Wednesday, February 28, 2024

መቋጫ ያጣው የሦስቱ አገሮች ድርድርና የህዳሴ ግድብ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከጣለች ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የግንባታ ሒደቱም 60 በመቶ እንደደረሰ ተነግሯል፡፡ የህዳሴ ግድቡን የመሠረት ድንጋይ በተጣለ ማግሥት ግብፅ ግድቡ ዕውን እንዳይሆን ሙሉ አቅሟን ተጠቅማ ስትንቀሳቀስ ነበር፡፡ በዚህም ስኬታማ ሆና ዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ የሚውል ገንዘብ እንዳያበድሩ አድርጋለች፡፡

የተፋሰሱ አገሮች በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም የቆመውን የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የተፋሰሱ አገሮች እንዲፈርሙ ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ስድስት አገሮች የፈረሙ ሲሆን፣ ሦስት አገሮች ደግሞ አፅድቀውታል፡፡

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመጡት አቶ ዘሪሁን አበበ ባለፈው ሳምንት የህዳሴ ግድቡ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያ ሆቴል የ2010 ዓ.ም. ዕቅድን በተመለከተ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ምክክር እንደተናገሩት፣ ግብፅና ሱዳን እስካሁን ስምምነቱን ተቃውመውታል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከ122 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የከርሰ ምድር ውኃ እንዳላት ይነገራል፡፡ ከዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው ወደ ውጭ እንደሚፈስም ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ከ122 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የውኃ መጠን ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ወደ ዓባይ ተፋሰስ ይገባል፡፡

አቶ ዘሪሁን እንዳሉት ከ1980ዎቹ ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የመጀመሪያው ቀደም ሲል የተሠሩ ጥናቶችን በመፈተሽና በመከለስ የውስጥ አቅምን ማጠናከር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከግርጌና ከላይኛው ተፋሰስ አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በሒደትም አገሮች ወደ ናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እንደመጡ አስረድተዋል፡፡ በናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት አንቀጽ 44 የዓባይን ውኃ የተፋሰስ አገሮች ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ ይህም ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መንገድ እንደሚፈጸም አስቀምጧል፡፡ በስምምነቱ የተቀመጠው ይህ ሆኖ ሳለ በግብፅ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ‹ጉዳት ላለማድረስ› ስምምነት ደርሳለች እያሉ እንደሚጽፉ ጠቅሰዋል፡፡ በግብፅ ሕዝብ የሰረፀው ይህ አስተሳሰብ ትክክል እንዳልሆነ የጠቆሙት አቶ ዘሪሁን፣ በስምምነቱ መሠረት ‹‹ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ›› እንጂ ‹‹ጉዳት ያለማድረስ›› የሚል እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን ድረስም የግብፅ ሚዲያዎች በካርቱን ሥዕሎችን የተሳሳቱ መልዕክቶችንና እንደሚያስተላልፉ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያና ግብፅ በዓባይ ወንዝ ለረዥም ዓመታት ሲነታረኩ ከቆዩ በኋላ፣ በአሁኑ ወቅት በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር ላይ ናቸው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማያደርስ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ከመቆየቷም በላይ፣ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ግድቡ በታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ጉልህ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑን እንዲያጠና በመፍቀዷ በአሁኑ ወቅት በመነጋገር ላይ ናቸው፡፡

ሦስቱ አገሮች በደረሱት ስምምነት መሠረት ሁለት የፈረንሣይ ኩባንያዎችን በመቅጠር ግድቡ ስለሚኖረው ተፅዕኖ ጥናት እንዲያደርጉ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር አጋማሽ ላይ የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሱዳን ተገናኝተው ‹‹ቢአርኤል›› እና ‹‹አርቴል›› የተባሉ የፈረንሣይ አጥኝ ኩባንያዎች ያቀረቡትን ሪፖርት አዳምጠዋል፡፡

የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ ኮሚቴ ዋና ዓላማ ዓለም አቀፍ የአጥኝዎች ቡድን በየጊዜው የሚያቀርበውን ሪፖርት በማዳመጥ የጋራ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማድረግ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የሦስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴው ካርቱም ላይ ከወራት በፊት አድርጎት በነበረው ስብሰባ ወዝግቦች ተነስተው እንደነበር መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ የዚህ አካል የሆነው ቀጣይ ስብሰባ ረቡዕ ጥቅምት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

የግብፅና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ከኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ጋር እንደተነጋገሩ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ስለሺ ከሱዳንና ከግብፅ አቻዎቻቸውን ሙአተዝ ሙሳና መሐመድ አብደል አቲ ጋር ተገናኝተው ሰኞ ዕለት ወደ ህዳሴ ግድቡ አቅንተዋል፡፡ የህዳሴው ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ስመኘው በቀለ (ኢንጂነር) ግድቡ አሁን ስለደረሰበት ደረጃና አጠቃላይ ገጽታ በተመለከተ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

ከዚህ በፊት የሁለቱም አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተናጠል ግድቡን እንደጎበኙ የሚታወቅ ሲሆን፣ የሦስቱም አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአንድ ላይ ሆነው ሲጎበኙ ይኼ የመጀመሪያው ነው፡፡

የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ የህዳሴ ግድቡን ጉብኝት ተከትሎ የሦስትዮሽ የሚኒስትሮች ስብሰባ እንደሚያካሂዱም ታውቋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚነስቴር የቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳሠፈረው፣ በስብስባው ላይ ሚኒስትሮቹ ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ፣ በተለይም የዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲጠኑ ብሎ በሰጠው ምክረ ሐሳብ መሠረት ሁለቱን ጥናቶች በተመለከተ ውይይት ያደርጋሉ፡፡

ሁለቱ ጥናቶች የሚደረጉት በሦስቱ አገሮችና በአማካሪ ድርጅቶች መካከል በተደረገው ስምምነትና የመሪዎች መግለጫ ስምምነት መሠረት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ዓለም አቀፍ የአጥኝዎች ቡድን የሚያቀርበውን ሪፖርት ከማዳመጥ  ባሻገር ሦስቱ አገሮች በዚህ ላይ የሚያደርጉት ውይይትና ድርድር ሊኖር እንደሚችል መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ ስብሰባ የመጨረሻው እንዲሆን ኢትዮጵያ ፍላጎት አላት፡፡ ከዚህ በፊት በካይሮና በካርቱም በተካሄዱ የሦስትዮሽ ስብሰባዎች ላይ ብዙ ውዝግቦችና ክርክሮች እንደነበሩ ጠቅሰው፣ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ስብሰባ ላይ ሙሉ ስምምነት ላይ ይደርሳል የሚል እምነት እንዳለ አስረድተዋል፡፡

ግብፅ ከዚህ በፊት ተካሂደው በነበሩ ውይይቶች ላይ ስለግድቡ ውኃ አሞላል ጥያቄ አንስታ ከኢትዮጵያ አጥጋቢ ምላሽ እንዳላገኘች ስታወሳ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ አሁን  በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ስብሰባ  የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ውይይት ከመግባታቸው በፊት ግድቡን እንዲጎበኙት የመደረጉ ሚስጥርም ይህ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በተለይ ከግብፅ የሚነሳውን የግድቡን የውኃ አሞላል ጥያቄ ለመመለስ ሲባል ይህ ጉብኝት በኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ መሠረት መካሄዱን ገልጸዋል፡፡ ጉብኝቱ ሁለቱን አገሮች ግልጽ አቋምና እምነት እንዲኖራቸው ያስችላል ተብሎ እንደሚታመን አክለዋል፡፡

እስካሁን ድረሰ ከግብፅ ሕዝብና መንግሥት የህዳሴ ግድቡን ግንባታ በተመለከተ የተሰጠ አረንጓዴ ካርድ ባይኖርም፣ በጉባ 24 ሰዓት ሥራ እንዳለ የህዳሴ ግደቡ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ ባለፈው ሳምንት መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የግድቡ ግንባታ ቆሟል ተብሎ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተወራ ቢሆንም፣ እሳቸው ግን ለሰኮንድ ያህል እንዳልቆመና ወደፊትም ሳይጠናቀቅ እንደማይቆም ተናግረዋል፡፡

አቶ ዘሪሁን ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ውስጣዊ አቅሟን ስታጎለበት መቆየቷን ተናግረዋል፡፡ የውስጣዊ አቅሟን ካጎለበተች ወዲህ ደግሞ አገሮች በተለይም ግብፅና ሱዳን ወደ ድርድሩ እንዲመጡ ስትጥር መቆየቷን ገልጸዋል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት ይስተዋላል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልል ውስጥ የነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ አገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህ ሳቢያም መንግሥት በአገሪቷ ለአሥር ወራት የዘለቀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ቆይቷል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ ወዲህ በጣት የሚቆጠሩ ወራት ብቻ ቢቆጠሩም፣ አሁንም በአገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች የተቃውሞ ሠልፎች እየተካሄዱ ነው፡፡

ከሁለት ወራት በፊት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሚኖሩ ዜጎች መካከል በተቀሰቀሰው ግችት በርካቶች ሞተዋል፡፡ በሺህ የሚቆጠሩት ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ይህን ግጭት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ  የተቃውሞ ሠልፎች እየተደረጉ ሰንብቷል፡፡

ብዙዎች የዚህ ግድቡ ዕውን መሆን በአገሪቱ ሰላምና ውስጣዊ ደኅንነት ላይ የሚመሠረት እንደሆነ ሲናገሩ ቢሰማም፣ አሁን አሁን በአገሪቱ እየተከሰተ ያለው የፀጥታ ችግር ለህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ሥጋት ሊሆን ይችላል ሲባልም ተደምጧል፡፡

ይህን መሰል ችግር በኢትዮጵያ ተስፋፍቶ እንዲቀጥል ግብፅ ምኞት እንዳላት ሲነገር ነበር፡፡ አሁን በግድቡ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር እየተደራደረችና እስካሁን ድረስ ከሞላ ጎደል ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ቢገኝም፣ ይህን መሰል ግጭትና  አገራዊ ተቃውሞ አጥብቃ እንደምትፈልግ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ይህ ግድብ ዕውን ሆኖ የተፈለገውን አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ፖለቲካዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ፣ የሚጠናቀቅበት ጊዜ በጉጉት ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል ሱዳን እስካሁን የስምምነት ማዕቀፉን ባትፈርምም፣ በአሁኑ ወቅት በግድቡ ላይ ከግብፅ በተለየ አቋም አላት፡፡

የሁለቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም ሁለት ጉዳይ እንዳለው የግብፁ አህራም ኦንላይን ዘግቧል፡፡ የመጀመሪያው ሚኒስትሮቹ ህዳሴ ግድቡ በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን ደረጃ ለመጎብኘትና የሦስትዮሽ ድርድሩ ላይ ለመሳተፍ ነው የመጡት፡፡

የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከህዳሴው ግድብ ጉብኝታቸው በኋላ ዓለም አቀፍ የአጥኝዎች ቡድን የሚያቀርቡትን ሪፖርት ከማዳመጥ ባሻገር፣ ግድቡ ውኃ አሞላል ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በዝርዝር እንደሚመክሩ በሁለተኛ ደረጃ አስቀምጦታል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -