የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የውኃ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላልና ግድቡ በታችኛው የአባይ ተፋሰስ አገሮች ላይ ሊኖሩ በሚችሉ ተፅእኖዎች ላይ በኢሊሊ ሆቴል ዛሬ እየተወያዩ ነው፡፡
ለዚሁ ውይይት ሲሉ ትናንት ኢትዮጵያ የገቡት ሚኒስትሮቹ የህዳሴ ግድቡን ሄደው የጎበኙ ሲሆን፣ በተለይ የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብደል አፊ (ዶ/ር) በግድቡ ላይ ያላቸውን ጥያቄና በውኃ አሞላሉ ጉዳት ሊኖረው ይችላል የሚሉ ስጋቶችን ለግድቡ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ስመኘው በቀለ እንደገለጹና ሥራ አስኪያጁም ምላሽ እንደሰጧቸው የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ኃይል ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) “ግድቡን ሄዳችሁ እንድትጎበኙ ያደረግነው ለውይይት፣ ለግልፅነትና መረጃን ለመለዋወጥ ይጠቅማል በማለት ነው፣” ሲሉ ለሚኒስትሮቹ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከግድቡ ጋር በተያያዘ በሁለቱ ተደራዳሪዎች ሲነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ስትሰጥ ቆይታለች ያሉት ሚኒስትሩ፣ በቀጣይም ማንም ሳይጎዳ ሁሉንም በሚጠቅም መልኩ መሥራት እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
የሱዳን የውኃ ሚኒስትር አምባሳደር ሙታዝ ሙሳ አብደላ “ጥቁር አባይ በጋራ ልንጠቀምበት የሚገባ ነው፤ ከዚህ በፊት በነበሩ ድርድሮች ያልተፈቱ ጥያቄዎች በዚህኛው ዙር ይፈታሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፣” ብለዋል፡፡
የግብፅ የውኃ ሚኒስትር የዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ካሁን በፊት ቢጠኑ ያላቸው ጉዳዮች እስካሁን አለመጠናታቸውና መዘግየታቸው የመንግሥታቸውና የርሳቸውም ስጋት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡