ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተከሰተው ደም አፋሳሽ ግጭት የፈጠረው ጥቁር ጠባሳ ገና አልሻረም፡፡ በሁለቱ ክልሎች የተከሰተው ደም አፋሳሽና ንብረት አውዳሚ ግጭት የፈጠረው ትኩሳት፣ በመላ አገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ፈጥሮ ነበር፡፡
መንግሥት በርካታ ሕይወት ያጠፋው፣ ንብረት ያወደመውና በርካቶችን ያሸማቀቀው ክስተት ሊፈጠር የቻለበትን ምክንያት በዝርዝር ቢያስቀምጥም በዋናነት ግን የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የሙስና መንሰራፋት፣ የመንግሥት አስፈጻሚዎች ማናለብኝነት፣ የድንበር ማካለል ችግር፣ ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ ወዘተ ተሰምሮባቸዋል፡፡ ከዚህም በዘለለ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች መደፍጠጥ ጉልህ ሥፍራ ይይዛሉ፡፡
እነዚህ መጠነ ሠፊ ችግሮች በፌዴራል መንግሥት፣ በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደርች የተንሰራፋ ቢሆንም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተለየ መንገድ በመገንፈሉ ለበርካታ ንፁኃን ሕይወት መጥፋት፣ ለአካል ጉዳትና ንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል፡፡
ይህ አገሪቱን ማቅ ያለበሰው ክስተት ዳግም እንዳያገረሽና እንዳይከሰት የፖለቲካ መፍትሔ ለመስጠት ታች ላይ እየተባለ ይገኛል፡፡
በተለይ የግጭት አውድማ ሆነው የከረሙትና ከአሥራ ሁለት ዓመት በኋላ በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት የሆኑት የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ለማድረግ ከመታተራቸውም በላይ፣ ሥራ ለመፍጠርና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ለማስፈን ‹‹የኢኮኖሚ አብዮት›› ማቀጣጠል ያስፈልጋል የሚል ዕቅዳቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
‹‹የኢኮኖሚ አብዮት›› በሚባል ኃይለ ቃል ታጅቦ የቀረበው አዲስና ግዙፍ ኩባንያዎችን የመመሥረት ዕቅድ በኅብረተሰቡ ዘንድ የተደበላለቀ ስሜት የፈጠረ በመሆኑ መሰንበቻውን መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይም ሆኗል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ባወጣው አዲስ ዕቅድ፣ አዳዲስ የቢዝነስ ዕቅዶችን አስተዋውቋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ባወጣው ትንታኔ በክልሉ በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው ዕድሜው 15 ዓመት ይሞላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዕድሜያቸው በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች በሥራ አጥነት ተመዝግበዋል፡፡ ይኼንን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት ክልሉ ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ለሚጠጋ ሰው በየዓመቱ ሥራ መፍጠር እንዳለበት ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፣ የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ልሳን የሆነው ሕዳሴ ጋዜጣ ላይ በወጣ ጽሑፍ እንደገለጹት፣ ክልሉ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ማድረግ ግዴታው ነው፡፡ ‹‹ይኼንን ማድረግ ካልተቻለ እንደ ክልልም ሆነ እንደ አገር ህልውናችን ችግር ውስጥ እንደሚገባ ሳይታለም የተፈታ ነው፤›› ሲሉ አቶ አዲሱ የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጸዋል፡፡
ክልላዊ መንግሥቱ በተያዘው በጀት ዓመት 1.2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶች ሥራ ፈጠራ 6.6 ቢሊዮን ብር በጀት ይዟል፡፡ አቶ አዲሱ በጽሑፋቸው እንዳብራሩት፣ የኦሮሚያ ክልል ዕቅድ ሥራ ፈላጊዎች ዳቦ እንዲያገኙ ማድረግ ብቻ አይደለም፡፡ የኦሮሞ ወጣት ባለሀብቶች እንዲፈጠሩ ማድረግ ላይም ትኩረት ተደርጓል፡፡
በዚህ መሠረት በመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ጥምረት (ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ) ጽንሰ ሐሳብ ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡ በዚህም የክልሉ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ከወጣቶችና ከባለሀብቶች ጋር በማስተሳሰር በርካታ ፋብሪካዎችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዟል፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥም በመንዲና በጭሮ (አሰበ ተፈሪ) ከተሞች በ256 ሚሊዮን ብር ሁለት የእምነበረድ ፋብሪካዎች፣ በነቀምት ከተማ በ146 ሚሊዮን ብር የማንጎና የቲማቲም ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች፣ በሻሸመኔና በጅማ ከተሞች በ78 ሚሊዮን ብር ሦስት የስልክ እንጨት መቀቀያ ፋብሪካዎች፣ ባልተጠቀሰ ዋጋ በጌዶና በቢሾፍቱ ከተሞች ሁለት የማዕድን ውኃ ፋብሪካዎች ለማቋቋም የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት ተካሂዷል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም በአምቦ ከተማ የሲሚንቶ ፋብሪካ እንዲሁም ግዙፍ ሪል ስቴት ለመገንባት ታቅዷል፡፡
አቶ አዲሱ እንዳብራሩት፣ ለፋብሪካዎቹ ግንባታ የሚያስፈልገው መነሻ ካፒታል የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በድርሻቸው ልክ የሚያዋጡ ሲሆን፣ የሥራ ፈላጊዎች ድርሻ ደግሞ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በብድር ይሸፈናል፡፡ ለባለሀብቶች የአክሲዮን ሽያጭ ይከናወናል፡፡
የካቲት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ስብሰባውን ያካሄደው የኦሮሚያ ክልል ካቢኔ የመንግሥትና የባለሀብቶች ጥምረት ምክር ቤት እንዲመሠረት ወስኗል፡፡ በጥምር ምክር ቤቱ አስተባባሪነት በርካታ ኩባንያዎች እንዲመሠረቱ እየተደረገ ሲሆን፣ ቅድሚያ ከያዙት ውስጥ ኦዳ ትራንስፖርት ኩባንያና ኬኛ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ኩባንያ ተጠቃሾች ሆነዋል፡፡
ለኦዳ ትራንስፖርት ኩባንያ ካፒታል ለማሰባሰብ መጋቢት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በኦሮሞ ባህል ማዕከል በተካሄደው ዝግጅት ከአክሲዮን ሽያጭ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መገኘቱ ታውቋል፡፡
የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊና የመንግሥትና የግል ባለሀብቶች ጥምረት ምክር ቤት አባል አቶ ታከለ ኡማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኦዳ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ከወጣቶች ጋር በጋራ የሚያተዳድሯቸው የነዳጅ ማደያዎችና የነዳጅ ዴፖዎች ይኖሩታል፡፡
የኦሮሚያ ክልል አዲስ ዕቅድ ግዙፍ ኩባንያዎችን በማቋቋም ለወጣቶች ሥራ በመፍጠርና ሀብት በማካፈል ብቻ አላቆመም፡፡ ከዚህ በጥልቀት በመሄድ በተለይ ተጨማሪ እሴት አይጨምሩም የተባሉ የማዕድን ማውጫዎችን ከባለሀብቶች ነጥቆ ለወጣቶች ማቅረብ ላይም ትኩረት አድርጓል፡፡
አቶ አዲሱ እንዳብራሩት፣ ወጣት ባለሀብቶችን ለመፍጠር ለተያዘው ዕቅድ መሳካት በክልሉ የሚገኘው ተፈጥሮ ሀብት ከግምት ገብቷል፡፡ ‹‹ባለሀብቶች ከዚህ በፊት በኢንቨስትመንት ስም የተፈጥሮ ማዕድናት ‘ሬድ አሽ፣ አሸዋ፣ ድንጋይ፣ ፑሚስና ታንታለም’ ምንም እሴት ሳይጨምሩ ሲጠቀሙበት ነበር፡፡ አሁን ግን ይኼን አሠራር አስቀርተናል፤›› ሲሉ አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡
ባለሀብቶች እሴት ወደሚጨምሩ ዘርፎች እንዲሄዱ እየተደረገ መሆኑን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የተፈጥሮ ሀብቱን የሚጠቀሙበት አሠራር መዘርጋቱን አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ዕቅድ መሠረት የኦሮሚያ ክልል በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የማዕድን ሥፍራዎችን ከባለሀብቶች በመንጠቅ ሒደት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ እነዚህን ቦታዎች ለወጣቶች በመስጠት ምርቶቹን ባለሀብቶች ከወጣቶቹ በግዢ ተረክበው እንዲሠሩ ተወስኗል፡፡
ነገር ግን በተለይ በገላንና በዱከም የሚገኙ ጠጠር አምራቾች ይህንን ውሳኔ ሕጋዊ መሠረት የሌለውና ሀብት የማፍራት መብትን የሚደፈጥጥ ነው ሲሉ አቤቱታቸውን ለክልሉ መንግሥት አቅርበዋል፡፡
በአማራ ክልልም በተመሳሳይ ግዙፍ ኩባንያዎች በመቋቋም ላይ ይገኛሉ፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግሥት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን፣ የኢንዶውመንት ኩባንያዎችንና ባለሀብቶችን በማጣመር ‹‹ዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር›› በሚባል ስያሜ የበርካታ ኩባንያዎች እናት በመሆን ሚናውን የሚወጣ ግዙፍ ኩባንያ መሥርቷል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የኢንዶውመንት ኩባንያዎች እናት የሆነው ጥረት ኮርፖሬትና ባለሀብቶች የአክሲዮን ግብይት ፈጽመዋል፡፡
ዓባይ ኢንዱስትሪ በክልሉ በተለይም በባህር ዳር ከተማ የብረታ ብረት ፋብሪካ፣ በምሥራቅ ጎጃም ደጀን አካባቢ የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ በደብረ ብርሃንና በወልድያ ከተሞች የእንጨት ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካዎች ግንባታ ለማካሄድ ከወዲሁ ዝግጅት እየተካሄደ ነው፡፡
የዓባይ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እስካለፈው ሳምንት ድረስ 990 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ተሸጦ ተሰብስቧል፡፡ 3.25 ቢሊዮን ብር ደግሞ ቃል የተገባ ካፒታል (የተፈረመ) አለ፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ግዙፍ ኩባንያ 750 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ አክሲዮን ለገበያ እየቀረበ ነው ሲሉ አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት የፋብሪካ ግንባታዎችን ለማካሄድ ዓባይ ኢንዱስትሪ ስድስት ቦታዎች የተረከበ ሲሆን፣ ፋብሪካዎቹን ለመገንባት የአዋጭነት ጥናት ተካሂዷል፡፡ አቶ ተስፋዬ አሁን ቁጥሩን በተመለከተ እርግጠኛ ባይሆኑም፣ ለበርካታ የክልሉ ወጣቶች ሥራ የሚፈጥሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የሚያንቀሳቅስ ተቋም እየተፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ለወጣቶች ሥራ ለመፍጠርና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ለማስፈን የጀመሯቸው እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ የአገሪቱን ፖሊሲ ይፃረራሉ የሚሉ ድምፆች እየተሰሙ ነው፡፡
የፌዴራል መንግሥት መስከረም 2005 ዓ.ም. ባሳተመው የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ መንግሥት በኢኮኖሚው ላይ ስለሚኖረው ሚና በግልጽ ተቀምጧል፡፡ አገሪቱ የምትከተለው የኢኮኖሚ ሥርዓት ነፃ ኢኮኖሚ በመሆኑ፣ የኢንዱስትሪ ተቋማትን በማቋቋም ረገድ የግሉ ዘርፍ ሞተር ይሆናል ይላል ስትራቴጂው፡፡
‹‹መንግሥት የግል ባለሀብቶች በአጥጋቢ ሁኔታ ሊሰማሩ በሚችሉባቸው የሥራ መስኮች ተደርቦ መሥራት አይገባውም፤›› በማለት የሚተነትነው የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ሰነድ፣ ‹‹የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሀብት ቀልጣፋ ድልድልን በማምታታት፣ የኢንዱስትሪ ልማት ዕድገትን ከማጓተት አልፎ የሚያስገኘው ጥቅም የለም፤›› ሲል ስረዳል፡፡
በኢትዮጵያ እንዲመጣ የሚፈለገው ፈጣን የኢንዱስትሪ ልማት ዕውን የሚሆነው፣ መንግሥት ብቃት ያለው አመራር ከሰጠ ብቻ መሆኑን የስትራቴጂ ሰነዱ አስምሮበታል፡፡
ነገር ግን በገበያውና በግሉ ዘርፍ በአጥጋቢ ሁኔታ ሊሠሩ የማይችሉ ክፍተቶች ካሉ፣ ይህ ክፍተት በሸማቹና በኅብረተሰቡ ላይ ችግር የሚያመጣ በመሆኑ መንግሥት ጣልቃ እንደሚገባም በሰነዱ ላይ ተገልጿል፡፡
በዚህ መሠረት ቀደም ባሉት ዓመታት የግሉ ዘርፍ ሊገባባቸው ባልቻለባቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መንግሥት ጣልቃ እየገባ ሲሠራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ የሥራ አፈጻጸማቸው ደካማ ቢሆንም በርካታ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች፣ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች፣ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ውስጥ የግሉ ዘርፍ አቅም ውስን ስለነበር መንግሥት ጣልቃ ገብቷል፡፡
ከዓመታት በኋላም በእነዚህ መስኮች የግሉ ዘርፍ የመሳተፍ ፍላጎት እያሳየ በመሆኑ፣ መንግሥት በግልና በመንግሥት ጥምረት ወይም በግሉ ዘርፍ ብቻ እንዲካሄድ ለማድረግ በሩን እየከፈተ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ ከዚህ አንፃርም የግል ባለሀብቶች በስኳር ፕሮጀክቶች፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ዘርፍ በማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካዎች ዘርፍ እንዲገቡ ጥሪ ማድረጉን ማስታወስ ይቻላል፡፡
ነገር ግን በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተቋቋሙ የሚገኙት ፋብሪካዎች በአብዛኛው የግሉ ዘርፍ የገባባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡ በሲሚንቶ፣ በብረታ ብረት፣ በለስላሳ መጠጦች፣ በእንጨት ሥራዎች፣ በትራንስፖርትና ነዳጅ ማደያዎች፣ በሪል ስቴትና በመሳሰሉት ዘርፎች በአሁኑ ወቅት የግሉ ዘርፍ በሰፊው የተሰማራባቸው ቢሆንም፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች አነሳሽነት እየተገባ ያለው በእነዚህ ዘርፎች መሆኑ ታይቷል፡፡
የኢኮኖሚው ባለሙያው ዶ/ር ወልዳይ አመሐ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ በረዥም ጊዜ ሒደት ለውጥ ማምጣት የሚችለውና የኢኮኖሚ ዕድገት ሞተር የሚሆነው የግሉ ዘርፍ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ይህ በምንም ሁኔታ የምደራደርበት ሐሳብ አይደለም፡፡ ምክንቱም ለለውጥ ይኸው ነው መንገዱ ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ለጊዜያዊ መፍትሔ ሲባል የሚሠሩ ነገሮች ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ውጤታማ አያደርግም፡፡ በወሳኝነት ለውጥ ለማምጣት መንግሥት የግሉ ዘርፍ በማይገባበት መስክ ገብቶ አሳይቶ የግሉ ዘርፍ እንዲከተለው ማድረግ ነው፡፡ መንግሥት በአንድ በኩል ፕራይቬታይዝ እያደረገ እንደሚገኝ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የነበሩትን እየሸጠ እየወጣ ነው፡፡ እንደ አዲስ እየገባ ነው ካልንም የግሉ ዘርፍ መግባት ባልቻለባቸው ቦታዎች እየገባ፣ መንግሥት ከሠራ የሚደገፍ ነው፡፡ የመንግሥት ሚና በጉልህ መለየት አለበት፡፡ በምንም ዓይነት ተዓምር የግሉን ዘርፍ ከጨዋታ እያስወጣን በሄድን ቁጥር የሩሲያ ዓይነት ችግር ውስጥ ነው የምንገባው፡፡ ወይም ደግሞ በደርግ መንግሥት ወቅት እንደነበረው ዓይነት ከባድ ውድቀት ውስጥ ነው የምንወድቀው፡፡ ይህ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ይልቅ አሁንም ቢሆን የሚያስደነግጠው ነገር ምንድነው ካልን፣ መንግሥት በአብዛኛው ኢንቨስተር መሆኑ፣ በፋይናንስ ዘርፉም ትልቁን ድርሻ መያዙ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርኼ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እነዚህ ኩባንያዎች ሊሰማሩባቸው ያሰቡዋቸው የሥራ ዘርፎች መደራረብ ብቻ ሳይሆን በራሱ ችግር ያለበት ነው፡፡ ለምሳሌ ይላሉ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፣ የጭነት አገልግሎት ኩባንያ ማቋቋም፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ – ጂቡቲ ኮሪደር ባቡር መስመር በተዘረጋበትና ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በተጠናቀቀበት ወቅት የኦሮሚያ የጭነት ትራንስፖርት ማቋቋሙ ያለው አስፈላጊነት አጠያያቂ ነው፡፡
ሲሚንቶም ቢሆን ግዙፎቹ ደርባ ሚድሮክና ዳንጎቴ ወደ ምርት ከተሸጋገሩ በኋላ ገበያ ከመረጋጋቱም በላይ መሰቦ፣ ሙገር፣ ብሔራዊ ሲሚንቶና የተቀሩት በርካታ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በገበያው አዎንታዊ ተፅዕኖ አምጥተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የገበያ ዋጋ እንዲረጋጋ አድርገውና በአሁኑ ወቅት ወደ ውጭ ኤክስፖርት ለማድረግ እየታሰበ ባለበት ወቅት፣ በመንግሥት ደረጃ ተደራራቢ ግንባታ ለማካሄድ መንግሥት መራሹ ‹‹የኢኮኖሚ አብዮት›› ሥራ ከመፍጠር በተጨማሪ የሰነቀው ህልም ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተጀመረው የኢኮኖሚ አብዮት ወደ ሌሎች ክልሎችም ሊያመራ እንደሚችል ፍንጮች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ‹‹የኢኮኖሚ አብዮቱ›› ኅብረ ብሔራዊነትን የሚያቀነቅኑ ተቋማት ከመፍጠር ይልቅ፣ አሁንም ክልል ተኮር ኩባንያዎችን ለማቋቋም ጥረት መደረጉ በበርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች አነጋገሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡
አቶ ታከለና አቶ ተስፋዬ ይህን አይበቀሉትም፡፡ አቶ ታከለ እንደሚሉት በኢትዮጵያ እንደ ኦሮሚያ ክልል የበርካታ ብሔርና ብሔረሰቦች መኖሪያ የለም፡፡ ‹‹ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ መኖር ባህላችን ነው፡፡ የዚህ ምስክሩ ታዋቂው የጉዲፈቻ ሥርዓታችን ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አክሲዮን መግዛት ይችላል ብለዋል፡፡ አቶ ተስፋዬም ዓባይ ኢንዱስትሪ ልማትን ለማቋቋም የቀረበው አክሲዮን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ክፍት ነው በማለት ገልጸዋል፡፡
ክልሎቹ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አክሲዮን መግዛት እንደሚችል ቢገልጹም የክልሎቹ የልማት ድርጅቶች፣ የኢንዶውመንት ኩባንያዎችና የክልሎቹ ተወላጅ ባለሀብቶች ተሳትፎ የጎላ በመሆኑ፣ ይህ ክልል ተኮር የሆነ ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ የፈጠረው ሥጋት በቀላሉ የሚታይ አይደለም በማለት ጥርጣሬያቸውን የሚገልጹ አሉ፡፡
የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ገዥ መንግሥት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተቋቋሙ የሚገኙ ኩባንያዎች የመንግሥት ባለቤትነት የሚጎላባቸው በመሆኑ፣ የግሉ ዘርፍ የሚያመርተውን ምርት ደግመው ለማምረት የተዘጋጁም ስለሆነ ፍትሐዊ የንግድ ውድድር ሊያሰፍን ይችላል ወይ? የሚል ሥጋት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ክልል ተኮር ፋብሪካዎች የሚያመርቱትን ምርት ክልሉ ያለ ውድድር በቀጥታ ግዢ የሚፈጽም ከሆነ፣ ቅድሚያ የገበያ ዕድል ሊሰጥ ይችላል ሲሉ አቶ ኃይሌ ሥጋታቸውን ይናገራሉ፡፡
እነዚህ ክልል ተኮር ኩባንያዎች የተፋጠነ መንግሥታዊ አገልግሎት፣ ፈጣንና የተመቻቸ የኢንቨስትመንት ምኅዳር፣ የመሬት አቅርቦት፣ ዋነኛ አበዳሪ ከሆኑት የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ፋይናንስ ያለምንም ውጣ ውረድ ሊያገኙ ይችላሉ የሚል አስተያየትም ይደመጣል፡፡ በአንፃሩ የግሉ ዘርፍ እነዚህን ጥቅሞች በቀላሉ ማግኘት የሚችል ባለመሆኑ፣ ፍትሐዊነቱን ጥያቄ ውስጥ የከተቱ በርካታ ባለሀብቶች ናቸው፡፡
አቶ ኃይሌ ለሪፖርተር እንደለጹት፣ ሀብት አሰባስቦና ትልቅ ካፒታል ፈጥሮ ወደ ሥራ መግባት የሚደገፍ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እየተቋቋሙ ያሉ ኩባንያዎች በውድድር ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ ይላሉ፡፡ መንግሥትም ኢንቨስት እያደረገ መቀጠል አለበት ብለውም እንደማያምኑ በአፅንኦት ያስረዳሉ፡፡
ለሥራ ዕድል ፈጠራ መንግሥት የግሉን ዘርፍ የሚያሠራ ጥሩ ምኅዳር ቢፈጥርለት ሊፈታ የማይችል ችግር እንደሌለም ይነገራል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የግሉ ዘርፍ በበርካታ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ የሥራ ፈላጊዎችን በሙሉ መያዝ አለመቻሉ ደግሞ ሌላው ፈተና ነው፡፡
ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፣ መንግሥት በየጊዜው ቢሊዮን ብሮችን እየመደበ ሥራ ሊፈጥር አይችልም ይላሉ፡፡ ሊሆን የሚገባው ጥራት ያለው ትምህርት ሰጥቶ ለገበያ ማቅረብ ነው፡፡ ጥራት ያለው ሙያተኛን ገበያው ራሱ የሚፈልገው ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ወጣቱ ሙያተኛ የራሱን ሥራም ሊፈጥር ይችላል በማለት ይህ አካሄድ ትክክለኛ አለመሆኑን አስረድተው፣ መንግሥት ጠንካራ የግል ዘርፍ እንዲፈጠር የተለያዩ ማነቆዎች የሚፈጥሩ አሠራሮችን መፍታትና ማስተካከል እንዳለበት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ አክለዋል፡፡
የኢኮኖሚ ምሁሩ ዶ/ር ወልዳይ የሥራ ፈጠራን በሚመለከት እንዳብራሩት፣ ወጣቶች ተነሱ ወዘተ. ተብሎ የሚደረገው ነገር ጊዜያዊ ችግርን ለመፍታት የሚወሰድ ዕርምጃ ነው፡፡ ‹‹እንደተጠቀሰው ያለ ዓይነት ነገር የሚሠራ ከሆነ ለእኔ የፖፑሊስት ወይም የሕዝባዊነት ስሜት ያነገበ አካሄድ ነው፡፡ ለዘለቄታው ያሉብን ችግሮች እንዴት ይፈቱ የሚለው ነው የእኔ ትኩረት፡፡ ችግሮችን ለማርገብና ለማረጋጋት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ይኖራሉ፡፡ እኔ ግን ዘላቂ ሥራዎች ላይ ማተኮሩን እመርጣለሁ፡፡ በወጣቶች ላይ ለመሥራት እኮ አሁንም አንዱ መፍትሔ፣ የግሉን ዘርፍ ማሳደግ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ ደካማ ነው ካልን እንዴት አድርገን ነው ጠንካራ እንዲሆን መሥራት ያለብን የሚለውን ማጤን ይኖርብናል፡፡ በአገሪቱ የታየውን ሁኔታ እንዴት ትተረጉመዋለህ ካልከኝ፣ እንደ የፍጥነት ማገጃ ወይም የፍጥነት መወሰኛ እመለከተዋለሁ፡፡ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ የተፈጠረው የንግድ ማኅበረሰብ ወቅታዊ አሠላለፍ ንግድ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት በንግድ ዘርፍ የተሰማራው ነጋዴ በኤክስፖርት ዘርፍ እንዲሰማራ መንግሥት ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም በርካታ ኤክስፖርተሮች ተፈጥረዋል፡፡ ከዚህም በኋላ በኤክስፖርት፣ በአገልግሎት ሰጪና በንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ መንግሥት ግፊት ከማድረግ ባሻገር፣ በጉዳዩ ላይ ከባለሀብቶች ጋር እያብሰለሰለ ይገኛል፡፡
ነገር ግን ሁለቱ ትልልቅ ክልሎች የግሉ ዘርፍ ሊገባባቸው በሚችሉ ዘርፎች መግባታቸው ግርምት ከመፍጠሩም በላይ፣ ምናልባት የግሉ ዘርፍ ሊገባባቸው ባልቻለባቸው የተመረጡ ዘርፎች ገብተው ቢሆን ድጋፍ እንጂ ጥርጣሬ እንደማይፈጠርም ሪፖርተር ያነጋገራቸው የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ገልጸዋል፡፡