በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተመሠረተውና ከ240 በላይ ልዩ ልዩ ዓይነት የዕፀዋት ዝርያዎች ያሉት የጉለሌ ዕፀዋት ማዕከል ከታኅሣሥ የመጀመርያ ሳምንት አንስቶ ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን የማዕከሉ ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡
መስከረም 6 ቀን 2010 ዓ.ም. የተካሄደውና የማዕከሉ ስትራቴጂክ ፕላን የተገመገመበትን ዐውደ ጥናት አስመልክተው ዳይሬክተሩ ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፈሰር) እንደገለጹት፣ ማዕከሉ በዕፀዋት ዙሪያ ምርምር የሚካሄድበትና የዕፀዋት ጥበቃ የሚደረግበት፣ ትምህርት የሚሰጥበትና የአዲስ አበባ ሕዝብ ንፁህ አየር የሚተነፍስበት ይሆናል፡፡
ይህን መሰል አገልግሎት የሚሰጠው ማዕከል ጠቅላላ ይዞታ 705 ሔክታር መሬት ሲሆን፣ በአብዛኛው ከውጭ በመጣው ባህር ዛፍ የተሸፈነ ነው፡፡ ሆኖም የውጭ አገር በቀል የሆኑ ዕፀዋት አገር በቀል በሆኑት ዝግባ፣ ወይራ፣ ጽድና ሌሎችም በመተካት ላይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የአየር ፀባይም በአብዛኛው ተስማሚነቱ ለመጤዎቹ ዕፀዋት ሳይሆን አገር ውስጥ በተፈጥሮ ለሚበቅሉት በመሆኑ ለዚህ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
ከተቋቋመ አሥር ዓመት የሆነው የጉለሌ ዕፀዋትን ማዕከል ከ250 ዓመት በላይ ልምድ ካላቸው ከለንደንና ከቺካጎ ቦታኒክ ጋርደን ማዕከላት ትምህርት ለመቅሰምና የዕውቀት ሽግግር የማድረግ ሥራ እንደሚኖረውም ፕሮፌሰር ሰብስቤ ተናግረዋል፡፡
በማዕከሉ ቅጥር ግቢ የሚበቅሉ ዕፀዋትን ለሕዝብ የማቅረብና ሌሎችም ከተሞች ተመሳሳይ የዕፀዋት ማዕከል እንዲኖራቸው ማድረግ ቀጣይ ሥራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የለንደን ቦታኒክ ጋርደን ዳይሬክተር ሚስተር ሪቻርጅ ዴቪርሊ፣ የጉለሌ ዕፀዋት ማዕከል የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የጥበቃ ማማዎችና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ መሠራታቸው ለአገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሆልቲካልቸራሊስቶችንና ሳይንቲስቶችን ለማሠልጠን፤ የተማሪዎች ልምድ ልውውጥ ለማካሄድ፣ ዕውቀትና ተሞክሮን ለማካፈል ድርጅታቸው ዝግጁ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አበበ ድንቁ (ፕሮፌሰር)፣ የጉለሌ ዕፀዋት ማዕከል ዓላማውን ለማሳካት በርካታ ተግባራትን እንዳከናወነ፣ ከእነዚህም መካከል የኮብልስቶን መንገድ መሥራት፣ የማዕከሉን ይዞታ በግንብ መከለል፣ የጥበቃ ማማ ማቋቋምና ካፍቴሪያ መገንባት እንደሚገኝበት አስረድተዋል፡፡፡
‹‹እኔ እስከማውቀው ድረስ ጉለሌ የዕፀዋት ማዕከል አዲስ አበባ ውስጥ ትልቁ ጥብቅ ቦታ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በምርምር፣ በጥበቃ፣ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማት ማስፋፋትና የማዕከሉን የመጨረሻ ዲዛይን በማዘጋጀት ረገድ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ከፍ ያደርገዋል፤›› ብለዋል፡፡