Tuesday, March 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹ስምዎ ማን ነው?›› ወይስ ‹‹ስምዎ ምንድን ነው?››

በልዑል ካሕሳይ

ኣንድ ጊዜ ኣንድ ወዳጄ የኣንዲትን ትንሽ ልጃገረድ ስም የጠየቅሁበትን የኣማርኛ ኣባባል ሰምቶ በኣግርሞት ኣረመኝ። የወዳጄ እርማት ከዓመታት በፊት በሁለት ካናዳውያን ወዳጆቼ መካከል የተከሰተ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ኣጠቃቀም እርማትን ኣስታወሰኝ። እኔ ልጅትን “ስምሽ ምንድን ነው?” እንደ ኣልሁ ኣት ነበር “ስምሽ ማን ነው?” ማለት እንደ ነበረብኝ ወዳጄ በለሆሳስ የኣሳሰበኝ። ነገር ግን ከኣማርኛ ከሰዋስው ኣንጻር እኔ ትክክል ነበርሁ። በተቃራኒ፣ በካናዳውያኑ ወዳጆቼ መካከል ተከስቶ የነበረው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ኣጠቃቀም እርማት ኣንደኛው “more better” የሚል የትንንሽ ልጆችን ኣነጋገር የሚመስል ድርብ ንፅፅርን ያሰለፈ ሰዋስዋዊ ወንጀል በመፈጸሙ ነበር። የኣማርኛ ቋንቋ ለእኔም ሆነ ለወዳጄ የኣፍ መፍቻ (የመጀመሪያ) ቋንቋችን በመሆኑ ቋንቋውን ኣስመልክቶ ብንተራረም ምንም ኣይነት የመሳለቅ ስሜት ኣንዳችን በሌላኛችን ላይ ኣሳድረን እንደ ኣልነበር ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ኣልነበረም። በተመሳሳይ፣ የእኔን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ኣጠቃቀም ህጸጾች ኣንዴም ለማረም ደፍረው የኣላወቁ ካናዳውያኑ ወዳጆቼ፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ለእነርሱ የመጀመሪያ ቋንቋቸው ስለ ነበር እርስ በርስ ለመተራረም ኣንዳችም ኣልተሳቀቁም ነበር። በማሕበረሰብ ውስጥ ኣንድን ቋንቋ እንደ ሁለተኛ ቋንቋቸው ለየሚጠቀሙ ሰዎች ሰዋስዋዊም ሆነ ዘዬ-ኣዊ እርማቶችን መስጠት በሰዎቹ ላይ ሊያመጣ ከሚችለው ምናልባት ስነልቦናዊ ተጽዕኖ ኣንጻር ብዙ የተለመደ ኣይደልም። እንዲያውም ሃሳባቸውን እስከ ገለጹ ድረስ ስህተቶቻቸውን ችላ ብሎ ማለፍ በብዙዎች ዘንድ የጨዋነት ምልክት ነው።

ጉዳዩ ግን ግራ-ኣጋቢ የሚሆነው እንደ ኢትዮጵያ በኣሉ የተዋበ ቋንቋ እየ ኣላቸው የቋንቋቸውን ሰዋስዋዊ ሕግጋት በስነጽሑፍም ሆነ በስነኣንደበት ሳያዳብሩ በቀሩ እና በተለያዩ ማህበራዊ እና ምጣኔሃብታዊ ምክንያቶች የቋንቋቸው የመግለጽ ብቃት እንደ ግመል እዳሪ እየ ኣደር ወደ ኋላ በሚቀርባቸው ሕብረተሰቦች ውስጥ ነው። በእነኚህ ሕብረተሰቦች ውስጥ የተሳሳተ የቋንቋ ኣጠቋቀም ከሚፈጥረው ግርታ ይልቅ፣ የቀና የቋንቋ ኣጠቃቀም የሚፈጥረው ግርታ እየከፋ መጥቶ ኣል።

የሰው ስም ግኡዝ ነው እንጂ እንደ የስሙ ባለቤት ህያው ኣይደለም። እንዲያውም በየኣማርኛ ሰዋስዋዊ ሕግ መሰረት፣ ቃሉ “ማን” በጅምላ ለማንኛውም ህያው ነገሮች ሳይሆን ለግለሰዎች (ለምሳሌ፦ ሰው፣ ኣምላክ፣ እና መላእክት) ብቻ ነው የሚያገለግል። ለምሳሌ፣ ‘ድመቱ ማን ነው?’ ኣንልም፤ ‘ሰውየው ማን ናቸው?’ ግን እንል ኣለን። ስም ኣንድን ሰው የሚወክል በራሱ ግን ሰብዕና የሌለው ነገር ነው። ሰዎች ከስም በተጨማሪ ሌሎች መለያዎች ሊኖሩ ኣቸው ይችል ኣሉ፣ ነገር ግን ቃሉን “ማን” በየትኛውም መለያዎች ላይ ማዋል ህጸጽ ነው። ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የኣንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃዎች ተማሪ እንደ ነበርሁ እንደ ሌሎች ተማሪዎች በየዓመቱ የመለያ ተራ ቁጥር ይሰጠኝ እንደ ነበር፣ ነገር ግን ማንም “ቁጥርህ ማን ነው?” ብሎ ጠይቆኝ ኣያቅ እንደ ነበር ኣስታውስ ኣለሁ።

በምትኩ ምን ማለት ይሻል ኣል? “ስምዎ ምንድን ነው?” ትክክለኛ ኣባባል ሲሆን፣ ከወዳጅ ዘመድ ግርታ እና ኣግራሞት ለመዳን ከፈለጉ ግን ባጭሩ ሁሌም የምንጠቀምበትን “ማን ልበል?” ን መጠቀም ይችል ኣሉ። ከሌሎች ኣማራጮች ኣንዱ ደግሞ “ስምዎን ቢነግሩኝ” ነው።

ኣንድ ሰው ግን ሰዎች እስከ ተግባቡ ድረስ በዘፈቀደ ቢነጋገሩ ምን ችግር እንደ የሚኖረው ይጠይቅ ይሆን ኣል። እንዲያው ኣንዳንዶች ቋንቋ የመግባቢያ መሳሪያ ስለ ሆነ ምንም ደንብ ሊወጣለት እንደ የማይገባ ይከራከር ኣሉ። በመሰረታዊ ደረጃ፣ በነዚህ በቀደሙት ሁለት ኣረፍተ-ነገሮች ውስጥ ከተካተቱት ኣንድምታዎች ጋር በኣብዛኛው እስማማ ኣለሁ። ማንም በትክክል የተግባቡ ኣካላትን “የተግባባችሁ የሰዋስው ሕግታትን በትክክል ሳትጠቀሙ ስለ ሆነ መግባባታችሁ ውድቅ ነው” ሊል ኣቸው ኣይችልም ወይም ኣይገባም። እንደዚሁም፣ ማንም በራሱ ኣነሳሽነት የቋንቋን ሕግጋት ሊደነግግ ኣይችልም። የሚገርመው ነገር ግን፣ እነዚሁ ሁለቱ ሃሳቦች ናቸው ቋንቋዎች መዳበር እና ሰዋስዋዊ ሕግጋትን ተከትለው መሄድ እንደ ኣለባቸው የሚያስገድዱ።

ለመሆኑ መግባቢያ እንዴት ነው የሚሰራ? በሕብረተሰብ ውስጥስ በኣንድ ቋንቋ ምክንያት ስልጠታዊ መግባባት መኖሩ እንዴት ነው የሚታወቅ? የስልጠታዊ መግባባት ጉድለት መዘዙስ ምንድር ነው? ኣፄ ኃይለ ሥላሴ ለምን ነበር ስለ “የሃገራችን የቋንቋ ድኽነት” የተናገሩ? ቋንቋ እንደ ማንኛውም ሃገራዊ ሃብት ሊበለጽግ ኣሊያም ሊኮሰምን ይችላል። ሰዎች ከጋርዮሽ ሕብረተሰብ የኣኗኗር ስልት ብዙም ሳይርቁ በኖሩባቸው ዘመናት፣ ስልጠታዊ መግባባት ብዙም ኣይፈልጉ ይሆን ነበር። ነገር ግን በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ለምንኖር ለእኛ በመግባባት ውስጥ የሚከሰቱ እንከኖች ኣያሌ ግላዊ፣ ማህበራዊ፣ ምጣኔሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ኣንድምታዎች ይኖሩ ኣቸው ኣል። ለምሳሌ፣ በኣማርኛችን ውስጥ ሰዋስዋዊ ጊዜያት የክንውኖችን ቅደም ተከተል በኣግባቡ እንድ ይገልጹ ስለ የማንጠቀምባቸው ንግግሮቻችን የተንዛዙ ብቻ ሳይሆኑ፣ ቁንጽል ኣንዳንዴም ኣስደንጋጭ መልእክቶችን ነው በኣብዛኛው የሚያስተላልፉ።

በኣንድ ወቅት ኣንድ የተከበሩ መልካም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቴሌቪዥን ቃለምልልስ ላይ “እኔ ተደባዳቢ ነኝ፤ ሰዎችን እፈነክት ኣለሁ፤ ጫትም እቅም ኣለሁ” እንደ ኣሉ ኣስተውዬ በጣም ነበር የደነገጥሁ። ከእይታው ሙላት እንደ ተረዳሁት፣ ሰውየው በእርግጥ ለማለት የፈለጉ “እኔ ተደባዳቢ ነበርሁ፤ ሰዎችን እፈነክት ነበር፤ ጫትም እቅም ነበር” ነበር።

ኣንዳንዴ ግን እንዲህ ኣይነቱ ሕጸጽ በህክምና እና በመሳሰሉ ስልጠታዊ መግባባትን በሚጠይቁ ሞያዎች ላይ ኣደገኛ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ በሽተኛው መርፌ “ተወግቶ ኣል” እና “ተወግቶ ነበር” ትልቅ የትርጉም ልዩነት ኣላቸው። እንደዚሁም፣ ኣንድ ሰው “ሞተ” (ወይም “ሞቶ ኣል”) እና “ሞቶ ነበር” ትልቅ የትርጉም ልዩነት ኣላቸው። እንዲያውም “እከሌ ሞቶ ነበር” ኣይባልም፣ ምክንያቱም አንድምታው “እከሌ ኣሁን ግን ከሞት ተነስቶ ኣል” ስለ የሚሆን። “እከሌ መርፌ ተወግቶ ነበር” ግን ይባላል፤ ነገር ግን ትርጉሙ ‘ኣሁን እከሌ ለሁለተኛ ዙር መርፌ ዝግጁ ነው፤ በመሆኑም በኣስቸኳይ ሌላ መርፌ ይሰጠው’ ማለት ሊሆን፣ ኣሊያም ‘በመርፌው ምክንያት ተፈወሰ’ ወይም ‘ሞተ’ ማለት ሊሆን ይችላል። ዞሮ ዞሮ ይህ ኣባባል የሚያሳየው፣ የመርፌ ውጋቱ የተከሰተ ከጊዜ ኣንጻር ኋላ ላይ ከተከስተ ወይም ሊከሰት ከሚገባው ኣንድ ሌላ ነገር በፊት መሆኑን ነው።

ነገር ግን ኣንድ ሰው “መርፌ ተወግቶ ኣል” ካልን፣ ኣሁናዊ የቅርብ እላፊ ስለ የሚሆን፣ በሽተኛው ሌላ መርፌ ሊሰጠው ኣይገባም በመሆኑም ከመርፌው ውጋት ወዲህ የተከሰተ እና ከሰዋስው ኣንጻር ሊዘገብ የተገባ ነገር የለም ማለት ነው። እንዲያውም፣ ይህ ሰው ሌላ መርፌ ቢደገመው እንደ መድሃኒቱ ጥንካሬ መጠን መርፌው ለህይወቱ ኣስጊ ሊሆን በት ይችል ኣል ማለት ይሆናል። የእንግሊዝኛ ቋንቋ የኣፍ መፍቻቸው ለሆኑ ሰዎች ይህን ኣይነተ የኣረፍተ-ነገሮችን ኣገባብ ለማስረዳት መሞከር ‘ለቀባሪ ኣረዱት’ ኣይነት የሚሆን ሲሆን፣ በሕብረተሰባችን ውስጥ ግን የሰዋስዋዊ ጊዜያት ጉዳይ እያደር እየተብላሸ ከመግባባት ይልቅ ኣለመግባባታችን እየጨመረ ይገኛል። በመሆኑም ኣንድ ጉዳይ ለመረዳት ወይም ለማስረዳት ሰዎች በቃላት ዙሪያ-ጥምጥም መሄድ ይኖርባቸው ኣል ኣሊያም ሙሉ ለሙሉ ሳይግባቡ ስህተቶች ይከሰታሉ።

የባዕዳን ቃላት በቋንቋችን ውስጥ እንደ ኣሸን መፍላት፣ ሰዎች ኣንደበታቸውን በፈቱበት ቋንቋ ሃሳባቸውን በጥራት እና በፍጥነት መግለጽ ኣለመቻላቸው፣ በቋንቋችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ኣለማስተማራቸው፣ ትልልቅ ሃግራዊ ተቋማት እና ታላላቅ መሪዎች ሳይቀሩ ከሞላጎደል እንግሊዝኛን በጉዲፈቻ ማዳበላቸው፣ ሰዎች ባዶ ቃላትን (“እንትን”) በንግግሮቻቸው ውስጥ ኣብዝተው መጠቀማቸው፣ ዜጎች በገዛ ሃገራቸው የባዕድ ቋንቋ ባለመቻላቸው፣ በሃኪሞች እና በህመምተኞች መካከል ኣስታራቂ የሆኑ ሃገራዊ የህክምና ቃላት መጥፋታቸው፣ በኣጠቃላይ ኣገራችን ኣጠቃላይ የሆነ የቋንቋ ቀውስ ውስጥ እንደ ኣለች የሚያመላክቱ ናቸው።

“ስምዎ ማን ነው?” ስለ ተባለ የዓለም መጨረሻ ኣይሆንም፣ ነገር ግን ‘የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ እንደ የሚያስታውቅ ሁሉ’ ቋንቋውን ያላዳበረ ሕብረተሰብም ካሉት መለያዎች ኣንዱ እንደዚህ ኣይነት ህጸጽ የተሞሉ ኣባባሎች ናቸው።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የ‹‹Proposed Language Reform for Ethiopia: Volume I (Orthography)›› [ውጥን የቋንቋ ህዳሴ ለኢትዮጵያ፦ ቅጽ  ስርዓተጽሕፈትደራሲ ናቸው። ጽሑፉ ከነአጻጻፉና ሆሄያት አጠቃቀሙ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles