Tuesday, January 31, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በደላላ አገር ተጉላላ!

የአገሪቱ የከተሞች መሬት የደላላ መጫወቻ መሆኑ ብዙ የተባለበት እውነታ ነው፡፡ የተመሰቃቀለው የግብይት ሥርዓት የደላላ ሰለባ መሆኑን ማንም የማይክደው ነው፡፡ ጤፍና ጥራጥሬን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ እህሎችና መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች የሚታገቱት በደላላ ነው፡፡ ሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት ሕዝቡን የሚያሰቃየው በደላላ ሳቢያ ነው፡፡ የቢሮና የመኖሪያ ቤት ኪራዮች የሚመሩት ባልተጻፈ የደላላ ሕግ ነው፡፡ የተሽከርካሪ ግብይትና የመኖሪያ ቤት ሠራተኞች ቅጥር የሚዘወረው በደላላ ነው፡፡ በርካታ ጉዳዮች የሚፈጸሙት የደላላ ሁለገብ ተሳትፎ ታክሎባቸው ነው፡፡ አሁን ጥያቄው ደላላ ለምን የሁሉም ነገር አልፋና ኦሜጋ ሆነ የሚለው አይደለም፡፡ ደላላማ መኖር አለበት፡፡ ድለላም እንደ ሙያ መታየት ይኖርበታል፡፡ መከበርም አለበት፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ውስጥ አሁን እየታየ ያለው የድለላ ሥራና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከልማቱ ይልቅ አጥፊነቱ እየበዛ መሆኑን በግልጽ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ድለላ በዓለም በሚገባ የሚታወቅ የተከበረ ሥራ ነው፡፡ ተቋማዊ ሆኖ በሙያ ሥነ ምግባር ሲመራ ጠቀሜታው ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ እዚህ አገር ግን በተበላሸ ጎዳና ላይ እየተጓዘ አገርና ሕዝብን እያስመረረ ስለሆነ አንድ መላ ሊፈለግለት ይገባል፡፡ የሕግ መላ፡፡

እዚህ አገር ድለላ (Brokerage) አማራጭ ያጡ ዜጎች የዕለት እንጀራ እንዲሆናቸው ከተጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በሌላው ዓለም ደግሞ ተቋማዊ (Brokerage Firm) ሲሆን፣ አገልግሎቱም ገዥና ሻጭን በፍትሐዊ መንገድ ማገበያየት ነው፡፡ ይህ ግብይት ከትልልቆቹ የፋይናንስ ተቋማት ጀምሮ እስከ ግለሰቦች ድረስ ይዘልቃል፡፡ ይህ ሥራ በሕግ ማዕቀፍ የሚገዛ ነው፡፡ በመስኩ የሚሰማሩትም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የወጡ ናቸው፡፡ የግለሰቦችን ይዞታ ከማሻሻጥ ጀምሮ እስከ አክሲዮን ድርሻዎችና ቦንዶች ድረስ የሚሳተፈው የድለላ ሥራ በሪል ስቴት ዘርፍም ትልቅ ሥፍራ አለው፡፡ በድለላ ሥራ የተሰማሩ ባለሙያዎችም ገበያውን በኃላፊነት በማጥናትና ተገቢውን መረጃ በመስጠት ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ፡፡ ሕጉ በሚያዘው መሠረትም የግብር ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡ ግብይቱ ጤናማ እንዲሆንም ተግተው ይሠራሉ፡፡ በዚያው መጠንም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ የአገልግሎታቸው ተፈላጊነትም የዚያኑ ያህል ነው፡፡

ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለስ ችግሩ የሚጀምረው ከመንግሥት ነው፡፡ የድለላ ሥራ በሕግ የሚመራና ግብይቱን በተገቢው መንገድ የሚያቀላጥፍ መሆን ሲገባው፣ ችላ በመባሉ ብቻ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ አሁንም እያደረሰ ነው፡፡ የድለላ ሥራን የሚቆጣጠር የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶ ተቆጣጣሪ ተቋም (Regulatory Body) መኖር የነበረበት ከዓመታት በፊት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በአንድ ወቅት ባወጣው ሪፖርት እንደገለጸው፣ ይህ ተቆጣጣሪ የሌላው የድለላ መስክ የአገሪቱን የከተሞች መሬት እንደፈለገው ሲጫወትበት ቆይቷል፡፡ በተለይ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የተሻረኩ ደላሎች መሬት ከማስወረር አልፈው የዋጋ ተመን እያወጡ እንዳሻቸው ሲፈነጩበት ከርመዋል፡፡ በሙያ ሥነ ምግባር የማይመራው ይህ የድለላ ሥራ የብዙዎችን ቀልብ በመሳቡ፣ በየቦታው እሴት ሳይጨምሩ ኮሚሽን የሚሰበስቡ በርካቶችን ቀፍቅፏል፡፡ ኮሚሽን የብዙዎችን ቀልብ እያሸፈተ የደላላ ሠራዊት በየሥርቻው ተሰማርቷል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ለመኖሪያ ቤት ወይም ለንግድ የሚሆኑ ግንባታዎች ለማካሄድ የደላላ ቡራኬ ያስፈልጋል፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚገኙ ይዞታዎች ተመናቸው የሚወሰነው በደላላ ብቻ ነው፡፡ ሻጭና ገዥ መብት የላቸውም፡፡ ቢኖራቸውም ከደላላ የተረፈ ነው፡፡

በጋራ የመኖሪያ ቤቶችም ሆነ በነባር መንደሮች ውስጥ የኪራይ ቤት ዋጋ የሚወሰነው በደላላ ተፅዕኖ ነው፡፡ አከራይ መብቱን ለደላላ አሳልፎ በመስጠቱ ብቻ፣ ተከራይ ከገቢው ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ለኪራይ እንዲያውል ተፈርዶበታል፡፡ ይህንንም ችሎ እየኖረ ሳለ ሳያስበው የተጋነነ ጭማሪ ይመጣበታል፡፡ የሚያቅማማ ከሆነ በአስቸኳይ ልቀቅ ይባላል፡፡ በተጋነነ የኪራይ ዋጋ ሌላ አዲስ ተከራይ ይመጣል፡፡ በተለይ በጋራ የመኖሪያ ቤቶች አካባቢ የመሸጉ ደላሎች የንጉሥ ያህል ይፈራሉ፡፡ ባሻቸው ጊዜ የፈለጉትን ይፈጽማሉና፡፡ የቤት ውስጥ ሥራ የሚያከናውኑ ሠራተኞችም ሆኑ ቀጣሪዎች የሚዘወሩት በደላላ ነው፡፡ ደላላው የተሻለ ጥቅም የሚያገኝ ከሆነ ሠራተኛ ያፈናቅናል፡፡ ቀጣሪውን ለችግር ይዳርጋል፡፡ ተቀጣሪዎችንም ያለፍላጎታቸው ጭምር ያንገላታቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ብቻ ሕፃናትና አቅመ ደካማ ያሉዋቸው በርካታ ቤተሰቦች ኑሮአቸው ይመሰቃቀላል፡፡ ከጥቅሙ ባሻገር ማየት የተሳነው የደላላ ግብረ ኃይል ያገለገሉ መኪኖች ግብይት ውስጥ ገብቶ ከይዞታቸው ይልቅ ለቀለም ዓይነቶች ደረጃ በማውጣት የዋጋ ግሽበት ይፈጥራል፡፡ አይጥማ፣ ጉበትማ፣ ሻምፓኝ መልክ. . . እያለ ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ መኪኖችን ከተገዙበት ዋጋ በላይ እጥፍ እንዲያወጡ ያደርጋል፡፡ ከኢኮኖሚ ሕግጋት ጋር የሚጋጩ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ለምን ብሎ የሚጠይቅ የለም፡፡ በደላላ የተጠለፈ አገር ሆኗል፡፡

ከሕዝቡ የዕለት መሠረታዊ ፍጆታዎች ጀምሮ በተለያዩ መስኮች ውስጥ ዳሰሳ ሲደረግ የደላላ ክንድ ፈርጣማ ነው፡፡ የሸቀጦች እጥረት ሲፈጠር በደላላ መሪነት የዋጋ ንረት ዘመቻ ይጀመራል፡፡ ከያሉበት ሸቀጦች ተሰብስበው ይደበቃሉ፡፡ የግብይት ሥርዓቱ በነፃ ገበያ መርህ ይመራል ቢባልም፣ ገበያውን የሚገዛው ደላላ እንጂ አቅርቦትና ፍላጎት አይደለም፡፡ የደላላ ዋናው ተግባር አቅርቦትና ፍላጎትን ማዛባት ነው፡፡ በተለያዩ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው ጉዳይ አስፈጻሚ አድርገው የሾሙ የደላላ ግብረ ኃይል አባላት፣ በሙሰኛ የመንግሥት ሹማምንት ድጋፍ ሕዝብ ያስበዘብዛሉ፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ በቀጥታ በነፃ ማግኘት ያለበት አገልግሎት ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› በሚባሉ ደላሎች ወደ ሙስና ይመነዘራል፡፡ ከደላላ በስተጀርባ የመሸጉ የመንግሥት ሌቦች ደግሞ በኔትወርክ ተቧድነው አገሪቱን ያደሟታል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሕዝብና የመንግሥት ነው የተባለውን መሬት በቁጥጥር ሥር ያዋለው የደላላ ሠራዊት በሙሰኛ ባለሥልጣናት አይዞህ ባይነት እየታገዘ፣ የተለያዩ ሴክተሮችን በማመስ ሕዝብና አገር እያስጮኸ ነው፡፡ ታዲያ ምን ይደረግ?

መልሱ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ድለላ በሕግ የበላይነት ሥር እንዲመራ ማድረግ፡፡ ጠንካራ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ በማውጣትና ተቆጣጣሪ ተቋም በመሰየም በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንደ ሠለጠኑት አገሮች እንዲሠራ ማድረግ፡፡ የታክስ መረቡ ውስጥ በማስገባት ተገቢውን የግብርና የቀረጥ ግዴታውን እንዲወጣ ማስገደድ፡፡ ድለላ በዕውቀት የሚመራ ሙያ እንደመሆኑ መጠን ባለሙያዎች በተቋማዊ መንገድ እንዲሰማሩበት መደረግ አለበት፡፡ ድለላ የሥራ አጦች መሰባሰቢያ ሆኖ ሕዝብና አገር የሚጉላሉበት እንዳይሆን፣ ጡንቻቸውን ያፈረጠሙ ወረበሎች የሚንጎማለሉበት የሕገወጦችና የማፊያዎች ዋሻ ሆኖ እንዳይቀጥል መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ አዲሱ ትውልድ መቀረፅ ያለበት በዕውቀትና በሙያ ሥነ ምግባር መሆን ሲገባው በስመ ኮሚሽን የሌብነት አጋፋሪ መሆን የለበትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ሕገወጥ ድርጊቶች የሚፈጸሙት ተቆጣጣሪ በሌለው የድለላ መረብ ውስጥ ነው፡፡ ከሕገወጥ የጦር መሣሪያ እስከ አደንዛዠ ዕፅ ዝውውር ድረስ ያለው አስከፊ ተግባር የደላላ መርገምት ነው፡፡ በሕገወጥ ሰዎች ዝውውር አማካይነት ሕይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች የደላላ ሰለባዎች ናቸው፡፡ ይህንን መረን የለቀቀ የድለላ መስክ በሕግ የበላይነት ሥር መምራት አለመቻል ይዋል ይደር እንጂ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡ በሥርዓተ አልባ ድለላ የሚመራ አገር ዕርባና አይኖረውም፡፡ እሴት ሳይጨምር ሕዝብና አገር የሚዘርፍ ኃይል ደግሞ በሕግ ሊዳኝ ይገባዋል፡፡ በዓለም የተከበረ ሙያ አገር ሲያጠፋ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ አይደለም፡፡ የአገሪቱ ምሁራንም ቢሆኑ የደላላ ሰለባ በመሆናቸው የበኩላቸውን ማለት አለባቸው፡፡ ሕዝብም መንግሥት ይህንን ሥርዓተ አልባ የደላላ ግብረ ኃይል እንዲያስታግስ ግፊት ማድረግ አለበት፡፡ በደላላ አገር ተጉላላ!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እንዲሠማሩ የሚፈቅድ መመርያ እየተዘጋጀ ነው

በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...

አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚለዋወጡ ስትራቴጂዎች እንደሚኖሩት ዕውን ቢሆንም፣ በየጊዜው መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን መለዋወጥ ግን አይችልም፡፡ ‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› የሚለው መጽሐፍ...