- ደህና አደርክ?
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምነው ፊትህ ጠቁሯል?
- እንዴት አይጠቁር?
- ምነው ቁጣ ቁጣ አለህ?
- መሮኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጣፋጭ ነገር ውሰዳ፡፡
- እኛማ አንድ የነበረንን ጣፋጭ ነገር ወሰዳችሁብን፡፡
- የምን ጣፋጭ ነው የወሰድንብህ?
- መቼም እንደ እርስዎ ኬክ ምናምን አልበላ? ስኳራችንን ካጠፋችሁብን ሰነባበታችሁ፡፡
- ስኳር እኮ አይጠቅምም፣ እንደውም ለበርካታ በሽታዎች ያጋልጣል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የሚያሳዝነኝ መጥፎ መሆናችሁ አይደለም፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- አሪፍ መጥፎ እንኳን አይደላችሁም፡፡
- ምን ይዘባርቃል ይኼ?
- ለማንኛውም ያኔ ትግል እንዴት ነበር የገቡት?
- ምን እያልከኝ ነው?
- ማለቴ ለመታገል ያነሳሳዎት ምንድን ነበር?
- ያው ሕዝቡ ተበድሏል፡፡ ተጨቁኗል ብዬ አስብ ነበር፡፡
- እሱ ነበር ምክንያትዎ?
- በወቅቱ የነበረው መንግሥት አፋኝና ጨቋኝ ስለነበር ያንን ሥርዓት ለመጣል ነው የታገልኩት፡፡
- ስለዚህ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ እያሉኝ ነው?
- ወዴት ልትሄድ ነው ደግሞ?
- እኔም ልታገል ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ ጠፋሁ፣ ዋናውን ፀረ ልማት በጉያችን ታቅፈነው ነበር በለኛ?
- ክቡር ሚኒስትር ፀረ ልማት ምናምን እያላችሁ የምታታልሉበት ጊዜ አልፏል፡፡
- የምን ትግል ነው ታዲያ የምታወራው?
- በቃ ትግል ያለበት ቦታ ሄጄ እታገላለሁ፡፡
- እኛ ልማትና ሰላም አስፍነን አገሪቷን በለውጥ ጎዳና እያስጓዝናት ባለንበት ወቅት፣ በጉያችን ሆነህ ጦር ልትሰብቅብን?
- ክቡር ሚኒስትር ዝም ብለው ልማት ልማት አይበሉኝ፡፡
- ከዚህ በላይ ልማት ከየት ይምጣ?
- የለሙት እኮ እርስዎ ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ምን?
- ከእርስዎም በላይ ጓደኛዎና ዘመዶችዎ ናቸው የለሙት፡፡
- አሁን አንተ ምን ጎደለብህ?
- እስቲ የሞላልኝን ይንገሩኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ይኸው እንደ ባለሀብት በቪ8 ከተማው ላይ ትንቀባረራለህ፡፡
- ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት አሉ፡፡
- ምን እያልከኝ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ከፎቅ ፎቅ ሲዘሉ፣ እኔ እኮ ከመኪና መኪና ነው የተገላበጥኩት?
- እሱንስ ማን አየበት?
- አሁን ግን መሮኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ሆነህ?
- ይኸው በጠራራ ፀሐይ እኮ ነው የተሰረቅነው፡፡
- ቤትህ ሌባ ገባ እንዴ?
- ቢገባስ ከእኔ ውጪ ምን ያገኛል ብለው ነው?
- ታዲያ ማን ነው የሰረቀህ?
- መንግሥት ነዋ የሰረቀኝ፡፡
- እንዴት አድርጎ?
- ባለፈው ሳምንት የነበረኝ 100 ብር በዚህ ሳምንት 85 ብር ሆኗል፡፡ ከዚህ በላይ ስርቆት አለ እንዴ?
- የብር ተመን ስለመቀነሱ ነው የምታወራው?
- እህሳ ክቡር ሚኒስትር?
- ለዚህ እኮ ነው ትንሽም ቢሆን አንብብ የምልህ፡፡ ሌላው ቢቀር ሳወራ ብትሰማኝ እንኳን ትንሽ ዕውቀት ትገበይ ነበር፡፡
- የብር የመግዛት አቅም ተዳክሟል ማለቴ ነው ዕውቀት የለህም ያስባለኝ?
- በሚገባ እንጂ፡፡
- እስቲ እርስዎ ያለዎትን ዕውቀት ያስጨብጡኝ?
- የብር ተመን እንዲቀንስ የተደረገው እኮ ለአገሪቷ ዕድገት ታስቦ ነው፡፡
- ምን?
- ስማ ተመኑ በመቀነሱ ምክንያት የአገሪቷ ኤክስፖርት ይጨምራል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የሚጨምረው የአገሪቷ ኤክስፖርት ሳይሆን. . .
- እ. . .
- የእርስዎ ኪስ ነው!
[ክቡር ሚኒስትሩ ለምሳ ከቢሮ ሲወጡ ጸሐፊያቸውን አገኟት]
- ምንድነው የያዝሽው ደግሞ?
- የምሳ ዕቃ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ትናትና ቤትሽ ድግስ ነበር እንዴ?
- የምን ድግስ?
- ማለቴ በጣም ልማታዊ ስለሆንሽ ለባንዲራ ቀን ደግሰሽ ከሆነ ብዬ ነው፡፡
- ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ አሉ?
- ምን እያልሽ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር በአሁኑ ወቅት እንኳን ልደግስ፣ ድግስ የሚጠራ
ዘመድ ካገኘሁም ዕድለኛ ነኝ፡፡ - ሰው ድግስ መደገስ ትቷል እያልሽኝ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር በቀን ሦስቴ መብላት ራሱ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል ስልዎት?
- ዝም ብለሽ አታማሪ ባክሽ?
- ከዚህ በላይ ምን እስኪመጣ ልጠብቅ ታዲያ?
- ምን መጥቶብሽ ነው እንደዚህ የምታማርሪው?
- ትናንትና አስቤዛ ልገዛ ወጥቼ ነበር፡፡
- እሺ?
- በቅርቡ በችጋር እንደምመታ ነው የተረዳሁት፡፡
- እንዴት?
- ክቡር ሚኒስትር አንድ ፌስታል የሚሞላ ነገር መግዛት አልቻልኩም፡፡
- ጨምረሽ አትገዥም ነበር?
- ከየት አምጥቼ ክቡር ሚኒስትር?
- በፊት ከየት ነበር የምታመጪው?
- ገንዘቡን እኮ ዓረፋ አደረጋችሁት፡፡
- ለምንድነው ዓረፋ የሆነው?
- ገበያው እኮ ተበጥብጧል፡፡
- ማን ነው የበጠበጠው?
- መንግሥት ነዋ፡፡
- ምን አድርጎ ነው የበጠበጠው?
- ይኸው የብር የመግዛት አቅም ቀንሷል ተብሎ ሁሉም ዋጋ ላይ ጭማሪ ተደርጓል፡፡
- ምን?
- ክቡር ሚኒስትር በፊት ይዤ በምወጣው ብር ሦስትም አራትም ፌስታል እገዛ ነበር፡፡
- እሺ፡፡
- አሁን ግን አንድ ፌስታል እንኳን መግዛት አልቻልኩም፡፡
- ማን ጨምሩ አላቸው?
- የሚገርመው እኮ ከዶላር ጋር ግንኙነት የሌላቸው ነገሮች ራሳቸው ጨምረዋል፡፡
- ለምሳሌ?
- ከታክሲ ቤት ድረስ ለሚሸከምልኝ ልጅ የተለመደውን ስሰጠው አልቀበልም አለኝ፡፡
- ለምን ተብሎ?
- ዶላር ጨምሯል ብሎ ጨምሪ አለኝ፡፡
- ይኼ እንዳይሆን እኮ አስፈላጊው ጥናት ተደርጎ ነበር፡፡
- የምን ጥናት?
- በዶላር ጭማሪ ምክንያት ዕቃ እንዳይንር ነዋ፡፡
- የማይገናኙ ነገሮች ራሳቸው እየጨመሩ ናቸው ስልዎት?
- መንግሥት እኮ አስፈላጊውን ቁጥጥር አደርጋለሁ ብሏል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የሸማቾችን ጥቅም አስጠብቃለሁ የሚለው ተቋም ምን እንደሚመስለኝ ያውቃሉ?
- ምን?
- ጥርስ የሌለው አንበሳ!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
- ክቡር ሚኒስትር ይኼን ደብዳቤ ይዩት፡፡
- የምን ደብዳቤ ነው?
- መጀመሪያ ይዩትና ምላሽዎትን ይሰጡኛል፡፡
- ከውጭ አገር ግብዣ ተላከልኝ እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር ደብዳቤውን የጻፍኩት እኔ ነኝ፡፡
- ባለፈው አዘጋጅ ያልኩህን ሪፖርት አዘጋጀህ እንዴ?
- ኧረ ለየት ያለ ጉዳይ ነው፡፡
- ለየት ያለ ጉዳይ ስትል?
- የሥራ መልቀቂያ ነው፡፡
- ምን?
- ክቡር ሚኒስትር ከዚህ በላይ በዚህ ሥራ ላይ መቆየት አልፈልግም፡፡
- ምን ሆንኩ ብለህ ነው የምትለቀው?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ አሁን የምፈልገው መልቀቂያዬን እንዲቀበሉኝ ነው፡፡
- አንተ ስትፈልግ እኮ አይደለም ከዚህ ሥራ የምትለቀው?
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የፓርቲያችንን ፖሊሲ ረሳኸው እንዴ?
- የምን ፖሊሲ ነው?
- ፓርቲው ጥበቃ አድርጎ ቢሾምህ እንኳን መሥራት አለብህ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከዚህ በኋላ በዚህ ኃላፊነት መቀጠል የማልችልበት በርካታ ምክንያቶች አሉኝ፡፡
- ምን ዓይነት ምክንያቶች?
- የማያቸው ነገሮች ሁሉ ደስ እያሉኝ አይደለም፡፡
- ምን ማለት ነው?
- የሕዝቡን ጥያቄ በተገቢው መሠረት ምላሽ መስጠት አልቻልንም፡፡
- የምን ጥያቄ ነው?
- በቃ አገሪቷ ላይ ሙሰኛ በዝቷል፡፡
- ሙሰኛ በዝቷል ነው ያልከኝ?
- ታዲያ ክቡር ሚኒስትር የዚህን የሙስና ጉዳይ ብንለው ብንለው ሊጠራ አልቻለም፡፡
- ዋናው ሙሰኛ አንተ አይደለህ እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር አይሳሳቱ፡፡
- እንዴት?
- በኪራይ ሰብሳቢነት ልጠረጠር እችላለሁ እንጂ ሙስናው ላይ የለሁበትም፡፡
- ምን እያልህ ነው?
- ይኸው ሦስት አራት ድርጅቶችን ከፍቼ እየተንቀሳቀስኩ እኮ ነው፣ እንዲያው ልማታዊ ባለሀብት ቢሉኝ ይቀላል፡፡
- ታዲያ ሞስነህ አይደል እንዴ ባለሀብት የሆንከው?
- እኔ ዕውቀቴን ተጠቅሜ ነው ባለሀብት የሆንኩት፡፡
- እኔ እኮ የሚገርመኝ እንደዚህ ዓይነት ዓይን ያወጣ ውሸት ስትዋሽ ነው፡፡
- እንዴት?
- አንተ አይደለህ እንዴት በሾፌርህና በጋርድህ ሳይቀር የከተማውን ቦታ ስታሸነሽነው የነበርከው?
- ማስረጃው አለዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ማስረጃ ተብለን ባንጠያየቅ ጥሩ ይመስለኛል፡፡
- እንዴት?
- ሰነድ መውጣት ከጀመረ እስር ቤቱ ላይበቃችሁ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ መልቀቂያዬን ይቀበሉኝ፡፡
- ለምንድነው የምትለቀው?
- ስለተነቃብኝ!
[ክቡር ሚኒስትሩ የፓርቲ ስብሰባ ላይ ተራቸው ደርሶ ከሰብሳቢው ጋር እያወሩ ነው]
- እኔ የተባለውን ነገር ሰምቻለሁ፡፡
- ምንድነው ታዲያ አስተያየትዎ ክቡር ሚኒስትር?
- አንድ ግልጽ እንዲደረግልኝ የምፈልገው ነገር አለ፡፡
- ምንድነው እሱ ክቡር ሚኒስትር?
- ሕዝቡ በቃኝ እያለ ነው፡፡
- በቃኝ ማለት?
- አልፈልጋችሁም እያለን ነዋ፡፡
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሕዝብን ማዳመጥ የለብንም ትላላችሁ?
- ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ ምን እንደሚያስፈልገው እኮ የምናውቅለት እኛ ነን፡፡
- እዚህ ጋ ግን አንድ ነገር መታየት አለበት እላለሁ፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ሕዝቡ እኮ እምቢ እያለ ነው፡፡
- ይኼን ነገር እኮ በተደጋጋሚ የተነጋገርንበት መሰለኝ፡፡
- ምኑን?
- የሕዝቡ ጥያቄ የሚያሳየው የአገሪቷ ኢኮኖሚ እያደገ መምጣቱን ነው፡፡
- ለዛ ነው በየቀኑ የተቃውሞ ሠልፍ ያለው?
- እሱማ ሰላማዊ ሠልፍ ስለተከለከለ ነው፡፡
- ግራ የሚያጋባ ነገር ነው እኮ ነው የምታወሩት፡፡
- ምኑ ነው ግራ የገባዎት?
- ሕዝቡ አልፈልግም ይላል፣ እኛ ደግሞ ለሕዝብ እናውቃለን እያልን ነው፡፡
- እርስዎ ይኼን ያህል ዓመት ፖለቲካ ውስጥ ቆይተው የምን መልፈስፈስ ነው?
- ተልፈስፍሼ አይደለም፡፡
- ለመሆኑ እርስዎ በልተው ጠግበዋል እንዴ?
- ቆይ ቆይ እኔ ስለመብላቴ ማስረጃ አለህ?
- ይኼን በሌላ ስብሰባችን እናየዋለን፡፡
- በየትኛው ስብሰባ?
- ሂስና ግለ ሂስ በምንውጥበት፡፡ ለማንኛውም ሕዝቡ ልቀቁ እያለን ነው፡፡
- እኛ ለቃቂዎች አይደለንም፡፡
- እና ምንድን ነን?
- አስለቃቂዎች!