Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዓለም ጤና ድርጅት ከመድኃኒት ጋር የተያያዙ ስህተቶችን የመቀነስ ዕርምጃውን ይፋ አደረገ

የዓለም ጤና ድርጅት ከመድኃኒት ጋር የተያያዙ ስህተቶችን የመቀነስ ዕርምጃውን ይፋ አደረገ

ቀን:

የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ስህተቶችን በአምስት ዓመት ውስጥ በግማሽ መቀነስ የሚያስችለውን ዕቅድ ማውጣቱን ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ አስታወቀ፡፡

ይህ የድርጅቱ የመድኃኒት ፈዋሽነትን የማረጋገጥ ዕርምጃ ከመድኃኒት ጋር የተያያዙ ስህተቶች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ የሕክምና ሥርዓት ድክመቶች ላይ በማተኮር በሚፈጠሩ ስህተቶች የሚደርስ ጉዳትን መቀነስን ያለመ ነው፡፡

ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ የሚፈጸም ስህተት (Medication Error) መድኃኒት ሲታዘዝ፣ ሲሸጥ ወይም ታካሚው እንዲወስደው ሲደረግ የሚፈጠሩ ስህተቶችን ይጨምራል፡፡ ብዙ ጊዜ ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ በሚፈጠር ስህተት ታካሚዎች ተጎጂ እንደሚሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ስህተቱ በተደጋጋሚና በስፋት የሚከሰት ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ ስህተቶች የሚደርስን ጉዳት ለመቀነስ ይቻል ዘንድ መድኃኒቶች የሚታዘዙበት፣ እንዲሁም የሚሠራጩበት መንገድ እንዲሻሻል እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን መድኃኒቶች የሚወሰዱበት መንገድ እንዲሻሻል መድኃኒትን በተገቢው መንገድ ካለመውሰድ ጋር በተያያዘ ስለሚፈጠሩ ችግሮች ግንዛቤ የመፍጠር ሥራም እንደሚሠራ ጠቁሟል፡፡

ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ በሚፈጠር ስህተት በተለይም የሕክምና አገልግሎት ሥርዓታቸው ባልዳበረ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል፡፡ በአሜሪካ እንኳ በዚህ ስህተት በቀን አንድ ሰው ሲሞት 1.3 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በዓመት ለጉዳት ይጋለጣሉ፡፡

ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮችም ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ መጠን ያለው ሞትና ጉዳት የሚመዘገብ ቢሆንም የዚህ ተፅዕኖ ግን በእነዚህ አገሮች ላይ እጅግ የበረታ መሆኑ በዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ተመልክቷል፡፡ ከመድኃኒት ስህተት ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደርሰው ኪሳራ በዓመት 42 ቢሊዮን የአማሪካ ዶላር እንደሆነ ይገመታል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ የሚፈጠር ስህተት የሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፍ በተጨማሪ የሰዎችን ሕይወት ሊያተርፍ የሚችል ሀብትና ግብዓትንም ያባክናል፡፡

ማንኛውም ሰው በሕይወት ዘመኑ አንድ አጋጣሚ ላይ በሽታ ለመከላከል አልያም ከበሽታ ለመፈወስ መድኃኒት ወስዷል ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን መድኃኒቶቹ በተሳሳተ መንገድ በመወሰዳቸው፣ ሥርጭታቸው ወይም አቀማመጣቸው ያልተጤነ በመሆኑና በሌሎችም ተያያዥ የመድኃኒት ስህተቶች ፈውስን ሳይሆን የባሰ ከፍተኛ ጉዳትን ሲያስከትሉ ይስተዋላል፡፡ ከመድኃኒት ጋር ተያያዥ የሆኑ ስህተቶች ደግሞ በሕክምና ባለሙያዎችም በበሽተኞችም ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡

እ.ኤ.አ. 2015 ላይ ከነርሶች ጋር በተያያዘ የመድኃኒት ስህተትን በሚመለከት በኢትዮጵያ የተሠራ ጥናት እንደሚያመለክተው ይህ ስህተት 56.4 በመቶ ያህል ይከሰታል፡፡ ለዚህ ስህተት የመድኃኒቶች የተሳሳተ መግለጫ፣ የቴክኒክና የጊዜ ስህተት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ የነርሶችን ብቃት ማሳደግ፣ ነርሶች ለሕመምተኛ መድኃኒት በሚሰጡበት ጊዜ ትኩረታቸውን ሊረብሽ ከሚችል ነገር ሁሉ እንዲጠበቁ ማድረግ ጥናቱ እንደ መፍትሔ ያስቀመጣቸው ናቸው፡፡ የመድኃኒቶች ደኅንነት ይረጋገጥ ዘንድ ነርሶችን በቅርበት መቆጣጠርም የተቀመጠ ሌላው ነጥብ ነው፡፡

ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ. 2012 ላይ በኢትዮጵያ የተሠራ ሌላ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ የሚፈጠር ስህተት ተደጋጋሚና አስከፊ ደረጃ ላይ መሆኑን አመልክቶ ነበር፡፡ እነዚህ ስህተቶች በተለይም በፅኑ ሕሙማን ክፍል (ICU) በስፋት እንደሚስተዋሉ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ እነዚህ ስህተቶች በብዛት የሚፈጠሩት መድኃኒቶች መሰጠት ባለባቸው ሳይሆን በሌለባቸው ጊዜ ሲሰጡ፣ ከነጭራሹ ሳይሰጡ ሲቀሩ፣ ካለመጠናቸው ሲሰጡና በሌሎችም ምክንያቶች ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ ከመድኃኒት ጋር ተያያዥ የሆኑ ስህተቶች ከሕክምና ባለሙያዎች መድከም፣ ከባለሙያ እጥረት፣ በቂ ሥልጠና ካለማግኘት የተነሳ ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ እነዚህ ስህተቶች ቀድሞ ሊያስቀሯቸው፤ ሊከላከሏቸው የሚችሉ በመሆናቸው ሕመምተኞች በትክክል የሚያስፈልጋቸውን መድኃኒት በተገቢው መንገድ፣ በተገቢው ጊዜ፣ በተገቢው መጠን እንዲወስዱ የሚያስችል የሕክምና አገልግሎት ሥርዓት መዘርጋትና አሠራር መከተል ዓይነተኛው መፍትሔ በመሆኑ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ይህን ዕቅድ በመጪው አምስት ዓመት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ዕርምጃውን አንድ ብሎ ጀምሯል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...