Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኢትዮጵያው ኤሌክትሮኒክ በዓለም መድረክ

የኢትዮጵያው ኤሌክትሮኒክ በዓለም መድረክ

ቀን:

መስቀል  ፍላወር አካባቢ  ከሚገኘው  ራዕይ ሪከርድስ የሙዚቃ ስቱዲዮ የተለያዩ ብሔረሰቦች ባህላዊ ሙዚቃ  ከዘመነኛው ኤሌክትሮኒክ ዳንስ  ሚዩዚክ  ጋር ተዋህዶ ይንቆረቆራል፡፡  የጋሞ፣ የኦሮሞና ሌሎችም ባህላዊ ሙዚቃ ምቶችን ተከትሎ በኮምፒዩተር የተቀናበረው ዜማ ጆሮ ይስባል፡፡ የምቱን ፍጥነት እየተከተለ አንገቱን  የሚያወዛውዘው ዲጄና ፐሮዲውሰር ሮፍናን ኑሪ (ሮፊ) ‹‹ ነፀብራቅ ›› በሚል ከሁለት ወራት በኋላ በሚለቀው  አልበም  ከሚካተቱ  ዘፈኖች መካከል ጥቂቱን አስደመጠን፡፡ አገርኛውን  የሙዚቃ ስልት ተመርኩዞ ያቀነባበራቸው እነዚህ ኤሌክትሮኒክ  ዘፈኖች በቅርቡ በተካሔደ ዓለም  አቀፍ የኤሌክትሮኒክ  ሙዚቃ  መድረክ ተካፋይ  እንዲሆንም አስችሎታል፡፡

  የ27 ዓመቱ ወጣት ሙዚቀኛ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ አንስቶ ልቡ ወደ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ እንደሚያዘነብል ይናገራል፡፡ እምብዛም ያልተለመደውን የሙዚቃ  ስልት ሲፈጥር፣ ስቱዲዮ ውስጥ ሆኖ በሶፍትዌር ሙዚቃ ከማቀናበር  በተጨማሪ መድረክ ላይ ዲጄ የማድረግ ሙያንም  አጣምሮባታል፡፡

ታዳጊ ሳለ፣ ትምህርት ቤት ውስጥ ጠረጴዛ  እየመታ  ተማሪዎችን ዘና ያደርግ ነበር፡፡ አብላጫውን የወጣትነቱን ክፍል ያሳለፈው በመዚቃ ውስጥ ሲሆን፣ የዚህ ዘመን ትውልድ  ውጤት የሆነውን ኤሌክትሮኒክ  ሙዚቃ ከኢትዮጵያዊ ቅኝት ጋር ለማዋሀድ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ቅኝቶቹን ሲያጠናና  ከኤሌክትሮኒክ  ሙዚቃ ጋር  በማዋሀድ ሲቀምር ያለፉትን አምስት ዓመታት አሳልፎም የመጀመሪያ አልበሙን አጠናቋል፡፡  በአልበሙ የአምስት  ብሔረሰቦች ባህላዊ ሙዚቃዎች ከኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ጋር ተዋህደው  ሲቀርቡ፣ የተቀሩት በኢትዮጵያ ቋንዎች የተሠሩ ሀውስ  ሙዚቃዎች  ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ያደግንበት ባህል ውስጥ ካሉ እሴቶች መካከል ከሙዚቃው ባሻገር የንግግር ዘዬው አልያም ሌሎችም እሴቶችን ከኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ጋር በማዋሃድ ስሠራ ቆይቻለሁ፤›› ይላል፡፡ አልበሙን ለመልቀቅ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ነበር በሜዲትራኒያን ባህር አካባቢ በምትገኘው የስፔኗ ደሴት ኢቢዛ በተዘጋጀው የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ መድረክ የመሳተፍ ዕድል ያገኘው፡፡ እንደ ሙዚቃ መዲና በምትቆጠረው የስፔኗ ኢቢዛ  መገኘት በሮፍናን የሙዚቃ ስልት ላሉ  ሙያተኞች ታላቅ ድል ነው፡፡

ደቡብ አፍሪካዊው ዴጂና ፕሮዲውሰር ብላክ ኮፊ የወንዶች ውበት መጠበቂያ ከሚያመርተው አክስ ጋር በመተባበር አክስኢቢዛ የተሰኘ የሙዚቃ መሰናዶ ያዘጋጃል፡፡ በመድረኩ በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ስመ ጥር የሆኑ ሙዚቀኞችንም ይጋብዛል፡፡ ዘንድሮ ከአህጉረ አፍሪካ ከመረጣቸው ሙዚቀኞች መካከል ከትውልድ አገሩ ደቡብ አፍሪካ፣ ከናይጄሪያና ከዛምቢያ የተውጣጡት ይገኙበታል፡፡ በብላክ ኮፊ ምርጫ ሮፍናንም በዝግጅቱ ያካተተ ሲሆን፣ በአክስአቢዛ ሥራዎቹን ማስደመጥ ችሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት መርሐ ግብሩን አጠናቆም ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል፡፡

‹‹መድረኩን ማግኘት ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ብላክ ኮፊን ጨምሮ ለወደፊት በሙያው ውስጥ በቢዝነስ ሊረዱኝ የሚችሉ ሰዎችን አውቄበታለሁ፤›› ይላል፡፡ መድረኩን በሚያዘጋጁት የኤሌክትሮኒክ ሙዚቀኞችና በሌሎችም ታዋቂ ሙዚቀኞች ፊት ሙዚቃውን በማቅረቡ ደስተኛ ነው፡፡ በሜዴትራኒያን ባህር ላይ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቀኞችን ሙዚቃ ማዳመጥ የማይረሳ ትውስታ ጥሎበትም አልፏል፡፡ ‹‹የአገራችንን ሰንደቅ ዓላማ ሰቅለው አስደስተውኛል፡፡ የኛን የመሰለ የሙዚቃ ቅኝት ፣ የኛን የመሰለ የሙዚቃ መሣሪያም ስለሌለ ከሌሎቹ የተለየ ሙዚቃ አስደምጫለሁ፤›› ሲል ተሞክሮውን ይገልጻል፡፡

ኢቢዛ መጠነኛ የባህር ዳርቻ ብትሆንም የተለያየ አገር ሙዚቀኞች ሥራቸውን እንዲያቀርቡ ዕድል በመስጠቷ የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ መሆን ችላለች፡፡ ‹‹ሙዚቃና ጥበብ ባጠቃላይ የሚገባውን ክብር አግኘቶ ተመልክቻለሁ፤›› የሚለው ሮፍናን፣ በኢትዮጵያም ሙዚቃ አሁን ካለው የተሻለ ቦታ ቢሰጠው የቱሪዝሙ የጀርባ አጥንት እንደሚሆን ያምናል፡፡ እንደ ምሳሌ የሚጠቅሰው ኢትዮጵያ በሬጌ ሙዚቃ ያላትን ዝና ነው፡፡ የሬጌ ሙዚቀኞች በዘፈኖቻቸው ኢትዮጵያን እንደማወደሳቸው፣ ወደ አገሪቱ መጥተው እንዲዘፍኑ መጥተው በመጋበዝ  ጎብኚዎች እንዲከተሏቸው ማድረግ እንደሚቻል ይገልጻል፡፡

‹‹ስሜቴን የማንፀባርቅበት ዘዬ ነው፤›› የሚለው ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ፣ በዚህ ዘመን ትውልድ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩ የሙዚቃ ስልቶች በግባር ቀደምነት ይጠቀሳል፡፡ ስልቱን በመከተል ውስጥ ከኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝት ጋር የሚዋሃድበትን ነጥብ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብሎ፣ የጃዝ ሙዚቃ ተፅዕኖ ቢያርፍባቸውም የኢትዮጵያን ድምፅ ማስተጋባት የቻሉ የ60ዎቹና የ70 ዎቹን ሙዚቃም ያጣቅሳል፡፡

የሚያደንቀው ሙዚቀኛ ሙላቱ አስታጥቄ ኢትዮ ጃዝን መፍጠር እንደቻለው ሁሉ፣ ኢትዮጵያዊ ቀለም ያለው ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃን ማስተዋወቅ እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡ ለዚህም በአልበሙ ዝግጅት ወቅት በርካታ ባህላዊ ሙዚቀኞች ያሉበት ቦታ ድረስ ሄዶ ስለሙዚቃቸው ካጠና በኋላ በአልበሙ እንዳካተታቸው ያክላል፡፡ የሙዚቃዎቹን ቱባ ይዘት ከኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ጋርም አዋህዷል፡፡ ‹‹ዓለምን የምመለከትበት መንገድ ነፀብራቅ ናቸው፤›› ሲልም ሥራዎቹን ይገልጻል፡፡ አልበሙ ለአድማጭ ጆሮ ከመብቃቱ በፊት፣ ስመጥር ከሆኑ የኤሌክትሮኒክስ ሙዚቀኞቹ ቶም ስዎንና ክዌንቲኖ ጋር በጥምረት ‹‹ቢራቢሮ›› የተሰኘ ኮንሰርት ጥቅምት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ያቀርባል፡፡

የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ በገነነባቸው የምዕራቡ ዓለም አገሮች ስልቱ ካለው ተደማጭነት አንፃር በአገራችን ብዙ እንደሚቀረው እሙን ነው፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያዊ ኤሌክትሮኒክ በሚል የኢትዮጵያንና ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃን በማዋሃድ የሚሠሩ ወጣት ሙዚቀኞች አሉ፡፡ ስልቱ ዘመነኛ የሙዚቃ ንቅናቄ እንደመሆኑ፣ የበርካታ ወጣቶችን ቀልብ መግዛቱም አልቀረም፡፡ ‹‹ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃን ይዞ የራስ ቀለም ያለው ሙዚቃ መሥራት ይቻላል፡፡ ስልቱ ለተለያየ ዓይነት ሙዚቃዊ ምርምር የተመቸም ነው፤›› ሲል ሮፍራን ይገልጻል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ውሰጥ ያለው እንቅስቃሴ የተዋቀረ እስከሚሆንና ቱባውን ባህል እስከሚያንፀባርቅ ‹‹የኢትዮጵያ›› ብሎ ለመሰየም እንደሚያስቸግር ይናገራል፡፡ የስልቱ ኢትዮጵያዊ ገጽታ በዓለም፣ የሙዚቃ መድረክ እውቅና ማግኘት ያስፈልገዋልም ይላል፡፡ ባለንበት የዲጂታል ዓለም መረጃን በፍጥነት መለዋወጥ መቻሉ የሙዚቃ ሥራዎች በቀላሉ ኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲደርሱ መንገድ ከፍቷል፡፡ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃም የኢትዮጵያን ቅኝት እስካካተተ በቀላሉ በኢትዮጵያና በዓለምም ለመሰራጨት ዕድል እንደሚኖረው ይገልጻል፡፡

በዚህ ዘመን ብዙ ሙዚቀኞች በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ መሳባቸው ለዘርፉ ዕድገት አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ሙዚቀኛው ያስረዳል፡፡ ሙዚቀኞቹ አድማጭ ጆሮ እንዲሰጣቸው በሙዚቃቸው የማሳመን ብቃት እስካላቸው ድረስ ስልቱ የበለጠ ተደማጭነት እንሚያገኝም እምነቱ ነው፡፡

ሙዚቀኛው እንደሚለው፣ በአገሪቱ የሚሠራው ሙዚቃ ከኢትዮጵያ ባለፈ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ መሥራት የግድ ይላል፡፡ ‹‹ሥራችን እዚህ ስለተወደደ ብቻ በቂ ነው ሳንል ግባችንን ማስፋት አለብን፤›› ይላል፡፡ የየትኛውም አገር አድማጭ ሊሰማውና ሊወደው የሚችል ሙዚቃ መፍጠር እንደሚያሻም ያስረግጣል፡፡ እሱ እንደተሳተፈበት አክስአቢዛ ዓይነት ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ መገኘት ሲቻል ሙዚቃውን ማስተዋወቅና ከሌሎች አገሮች ባለሙያዎች ጋር አብሮ መሥራት ያለውን ሚናም ሳይጠቅስ አያልፍም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሙዚቃ መሥራትን ፈታኝ ከሚያደርጉት አንዱ ሙያተኞች ሙዚቃ ከመቀመር ባሻገር ስፖንሰር ፈልጎ የማሳተምም ጫና ይወድቅባቸዋል፡፡ እርስ በርስ በሙያው ተሳስሮ መሥራትም አይስተዋልም፡፡ ‹‹ጥሩ ተቀባይነት ያለው አንጋፋ ሙዚቀኛና ወጣቱ መካከል ትስስር ቢፈጠር፣ ሁሉንም ዓይነት አድማጭ መድረስ ይቻላል፤›› ይላል ሙዚቀኛው፡፡

በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ትልቁን ቦታ የሚይዙት ዲጄዎችና ፕሮውዲሰሮች ናቸው፡፡ ከድምፃውያን በስተጀርባ ለሚሠሩ ሙዚቀኞች ብዙም ቦታ በማይሰጥበት የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ፣ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ፈር እንደሚቀድ ያምናል፡፡ ተገቢውን ክብር የተነፈገው የዲጄነት ሙያ ቦታ እንዲሰጠው የሚረዳ መንገድም ነው ይላል፡፡ ምክንያቱም ኤሌክትሮኒክ ሙዚቀኞች ከማቀናበር ጎን ለጎን ሙዚቃዎቻቸውን በተለያዩ መድረኮች በዲጄነት ስለሚያስደምጡ ነው፡፡

እንደ ብላክ ኮፊ ባለ እውቅ የኤሌክትሮኒክ ሙዚቀኛ መመረጡ በሙያው ትልቅ ቦታ እንደሚያሰጠው ገልጾ፣ ‹‹በሱ መመረጥና ብዙ በሮች የሚከፍት ዕድል ነው፡፡ የቀሰምኩት ልምድ ለሙዚቃዎቼ ግብአት ይሆናል፤›› ሲልም ያስረዳል፡፡ መሰል ትላልቅ ዕድሎች በሱ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሙዚቀኞችም ተደግመው እንደሚያይም ያደርጋል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...