Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊለመኪና ቦታ የለንም

ለመኪና ቦታ የለንም

ቀን:

ፒያሳ ወርቅ ቤቶቹ አካባቢ፣ ከቀኑ አሥር ሰዓት ገደማ ነው፡፡ በአካባቢው ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ተፈጥሯል፡፡ በግራና በቀኝ ያሉት ንግድ ቤቶች ደግሞ ለራሳቸው እንኳን በቂ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ማጣታቸው ችግሩን እንዲከፋ አድርጎታል፡፡

መኪና ማቆም (ፓርክ) ማድረግ የሚቻለው በመንገዱ ከራስ መኮንን ድልድይ በኩል እየመጡ ከሆነ በስተግራ ብቻ ነው፡፡ ይሁንና የመጣው ይምጣ ያሉ መኪናቸውን በተከለከለው የመንገዱ ጥግ ደርድረው ወደየጉዳያቸው የሚሰማሩበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በጠባቡ የፒያሳ አስፋልት ለመኪና ማቆም በተፈቀደሙ ስፍራ አለልክ ተጠጋግተው የተደረደሩ መኪናዎችም ይታያሉ፡፡

መኪናቸውን ማቆም የሚፈልጉ ሰዎች ክፍት ቦታ ለማግኘት ቢያንስ መቶ ሜትር ድረስ መንዳት ይኖርባቸዋል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ቦታ አጥተው የሚመለሱ፣ ከአንዱ ጥግ ገብተው መኪና እስኪወጣ የሚጠባበቁ አሉ፡፡ የተጣደፉት ደግሞ መኪናን ካለአሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ባልተፈቀደው የመንገዱ ጥግ መኪናቸውን ያቆማሉ፡፡ ዕድል የቀናው ጉዳዩን ፈጽሞ ሲሄድ፣ አንዳንዶች ደግሞ ለትራፊክ ቅጣት ሲሳይ ይሆናሉ፡፡ እንዲህ ተጨናንቀው የቆሙትን መኪኖች የሚጠብቁት በሃምሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት አቶ ባባንጋ ሡሩር በሥራ ተወጥረዋል፡፡

- Advertisement -

ለካፊያው ጃንጥላ እንኳን ሳያጠሉ ከወዲያና ከወዲህ እየተሯሯጡ ትኬት ይቆርጣሉ፣ ከቆሙበት የሚወጡ አሽከርካሪዎች እንዳይጋጩም በእጅ ምልክት እየሰጡ ይመራሉ፡፡ ለአንዱ መኪና ትኬት እየቆረጡ፣ በርቀት የቆሙትን ተሽከርካሪዎችም በዓይናቸው ይቆጣጠራሉ፡፡ በዚህ አካባቢ ፓርኪንግ መሥራት ከጀመሩ አምስት ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ወደሥራው የገቡትም በጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበር ተደራጅተው ነው፡፡

ከቀኑ አሥር ሰዓት እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ መኪኖች እንደሚበዙ በመንገዱ ጠርዝ የቆሙትን መኪኖች በእጃቸው እየጠቆሙ ይናገራሉ፡፡ በሕገወጥ ቦታ ላይ የቆሙትን ተሽከርካሪዎች ትራፊክ ቢያገኛቸው ‹‹ታርጋ ይፈታባቸዋል›› ይላሉ፡፡ እሳቸው የሚጠብቋቸው መኪኖች መኪና ማቆም በተፈቀደበት ሥፍራ ለሚያቆሙት ብቻ ሲሆን፣ ከአንድ መኪና በ30 ደቂቃ 50 ሳንቲም ያስከፍላሉ፡፡

በትራንስፖርት እጦት ከተቸገሩት አዲስ አበቤዎች መኪና መግዛት ቅንጦት እንዳልሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ በከተማው ውስጥ ባለው የትራንስፖርት ችግር መኪናን እንደ አንድ መሠረታዊ ፍላጎት የሚቆጥሩም ብዙ ናቸው፡፡ ከመኖሪያ ቤት ቀጥሎ መኪና መግዛትን ትዳር ለመመሥረት እንደ አንድ መሥፈርት የሚያስቀምጡም ያጋጥማሉ፡፡

ለባለመኪኖች ደግሞ መኪናቸውን ፓርክ የሚያደርጉበት ቦታ ማግኘት ትልቁ ጥያቄ ነው፡፡ አሠልቺውን የትራፊክ መጨናነቅ ታግሰው በየመንገዱ እየቆሙ እሚፈልጉበት ቦታ ከደረሱ በኋላ መኪናቸውን የሚያቆሙበት ቦታ ፍለጋ ይባዝናሉ፡፡  አንገብጋቢው የፓርኪንግ ችግር ባለባቸው በአንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች ደግሞ ክፍት ቦታዎች ማግኘት ዘበት ነው፡፡ እርስዎ እንግዳ በሆኑበት አካባቢ መኪናዎን ለማቆም ቦታ ቢኖር እንኳን በቦታው ላይ ፓርክ ለማድረግ በአካባቢው ካሉ የፓርኪንግ ሠራተኞች ጋር ትውውቅ ካልኖሮት ከባድ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ‹‹ኖ ፓርኪንግ›› የሚል ማስታወቂያ በያዘ ብረት ቦታውን የሚያጥሩም ያጋጥማሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ የፓርኪንግ ቦታ ላይ ወንበር ይዘው በመቀመጥ ደንበኛቸው ወይም አካባቢው ላይ ሱቅ ወይም ቢሮ ያለው ሰው እስኪመጣ ተቀምጠው ለጥቂት ደቂቃ የመጣን ሰው እንኳን የሚያስገቡም ያጋጥማሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታ ችግር በከተማዋ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ባለው ችግር ባለመኪኖች ብቻ ሳይሆኑ እግረኞችም ጭምር መንገድ አጥተው ሲቸገሩ ይታያል፡፡ በእግረኞች መንገድ ላይ መኪኖች ይቆማሉ፡፡ ማቆም በተከለከለባቸው ሌሎች ቦታዎች የሚያቆሙም ብዙ ናቸው፡፡ የፓርኪንግ አገልግሎት የሚሰጠው በመንገድ ዳርና በሕንፃዎች ስር ነው፡፡ በስፋት እየተሠራበት የሚገኘው የመንገድ ዳር ፓርኪንግ ሲሆን፣ በመንገድ አጠቃቀምና በትራንስፖርት ፍሰት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከተማው የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ወደ 120 የሚጠጉ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ አገልግሎቱን በአሥሩም ክፍለ ከተሞች እየሰጡ የሚገኙት 120 ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በከተማዋ 19,000 የመንግድ ዳር የተሽከርካሪ ማቆሚያ ሥፍራዎች እንዳሉ ይገመታል፡፡

በ2008 ዓ.ም. የወጣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ማስተባበሪያ ጽሕፍት ቤት ጥናት እንደሚያመለክተው በመዲናይቱ የተመዘገበው የተሽከርካሪ ብዛት 426 ሺሕ ደርሷል፡፡ 73 በመቶ የሚሆኑት ከቀላል የተሽከርካሪ የሚመደቡ ናቸው፡፡ የከተማዋ ተሽከርካሪ በአሥር ዓመታት ውስጥ 169 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ይሁንና የፓርኪንግ አገልግሎት አሰጣጡ ከነበረበት ብዙም ለውጥ አላሳየም፡፡

የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን ማዘጋጀት ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን ለማሳየት የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፣ አንድ መኪና በአማካይ 95 በመቶ የሚሆነውን ጊዜውን የሚያሳልፈው በመቆም ነው፡፡ ይህንን አሃዝ መነሻ በማድረግ በከተማዋ ያለው አጠቃላይ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ፍላጎት ሲሰላ፣ የከተማዋን 2.76 በመቶ የቆዳ ስፋት አልያም 1,457 ሄክታር መሬት ነው፡፡

የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች በዚህ መጠን አስፈላጊ ቢሆኑም፣ ለፓርኪንግ ተብለው የሚተዉ ቦታዎች እምብዛም አይታዩም፡፡ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘውም የመንገድ ዳር የፓርኪንግ አገልግሎት ነው፡፡ አሠራሩም ብዙዎች የሚያማርር እንደሆነ አሽከርካሪዎች ይናገራሉ፡፡ በተለይም አብዛኛውን ጊዜያቸውን በመኪና ላይ ለሚያሳልፉ ሾፌሮች ከባድ ነው፡፡

ሾፌር ሆኖ መሥራት ከጀመረ 11 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ነፃነት ቶሎሳ ይባላል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ በባህዳርና በሐዋሳ ከተሞች በተመሳሳይ ሠርቶ ያውቃል፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባን ያህል የፓርኪንግ ችግር ያለበት ከተማ አጋጥሞት እንደማያውቅ ይናገራል፡፡

መርካቶ፣ ፒያሳ፣ ቦሌ በከተማዋ ከሚገኙት ሌሎች አካባቢዎች በተለይ የፓርኪንግ ችግር ያለባቸው ቦታዎት እንደሆኑ በምሬት ይገልፃል፡፡ ‹‹መርካቶ በጣም ትልቅ ችግር አለ፡፡ በሥራ ምክንያት ቢያንስ በሳምንት ሁለትና ሦስት ጊዜ እሄዳለሁ፤›› የሚለው ነፃነት፣ መኪናውን አንድ ቦታ አቁሞ ወደ ጉዳዩ ለመሄድ በጣም እንደሚቸገር ያማርራል፡፡

 እሱ እንደሚለው፣ በመርኮቶ የፓርኪንግ ቦታ ለማግኘት ማልዶ ካልሄደ አይሆንም፡፡ አልፎ አልፎ ቢኖርም አንዳንድ ቦታዎች ላይ ቅድሚያ የሚሰጡት ለሚያውቁት ሰው ነው፡፡ ‹‹እቃ ከምገዛበት ሱቅ በረንዳ ላይ ለማቆም እንኳ ችግር ነው፡፡ በሱቁ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰዎች የባለቤቱ መኪና ማቆሚያ ቦታ ነው ብለው ይከለክላሉ፡፡ ከተገኘ ራቅ ያለ ቦታ ማቆም ነው፡፡ እሱም ላይገኝ ይችላል፡፡ ያለኝ አማራጭ ደርቦ ማቆም ነው፡፡ እንደዚያ ሲሆን ደግሞ ትራፊክ ይቀጣል፤›› የሚለው ነፃነት፣ መርካቶ አካባቢ ብቻ ደርቦ በማቆም ሦስት ጊዜ ያህል ተቀጥቶ እንደሚያውቅ አስታውሷል፡፡

አለበቂ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራ የሚገነቡ ሕንፃዎች መብዛት ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አወሳስቦታል፡፡ ሕንፃዎች ሲገነቡ ማካተት ካለባቸው ነገሮች መካከል የመኪና ማቆሚያ ቦታ አንዱ ነወ፡፡ ይሁንና አብዛኛዎቹ ሕንፃዎች ይህንን እየተገበሩት አለመሆኑን በከተማዋ ተዘዋውረን ለመመልከት ችለናል፡፡ የሕንፃዎቹ የታችኛው ክፍል ለፓርኪንግነት ተብሎ የሚገነባ ቢሆንም፣ የመጠቀሚያ ፈቃድ ካገኙ በኋላ ተፈጻሚ የሚያደርጉት እምብዛም አይደሉም፡፡

ቦታውን ሸንሽነው ቢሮ የሚያደርጉ፣ ለሱቅነት የሚያከራዩና ሱፐርማርኬት የሚያደርጉ ጥቂት አይደሉም፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ቦታውን እኩል ከፍለው ለፓርኪንግና ለሌላ ጉዳይ የሚያውሉት አሉ፡፡ ከፊሉን የሕንፃው ተከራዮች መኪና የሚቆምበት እንዲሆን የሚያደርጉ ያጋጥማሉ፡፡ እንደዚያም ሆኖ የተከራዮቻቸውን መኪና በወጉ ለመያዝ ቦታ የሚያጥራቸውና ተከራዮችን የሚያጉላሉ አሉ፡፡

ቦሌ አካባቢ የሚገኝ ሕንፃ ነው፡፡ ካፌ፣ የልጆች መጫወቻ፣ ሱፐር ማርኬትና ሌሎችም አገልግሎት መስጫዎች አሉት፡፡ በመሆኑም በቀን በርካታ ደንበኞች የተለያዩ አገልግሎቶችን ፈልገው ወደ ሕንፃው ጎራ ይላሉ፡፡ ይሁንና ሕንፃው መኪናቸውን ይዘው የሚዘዋወሩ ደንበኞችን ለማስተናገድ በቂ የመኪና ማቆሚያ የለውም፡፡

የሱፐር ማርኬቱ ደንበኞች መኪናቸውን የሚያቆሙት ከሕንፃው ጎን ባለ ጠባብ ቦታ ላይ ነው፡፡ የፓርኪንግ ቦታ ያላገኙ ደንበኞች ደግሞ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት እና ከእሑድ በስተቀር መኪና ማቆም ክልክል መሆኑን ከሚያሳስበው ማስታወቂያ ስር ጥግ ይዘው ይቆማሉ፡፡

መኪናቸውን አልሆነ ቦታ ላይ አቁመው መሄድ ስለማይችሉ የሚፈልጉትን የሚታዘዟቸው እንደ ኃይሉ (ስሙ ተቀይሯል) ያሉ የፓርኪንግ ሠራተኞች ናቸው፡፡ በአካባቢው ያለውን የፓርኪንግ ችግር ሥራውን ከጀመረ አምስት ዓመት ወዲህ እንኳን ሲቃለል እንዳላየ ይናገራል፡፡ ከሕንፃው በስተጀርባ ያለው ቦታ ከጥቂት መኪናዎች በላይ የመያዝ አቅም የለውም፡፡ ይህ በአብዛኞቹ በከተማው ውስጥ በሚገኙ ሕንፃዎች ላይ የሚስተዋል ችግር ሲሆን የተለያዩ ጉዳዮች በምክንያትነት ይነሳሉ፡፡

አቶ ኤፍሬም ዘሩ የተለያዩ የፓርኪንግ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ይታወቃሉ፡፡ በከተማው ያለው የፓርኪንግ ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነገር ግን፣ ማኅበረሰቡ ስለ ፓርኪንግ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ ችግሩ በቀላሉ መስተካከል የሚችል ሆኖ ሳለ ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ፡፡ አንድ ሕንፃ ከሰባት ፎቅ በላይ ወለል ሲኖረው የደንበኞቹን መኪና ማስተናገድ እንዲችል ሁለት የመኪና ማቆሚያ ቤዝመንት (የታችኛው የሕንፃ ክፍል) ሊኖረው እንደሚገባ የሚጠይቅ ደንብ መኖሩን ይገልጻሉ፡፡

ይሁንና አብዛኛዎቹ በከተማው የሚገኙ ሕንፃዎች ይኼንን መሥፈርት እንደማይከተሉ ግልጽ ነው፡፡ አሁን ላይ አንዳንድ ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ ቢኖሩም፣ ለፓርኪንግ ከአንድ ቤዝመንት ያለፈ አይገነቡም፡፡ የመጠቀሚያ ፈቃድ ካገኙ በኋላ ደግሞ ለተለያዩ አገልግሎቶች ያውሉታል፡፡

ከዚህም ባሻገር ሕንፃዎች በትናንሽ ካሬዎች ላይ በሚገነቡበት ወቅት የመኪና ማቆሚያ ቦታን በተገቢው ለመጠቀም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ መኪኖች ወደ ቤዝመንቱ የሚገቡበት ራምፕ (መወጣጫ) ከፍታው ከ12 ዲግሪ ያልበለጠ መሆን አለበት፡፡ ይሁንና ሕንፃው የሚገነባበት ቦታ ጠባብ በሚሆንበት ጊዜ የራምፑ ከፍታ ከ12 ዲግሪ እንዲበልጥና ለመወጣጣት አስቸጋሪ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን አቶ ኤፍሬም ይናገራሉ፡፡ እንዲህ በሁኔታዎች ተገድደው ያልተመቸ መወጣጫ ከሚሠሩት ባሻገር፣ ባለማወቅና በግንዛቤ ችግር ተዳፋት የሆነ ራምፕ የሚሠሩም ብዙ ናቸው፡፡

አቶ ኤፍሬም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ውስጥ ከማስገባት ባሻገር የተለያዩ ሕንፃዎችን ፓርኪንግ ሥራ በኮንትራት ወስደው ያስተዳድራሉ፡፡ ይህም በከተማው ያለውን የፓርኪንግ ችግር በቅርበት እንዲያውቁት አድርጓቸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ በሕንፃዎች ላይ ለፓርኪንግ የሚተወው ቦታ የሕንፃዎቹ ደንበኞች እንዲጠቀሙበት ተብሎ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ይሁንና ባለው ችግር ተጠቃሚ ያልሆኑ ሰዎች መኪናቸውን ለደንበኞች ተብሎ በተዘጋጀ ቦታ ላይ አቁመው ይሄዳሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች ከፍተኛ መጣበብ የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች መኪናቸውን ከተፈቀደው ጊዜ በላይ አቁመው የሚጠፉ ሰዎች መኖርም ሌላው ፈተና ነው፡፡ ከአገልግሎቱ ተደራሽነት እጥረት ባሻገር በተለያዩ ቦታዎች የሚጠየቀው ክፍያ ወጥነት የጎደለው በመሆኑ ከፓርኪንግ ሰራተኞች ጋር እሰጣገባ የሚገጥሙ ደንበኞች አሉ፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ወቅት በሕንፃዎች የምድር ወለል አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በ30 ደቂቃ ከአንድ እስከ ሦስት ብር ድረስ ያስከፍላሉ፡፡ ለአንድ ሰዓት ቆይታ ደግሞ ከሦስት ብር እስከ ስምንት ብር ይጠይቃሉ፡፡ ይህ የዋጋ ምጣኔ በአገልግሎት ሰጪዎች የሚወሰንና በከተማው አስተዳደር ቁጥጥር የማይደረግበት ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ በበላይነት የሚመራው የመንገድ ዳር የመኪና ማቆሚያ አገልግሎት የዋጋ ተመን ደግሞ፣ በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ለ30 ደቂቃ ከተቀመጠው የዋጋ ምጣኔ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ነገር ግን ተመኑ በተሽከርካሪዎች ዓይነት የተለያየ ነው፡፡ ለአውቶሞቢሎች በ30 ደቂቃ 50 ሣንቲም፣ እስከ 70 ኩንታል ለሚመዝኑ ተሽከርካሪዎች አንድ ብር፣ እንዲሁም ከ70 ኩንታል በላይ ለሚጭኑና ከነተጎታች ለሚቆሙ ከባድ ተሽከርካሪዎች አራት ብር ያስከፍላል፡፡ ይሁንና አንዳንድ ከወጣው የዋጋ ተመን በላይ የሚያስከፍሉ ሕገወጥ አገልግሎት ሰጪዎች መኖራቸው ይነገራል፡፡

አቶ ትንሳኤ ወልደ ገብርኤል በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የመሠረተ ልማት የሥራ ክፍል ተወካይ ናቸው፡፡ ፅህፈት ቤቱ የተቋቋመው በ2007 ዓ.ም. ሲሆን፣ ተልዕኮው በከተማ ውስጥ ያለውን የትራፊክ ፍሰት ሥርዓት ማስያዝና ዘመናዊ ማድረግ ነው፡፡

በከተማ ውስጥ በቂ የተሽከርካሪዎች ማቆሚያ ስፍራ አለመኖር በከተማው ላለው የትራፊክ ፍሰት ችግር አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ችግሩን ለማስተካከል በከተማዋ ማስተር ፕላን ላይ ወደ 60 የሚጠጉ ቦታዎች ለፓርኪንግ ተለይተዋል፡፡ ከ60ዎቹ የተወሰኑትን ለማልማት ተችሏል፣ በመልማት ላይ ያሉም አሉ፡፡

ሦስት ዓይነት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች ሲኖሩ፣ የመጀመሪያው መደበኛ የሆነ የሕንፃ ላይ ተሽከርካሪ ማቆሚያ፣ አውቶማቲክ የተሽከርካሪ ማቆሚያና ክፍት ቦታ ላይ የሚዘጋጅ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ናቸው፡፡ አቶ ትንሳኤ እንደሚሉት፣ መገናኛ ሾላ ገበያ አካባቢ በአንዴ 1000 መኪናዎች ማስተናገድ የሚችል በ6200 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሕንፃ ላይ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ለመገንባት የዲዛይን ሥራው አልቋል፡፡ 530 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅና በ2011 ዓ.ም. ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አቶ ትንሳኤ ተናግረዋል፡፡

ሌላው ሜካኒካል ፓርኪንግ የሚባለው ዘመናዊ በኤሌክትሪክ የሚሠራ እንዲሁም ቦታና ጊዜ የማይፈጅ የፓርኪንግ ሥፍራ ነው፡፡ መገናኛ አካባቢ ሰሞኑን የተጠናቀቀው የፓርኪንግ ሥፍራ የዚህ ፕሮጀክት አካል ነው፡፡ ይህ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ 19 ወለሎች አሉት፡፡ 170 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ 90 ተሽከርካሪዎችን በአንዴ የማስተናገድ አቅም አለው፡፡

አንዋር መስጊድ አካባቢ በአንዴ 80 ተሽከራካሪዎችን መያዝ የሚችል፣ በ150 ካሬ ላይ ያረፈ ተመሳሳይ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ግንባታም ተጀምሯል፡፡ እስከ ነሐሴ 2009 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ አቶ ትንሳኤ ተናግረዋል፡፡ ቸርችል ጎዳና አካባቢም እንዲሁ በ120 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ 60 መኪኖችን መያዝ የሚችል ተመሳሳይ ፓርኪንግ ግንባታ ተጀምሯል፡፡ ግንባታው እስከሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት ወር ድረስ  ይጠናቀቃል፡፡ እነዚህ በጽሕፈት ቤቱ የሚከናወኑ ፓይለት ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...