Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

‹‹ሰንደቅ ዓላማው ኢትዮጵያውያንን በሚመጥን ከፍታ ላይ ተውለብልቧል!››

ትኩስ ፅሁፎች

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ 10ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም  በተከበረበት ጊዜ የተናገሩት፡፡ ፕሬዚዳንቱ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት መስክ በአርበኝነት ስሜት መሥራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ የሰንደቅ ዓላማው ቀን የተከበረው ‹‹ራዕይ ሰንቀናል ለላቀ ድል ተነስተናል›› በሚል መሪ ቃል ነው፡፡

******

ተማፅኖ ለአምላክ

ጥፋታቸው የመረረ፣

ጥቃታቸው የከረረ፣

ሺሕ ምንተ-ሺሕ! ኩነኔ፣

በደል ቢፈጽሙ በኔ፣

እባክህ ተዋቸው፤

ምሕረቱን ሰጥተህ፤ በረከቱን አብዛላቸው፡፡

አልተማሩምና ቃልህን፣

አላወቁምና ፍርድህን፣

እባክህ ጌታዬ እነርሱን ማራቸው?

በደሌን አስበህ ቅንጣት እንኳ አትቅጣቸው

  • ደረጀ ትዕዛዙ፣ ‹‹ሳተናው እና ሌሎች. . .›› (የካቲት 2003 ዓ.ም.)

********

አድናቂዎችን ያሳዘነው የፔንግዊን ሕልፈት

ባለፈው ሳምንት ጃፓን ውስጥ በሚገኝ የእንስሳት ማቆያ የሚኖረው የአዕዋፋት ዝርያው ፔንግዊን በ21 ዓመቱ መሞቱ ብዙዎችን ያሳዘነ ዜና ነበር፡፡ ፔንግዊኑ ግራፔ ይባላል፡፡ በጃፓንና በሌሎችም አገሮች ዝነኛ ነበር፡፡ የግራፔ ዝና የናኘው በእንስሳት ማቆያው የአንዲት ልቦለዳዊ ፔንግዊን ቅርፅ ከተሰቀለ በኋላ ባሳየው ባህሪ ነበር፡፡ በፓጃን ታዋቂ የሆነውን ኬሞኖ ፍሬንድስ የተባለ አኒሜሽን ፊልም ለማስተዋወቅ የፊልሙ ዋና ባህሪ የሆነችው ሁሉሉ የተባለች ሬንግዊን ምስል በእንስሳት ማቆያው ይሰቀላል፡፡ ቅርፁ ከተሰቀለበት ዕለት አንስቶ ግራፔ ከቅርፁ አጠገብ አልለይም አለ፡፡ ግራፔ አብዛኛውን ጊዜውን የሁሉሉን ቅርፅ በመመልከት ማሳለፉ ያስገረማቸው የማቆያው ኃላፊዎች የትዊተር አካውንት ከፈቱለት፡፡ ዜናውንም በዓለም አሠራጩ፡፡ ብዙ ጎብኚዎች ግራፔ የሁሉሉን ቅርፅ በተመስጦ ሲመለከት ለማየት ብለው ወደ ጃፓን መጓዝም ጀመሩ፡፡ ግራፔም አድናቂዎችን አፈራ፡፡ ለአኒሜሽን ፊልሙ ማስታወቂያ የተያዘለት ጊዜ ቢጠናቀቅም የሁሉሉ ቅርፅ ከእንስሳት ማቆያው እንዳይነሳም ተወሰነ፡፡ ይህ ዝነኛ ፔንግዊን ባልታወቀ ምክንያት ያረፈው ባለፈው ሳምንት ሲሆን፣ የእንስሳት ማቆያው ኃላፊዎች ሞቱን በትዊተር ገጹ አሳውቀዋል፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ከዓለም ዙሪያ ሐዘናቸውን የገለጹ አድናቂዎቹ በርካቶች ናቸው፡፡ ቶቡ ዙ የተባሉት የማቆያው ኃላፊ፣ ‹‹በሰው ዕድሜ አቆጣጠር 81 ዓመት ኖሮ አልፏል፤›› ሲሉ ነበር ሐዘናቸውን የገለጹት፡፡

አድናቂዎችን ያሳዘነው የፔንግዊን ሕልፈት

******

12 ሺሕ ዶላር ያወጣው የሲጋራ ቁራጭ

ሲጋራ በየትኛው አገር ለገበያ የሚቀርብበትን ዋጋ የሚገዳደር ክፍያ የተሰማው ባለፈው ሳምንት ቦስተን ውስጥ ነበር፡፡ 12 ሺሕ ዶላር ለሲጋራ ቁራጭ ማን ይከፍላል? ብለው ብዙዎች ግራ ሊጋቡ ይችላሉ፡፡ ቦስተን ውስጥ የኦንላይን ጨረታ መውጣቱ ሲገለጽ፣ ለሽያጭ የቀረበው ምን እንደሆነ ለማወቅ ብዙዎች ጓጉተው ነበር፡፡ ግማሹ የተጨሰ ቁራሽ ሲጋራ መሆኑን ሲያውቁ ግን ተደነቁ፡፡ ጨረታውን ያወጡት ሰዎች ሲጋራው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዊንስተን ቸርችል እ.ኤ.አ. በ1947 ወደ ፓሪስ ባደረጉት ጉዞ ወቅት ያጨሱት መሆኑን ሲያሳውቁ ግን የዋጋ ድርድሩ ጦፈ፡፡ አሥር ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው ሲጋራ፣ ዊንስተን ቸርችል ለ ቦርጌት አየር ማረፊያ ውስጥ ያጨሱት ነው፡፡ ካፕቴን ዊልያም አለን ተርነር የተባለ አብራሪ የሲጋራውን ቁራጭ አስቀምጦ ከዓመታት በኋላ ለገበያ ቀርቧል፡፡ ሲጋራው የኩባ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስም ይገኝበታል፡፡ በወቅቱ ሲጋራውን ሲያጨሱ የሚያሳይ ፎቶም በመገናኛ ብዙኃን እየተሠራጨ ነው፡፡ አሶሽየትድ ፕረስ እንደዘገበው፣ የሲጋራውን ቁራሽ በ12 ሺሕ ዶላር ያሸነፉት ግለሰብ ማንነት እስካሁን ባይታወቅም፣ የፍሎሪዳ ነዋሪ መሆናቸው ተደርሶበታል፡፡

12 ሺሕ ዶላር ያወጣው የሲጋራ ቁራጭ

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች