- የኖርዌይ ማዳበሪያ አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ አንድ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ አቅዷል
የመዳረሻዎቹን ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት በማሳደግ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ባለፈው ሳምንት ወደ ኦስሎ ኖርዌይ የከፈተው አዲስ የበረራ መስመር በኢትዮጵያና በኖርዌይ መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት እንደሚያጠናክር ተገለጸ፡፡
መጋቢት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ማምሻውን ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የተነሳው ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ለሰባት ሰዓታት ያህል በ38,000 ጫማ ከፍታ ከከነፈ በኋላ፣ ኦስሎ ጋይደርሞን ኤርፖርት ሲያርፍ የኤርፖርቱ የእሳት መከላከያ ብርጌድ ውኃ በመርጨት ተቀብሎታል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር አንድሪያስ ጋርደር፣ የአስጎብኚ ድርጅቶች ኃላፊዎች፣ ኢትዮጵያን ሆሊዴይስ ባዘጋጀው የቡድን ጉብኝት ፕሮግራም ለማሳተፍ የተጓዙ ኢትዮጵያውያን ጎብኚዎች የተሳፈሩበት አውሮፕላን ኦስሎ ኤርፖርት በደረሰበት ወቅት፣ የኦስሎ ኤርፖርት ኃላፊዎች፣ በኖርዲክ አገሮች የኢትዮጵያ አምባሳደር ወ/ሮ ወይንሸት ታደሰ፣ በኖርዌይ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፡፡
አምባሳደር አንድሪያስ ለሪፖርተር እንደተናገሩት ኢትዮጵያና ኖርዌይ ለረዥም ዓመታት የቆየ መልካም ወዳጅነት አላቸው፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ሰላም በማስከበር፣ በልማት፣ በአየር ንብረት ጉዳዮችና በትምህርት ተባብረው እንደሚሠሩ የተናገሩት አምባሳደር ጋርደር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኦስሎ ቀጥታ በረራ መጀመሩ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እያደገ መምጣቱን እንደሚያመላክት አስረድተዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1940ዎቹ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሚሲዮናውያን በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ለመጀመሩ ምክንያት እንደሆኑ ይነገራል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከኖርዌይ መንግሥት ጋር በመሠረተው የጠበቀ ወዳጅነት አማካይነት የኖርዌይ ባህር ኃይል የኢትዮጵያን ባህር ኃይል በ1955 ዓ.ም. እንዲያቋቁምና እስከ 1965 ዓ.ም. እንዲመራ አድርገዋል፡፡ ይሁንና ኖርዌይ አምባሳደር ሾማ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት ያሳደገችው ከደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1995 ነበር፡፡ የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት ረዥም ዓመታት እንደማስቆጠሩ የንግድና የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ግን ያደገ አይደለም፡፡ የንግድ ግንኙነቱ ውስን እንደሆነ የሚናገሩት አምባሳደር ጋርደር፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰቱን ማሳደግ እንደሚቻል ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀጥታ በረራ መጀመር መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ከኖርዌይ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት መጨመር እንችላለን፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኦስሎ በረራ መጀመሩ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የኖርዌይ ቱሪስቶች ቁጥር ለመጨመር ያስችላል፡፡ የመጣሁት ዘመናዊ በሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ነው፡፡ መስተንግዶው የተዋጣለት በመሆኑ የኖርዌይ ቱሪስቶች ይህን ኢትዮጵያዊ መስተንግዶ እንደሚወዱት እርግጠኛ ነኝ፤›› ብለዋል፡፡
በአውሮፓ በነዳጅ ሀብቷ የምትታወቀው ኖርዌይ በዓሳ ምርትም ቀዳሚ ናት፡፡ በዓመት 1.2 ሚሊዮን ቶን ሳልመን የምታመርተው ኖርዌይ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጀመረው አዲስ በረራ አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ ሳልመን ኤክስፖርት እንደምታደርግ አምባሳደር ጋርደር ጠቁመዋል፡፡
ኖርፈንድ የተሰኘው የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ በኢትዮጵያ አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ኢንቨስት እያደረገ ሲሆን፣ ያራ ኢንተርናሽናል የተባለው የኖርዌይ ማዳበሪያ አምራች ኩባንያ በአፋር ክልል የፖታሽ ማዕድን ፍለጋ ላይ ተሰማርቷል፡፡ ያራ ዳሎል ቢቪ በሚባል ስም ኢትዮጵያ ውስጥ ባቋቋመው እህት ኩባንያ አማካይነት 100 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት ውጤታማ የፖታሽ ማዕድን ፍለጋ ሥራ አከናውኗል፡፡ ኩባንያው የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ከፍተኛ የማዕድን ማምረት ፈቃድ እንዲሰጠው አመልክቶ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡
ያራ የፖታሽ ክምችቱን ለማልማት አንድ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ማቀዱን የገለጹት አምባሳደር ጋርደር፣ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ከተደረገ በኢትዮጵያ ግዙፍ የኖርዌይ ኢንቨስትመንት እንደሚሆንና ሌሎች ኩባንያዎችን እንደሚስብ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ መጋቢት 18 ቀን 2009 ዓ.ም. በኦስሎ ፓርክ ኢን ሆቴል ባዘጋጀው ኢትዮጵያን የማስተዋወቂያ መድረክ የኦስሎ ኤርፖርት አስተዳደሮች፣ የኖርዌይና የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶችና የጉዞ ወኪሎች፣ የኖርዌይ ባለሀብቶችና የአየር መንገዱ የሽያጭና የፕሮሞሽን ባለሙያዎች ተካፍለዋል፡፡ አቶ ተወልደ ስለኢትዮጵያ አየር መንገድ ታሪክና ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድት ጋር ተያይዞ ስለተፈጠረው ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድል፣ እንዲሁም ሊጎበኙ ስለሚገባቸው ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች በፎቶግራፎች የተደገፈ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ተወልደ ለሪፖርተር እንደተናገሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ በማከናወን ከኖርዌይ ቱሪስቶችን ለማምጣት አቅዷል፡፡ በኖርዌይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ ሶማሊያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን እንደሚኖሩ ገልጸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚያመላልሳቸው ተናግረዋል፡፡
አየር መንገዱ የኢትዮጵያን የአበባ ምርት ወደ ኖርዌይ ለማጓጓዝ እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለጹት አቶ ተወልደ፣ በሳምንት ከ30 እስከ 40 ቶን የኢትዮጵያ አበባ ከሚገዛ የኖርዌይ ኩባንያ ጋር ከስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም አየር መንገዱ በዓሳ ምርት ከታወቀችው ኖርዌይ ሳልመን ወደ ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንደሚያጓጉዝ አስረድተዋል፡፡
አምባሳደር ወይንሸት በበኩላቸው ኖርዌጂያን የኢትዮጵያን ጣፋጭ ቡናዎች እያጣጣሙ መሆኑን ገልጸው፣ የኖርዌይ ቱሪስቶች ሊጎበኟቸው የሚገቡ በርካታ አስደናቂ ሥፍራዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ የሁለቱ አገሮች የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ቀስ በቀስ ቢሆንም እያደገ እንደመጣ የገለጹት አምባሳደር ወይንሸት ያራ፣ ኖርፈንድ፣ ሜስተርግሮን፣ አፍሪካን ጁስ፣ ኔራና ኖርፕላን የተባሉ የኖርዌይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ውስጥ በመሳተፍ ላይ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ ለኖርዌይ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ የተመቻቹ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዳሉ ገልጸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ መጀመሩ የኖርዌይ ባለሀብቶችና ቱሪስቶች ሳይጉላሉ ወደ ኢትዮጵያ ምቹ ጉዞ ማድረግ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል፡፡
ፓራዳይዝ ኢትዮጵያ የተሰኘ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት አቶ ፍጹም ገዛኸኝ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኦስሎ በረራ መጀመሩ ኩባንያቸውና ሌሎች የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ከኖርዌይና ከሌሎች የሰሜን አውሮፓ አገሮች ቱሪስቶችን ለመሳብ ያስችላቸዋል፡፡
‹‹አየር መንገዱ ወደ ኦስሎ አዲስ በረራ መጀመሩ ኢትዮጵያን በሰሜን አውሮፓ በማስተዋወቅ ቱሪስቶችን ወደ ኢትዮጵያና ሌሎች አፍሪካ መዳረሻዎች ለማምጣት ይረዳናል፡፡ አየር መንገዱ ወደ ኦስሎ በረራ መጀመሩን ስለሚያስተዋውቅ ቱሪስቶችን ለመሳብ እገዛ ያደርግልናል፡፡ እኔና ሌሎች አስጎብኚ ድርጅቶች ወደ ኦስሎ የመጣነው የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በማስተዋወቅ ከኖርዌይ የጉዞ ወኪሎች ጋር ሥራ ለመጀመር ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየጊዜው አዳዲስ በረራዎች መጀመሩ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፤›› ሲሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፍጹም ገልጸዋል፡፡
በኖርዌይ ለ44 ዓመት የኖሩት አቶ ሰለሞን ሥዩም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንን በኦስሎ ኤርፖርት መመልከታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አባልና የአፄ ኃይለ ሥላሴ የግል ጀልባ ካፒቴን የነበሩት አቶ ሰለሞን በየዓመቱ ወደ አገር ቤት እንደሚጓዙ ገልጸው፣ አየር መንገዱ ቤታቸው ድረስ በመምጣቱ ጉዟቸውን ምቹ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹አየር መንገዱ በፍጥነት በማደግ ላይ መሆኑ ከፍተኛ ደስታ ፈጥሮብኛል፡፡ ሦስት ቀለማት ያለውን ሰንደቅ ዓላማችንን አንግቦ በመላው ዓለም የሚጓዝ በመሆኑ በኩራት ነው የምንመለከተው፤›› ብለዋል፡፡
በኦስሎ የጣይቱ ምግብ ቤት ሥራ አስኪያጅ የሆነው ደምስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኦስሎ በረራ መጀመር እንዳስደሰተው ገልጾ፣ በመጀመሪያው በረራ ትኩስ እንጀራ ከአገር ቤት እንዳስመጣ ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡ ‹‹እኛ እዚህ የምንሠራው እንደ ነጋዴ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል እናስተዋውቃለን፤›› ብሏል ደምስ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉት 86 ዘመናዊ አውሮፕላኖች ወደ 94 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች የሚበር ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ብቻ ሦስት በረራዎች ወደ ኦስሎ፣ ቪክቶሪያ ፎልስና አንታናናሪቮ ጀምሯል፡፡ በቅርቡም ወደ ቼንግዱ ቻይና፣ ጃካርታና ሲንጋፑር ሦስት መዳረሻዎች እንደሚከፍት ለማወቅ ተችሏል፡፡