርቶችና አገር ውስጥ በተመረቱ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለውና ሕገወጥ በመሆኑ፣ መንግሥት የማስተካከያ ሕጋዊ ዕርምጃ ይወስዳል ብሏል፡፡ ከወራት በኋላ ወደ አገር በሚገቡ ምርቶች ላይ ሊኖር የሚችለውን የዋጋ ጭማሪ ከወዲሁ እየተጨመረ መሆኑ ከፍተኛ ሥጋት መፍጠሩን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

ቢያንስ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ሊኖር የሚችለውን ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አሁን እያደረጉ በሚገኙ፣ ምርቶችን በሚሰውሩና በሚያከማቹ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ በፌዴራል ደረጃ ግብረ ኃይል መቋቋሙ ተገልጿል፡፡

በንግድ ሚኒስትሩ በቀለ ቡላዶ (ዶ/ር) የሚመራው ግብረ ኃይል ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ዋጋ በሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡

የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የገበያ መረጃ ዳይሬክተር አቶ ኢቲሳ ደሜ፣ ‹‹የእኛ መሥሪያ ቤት አባል የሆነበት ግብረ ኃይል በንግድ ሚኒስቴር ሥር ተቋቁሟል፡፡ የሚመለከታቸው ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች በግብረ ኃይሉ ተካተዋል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አቶ ኢቲሳ ጨምረው እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በሸቀጦች ላይ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ኢኮኖሚያዊ መሠረት የለውም፡፡ ነገር ግን ጭማሪ እየተደረገ በመሆኑ መሥሪያ ቤታቸው በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ዕርምጃ መውሰድ ይጀምራል፡፡

ግብረ ኃይሉም ሆነ ባለሥልጣኑ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙት ላይ የንግድ ፈቃድ ከማገድ እስከ ንግድ መደብር የማሸግ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች፣ እንዲሁም በሕግ እስከ መጠየቅ የሚደርስ ዕርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል፡፡  

ከዚህ በተጨማሪ የባለሥልጣኑ መግለጫ በአቋራጭ አላስፈላጊ ትርፍ ለማግበስበስ ከሚደረግ ጥረት ነጋዴው በመቆጠብ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስቧል፡፡

‹‹የውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ የተደረገው ማሻሻያ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የተፈጸመ ነው፡፡ የወጪ ንግድን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በአገር ውስጥ ምርትና በውጭ ምርቶች ላይ በአሁኑ ጊዜ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል የሚችል ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለ መሆኑ ታውቆ፣ ማንኛውም በድርጊቱ የሚሳተፍ በአቋራጭ ትርፍ ለማግበስበስ ከሚደረግ ጥረት በመቆጠብ በማኅበራዊ ኃላፊነት ኅብረተሰቡን እንዲያገለግል እናሳስባለን፤›› ሲል ባለሥልጣኑ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በዚህ ዓመት ከቀድሞ የተለየ የፍላጎት መጨመር ያልታየ በመሆኑ፣ የነዳጅ ዋጋም የተረጋጋ ስለሆነና በአገር ውስጥ የተለየ ጭማሪ ያልተደረገ በመሆኑ የሰሞኑ የዋጋ ጭማሪዎች ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌላቸው ናቸው ብሏል፡፡ ‹‹በተለይ ዋጋ እየጨመረ የሚገኘው ወደፊት ሊጨምር ይችላል ከሚል ሥጋት (Speculation) በመሆኑ፣ በንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ ዋጋ ይጨምራል ብሎ በማሰብ ምርትን መደበቅ፣ መገደብና ሰው ሠራሽ እጥረት መፍጠር በሕግ ያስቀጣል፤›› ሲል አስገንዝቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች