Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሁለት የራዲሰን ብሉ ብራንዶች ገበያውን ሊቀላቀሉ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ በሆቴል ማስተዳደር ሥራ በሚታወቀው ካልሰን ሬዚዶር ግሩፕ ሥር የሚገኙት ራዲሰን ብሉና ፓርክ ኢን ባይ ራዲሰን የተባሉ የሆቴል ብራንዶች በኢትዮጵያ የሚያስተዳድሩትን ሆቴል ወደ አራት ከፍ የሚያደርግላቸውን ሁለት አዳዲስ የኮንትራት ስምምነቶች ፈጸሙ፡፡

የኮንትራት ስምምነቶቹን ካስፈጸመው ከኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት ግሩፕ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ከራዲሰን ብሉ ጋር ስምምነት የፈረመው አንደኛው ኩባንያ በላይን ቢዝነስ ግሩፕ ሥር የሚገኘው አዱላላ ኮንፈረንስና ስፓ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለ አገር በቀል ኩባንያ ነው፡፡ በራዲሰን ብሉና በአዱላላ መካከል የተደረሰው ስምምነት አዱላላ በቢሾፍቱ የሚያስገነባውን ሪዞርት ካጠናቀቀ በኋላ ሙሉ የማስተዳደር ሥራውን ራዲሰን ብሉ እንዲረከብ የሚያስችል ነው፡፡ ሪዞርቱም የራዲሰን ብሉ መስፈርት በሚጠይቀው መሠረት የሚገነባ ይሆናል፡፡

ይህ ሪዞርት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ሲሆን፣ 157 የሚሆኑ ክፍሎች ስምንት መሰብሰቢያ አዳራሾችና ሌሎች አገልግሎቶችን አካትቶ የያዘ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ ሪዞርቱ በሦስት ዓመት ውስጥ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ከኦዚ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ሁለተኛው የኮንትራት ስምምነት የተፈጸመው ፓርክ ኢን ባይ ራዲሰን አዲስ አበባ የሚል ስያሜ ለሚኖረው ሆቴል ነው፡፡ ፓርክ ኢን ባይ ራዲሰን ለማስተዳደር ስምምነት የፈጸመው ኤቲጂ ጆይ ኮንፊክሽነሪ ኢንዱስትሪ ከተባለው ኩባንያ ጋር ነው፡፡ ኤቲጂ የተባለው ይህ አገር በቀል ኩባንያ ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለውን ሆቴል አዲስ አበባ በተለምዶ ቺቺኒያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ‹‹ዮሊ ሕንፃ›› ፊት ለፊት እየገነባ ያለውን ሆቴል እንዲያስተዳድርለት ነው፡፡ ይህ ሆቴል ለመዝናኛና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 160  ክፍሎችን አካቶ የያዘ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የዚህ ሆቴል ግንባታ ከ75 በመቶ በላይ እንደተጠናቀቀ የተገለጸ ሲሆን፣ ቀሪ የማጠናቀቂያ ሥራዎቹን በመጨረስ በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ወደ ሥራ ይገባል ተብሏል፡፡

በካልሰን ሬዚዶር ግሩፕ ሥር ያሉት ሁለቱ ራዲሰኖች ባለፈው ሳምንት ያደረጉዋቸው አዳዲስ ስምምነቶች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስተዳድሩትን ሆቴል ወደ አራት እንደሚያሳድግላቸው የኦዚ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ራዲሰን ብሉ ካዛንቺስ የሚገኘውን ሆቴል በማስተዳደር ላይ ሲሆን፣ በቦሌ መንገድ እየተገነባ ያለውን አዲስ ሆቴልም ለማስተዳደር ከዚህ ቀደም ስምምነት መፈረሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች