- በመጀመርያው ሩብ ዓመት ከ4.1 ቢሊዮን ብር በላይ አገበያቷል
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመስከረም 2010 ዓ.ም. ያካሄደው አጠቃላይ ግብይት በቀዳሚው ወር ከተፈጸመው ግብይት በ400 ሚሊዮን ብር ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፣ ወደ ምርት ገበያው ለግብይት የቀረበውም የምርት መጠን መቀነሱ ተመለከተ፡፡
ምርት ገበያው በመስከረም ወር ማገበያየት የቻለው፣ 1.3 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን 24,892 ቶን ቡና፣ ሰሊጥና የቦሎቄ ምርቶች ነው፡፡ ይህ የግብይት መጠን ግን ካለፈው ወር (ነሐሴ 2009 ዓ.ም.) አገበያይቶት ከነበረው የምርት መጠን አንፃር ሲታይ የመስከረም ወር አንሶ ተገኝቷል፡፡ ምርት ገበያው ባለፈው ነሐሴ ወር 1.7 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው 33,528 ቶን ቡና፣ ሰሊጥና ቦሎቄ አገበያይቶ የነበረ በመሆኑ፣ የመስከረም ወር አጠቃላይ ግብይቱ በገንዘብ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ አንሷል፡፡ በምርት መጠኑ ደግሞ በነሐሴ ወር ከቀረበው በ8,634 ቶን ዝቅ ያለ ሊሆን ችሏል፡፡ የመስከረም ወር ለግብይት የቀረበው አጠቃላይ የምርት መጠን ዝቅ ሊል የቻለው ተገበያዮች ከቀደመው ወር ያነሰ ምርት በማቅረባቸው ነው፡፡
በተለይ ባለፈው ወር በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ምርት ገበያው ቀርቦ የነበረው የቡና መጠን በመስከረም ወር ማነሱ ለአጠቃላይ የግብይት መጠኑ ዝቅ ማለት አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ በመስከረም ወር ለግብይት የቀረበው የቡና መጠን 17,000 ቶን ሲሆን፣ የግብይት መጠኑም 1.14 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ የመስከረም ወር የቡና የግብይት መጠን ከነሐሴ ወር ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ፣ በመጠን ደግሞ በ39,940 ቶን ያነሰ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመስከረም 2010 ዓ.ም. ግብይት አፈጸጸሙ እንደሚያሳየው፣ ከቡና ሌላ 11 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው 705 ቶን ቦሎቄ አገበያይቷል፡፡ በተመሳሳይ 6,970 ቶን የሰሊጥ ምርት በ181 ሚሊዮን ብር አገበያይቷል፡፡ እነዚህም ምርቶች ከቀዳሚዎቹ ሁለት ወራት ያነሰ ግብይት የተፈጸመባቸው ናቸው፡፡
በነሐሴ ወር 303 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው 11,479 ቶን ሰሊጥ፣ በሐምሌ ደግሞ ወር ደግሞ 317 ሚሊዮን ዋጋ ያለው 12,660 ቶን ሰሊጥ ተገበያይቶ ነበር፡፡ የቦሎቄ ግብይት ሲታይም በሐምሌ ወር ለግብይት ቀርቦ የነበረው 1,850 ቶን ሲሆን፣ በነሐሴ ደግሞ 890 ቶን ቀርቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ምርት ገበያው በመስከረም ወር ያገበያየው የምርት መጠን በዚህ ደረጃ ቢያንስም፣ በቀጣይ ወራት ከፍ ሊል የሚችልባቸው ዕድሎች እንዳሉ ግን ተመልክቷል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሦስቱ ወራት (በ2010 ዓ.ም. በመጀመርያው ሩብ የበጀት ዓመት) ከ4.1 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን 85,422 ቶን ቡና፣ ሰሊጥና ቦሎቄ ማገበያየት ችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው የቡና ድርሻ ነው፡፡