Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትቱርካዊቷ ዐቢይ ለገሠ የቤጂንግ ኦሊምፒክ ሁለት ብር ሜዳሊያዎቿን ተነጠቀች

ቱርካዊቷ ዐቢይ ለገሠ የቤጂንግ ኦሊምፒክ ሁለት ብር ሜዳሊያዎቿን ተነጠቀች

ቀን:

  • የመሠረት ደፋር ነሐስ ወደ ብር ሜዳሊያ ከፍ ይላል
  • አበባ አረጋዊ የለንደን ኦሊምፒክ ነሐስ ሜዳሊያን ልታገኝ ነው

የዘመኑ አትሌቲክስ ላይ ባጠላው ዶፒንግ (አበረታች ንጥረ ነገር) ምክንያት፣ በርካታ አትሌቶች በኦሊምፒክና በዓለም ሻምፒዮና ያገኟቸውን ሽልማት እያሳጣቸው ነው፡፡

ኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (ኢአፌማ) ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ከዙሪክ ይፋ እንዳደረገው፣ በ5,000 ሜትር እና 10,000 ሜትር በቤጂንግ ኦሊምፒክ ሁለት የብር ሜዳሊያዎች ያገኘችው ዐቢይ ለገሠ የተከለከለው ዶፒንግ መውሰዷ በመረጋገጡ ውጤቷ ተሰርዟል፡፡

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ዐቢይ፣ ከኦሊምፒክ ሌላ በ1999 ዓ.ም. በኦሳካ በተካሄደ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10,000 ሜትር ባለድሏን ጥሩነሽ ዲባባን ተከትላ ሁለተኛ የወጣችበት ውጤቷም እንዲሁ ተሰርዟል፡፡

- Advertisement -

ዐቢይ ከ10 ዓመታት በፊት በኦሳካ ሁለተኛ ስትወጣ በተደረገላት ምርመራ የተከለከለውን ስቴሪዮድ ስታኖዞሎ ንጥረ ነገር በመውሰዷ ዳግም በተደረገው ፍተሻ በመረጋገጡ፣ ከ1999 ዓ.ም. እስከ 2001 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 2007-09) ያስመዘገበችው ውጤቶች በሙሉ ውድቅ ተደርገዋል፡፡

በዚህም መሠረት በቤጂንግ ኦሊምፒክ በ5,000 ሜትር ዐቢይን ተከትላ ሦስተኛ ወጥታ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ መሠረት ደፋር፣ ውጤቷ ወደ ሁለተኛነት ከፍ በማለቱ የብር ሜዳሊያ ስታገኝ፣ አራተኛ ወጥታ የነበረችው ኬንያዊቷ ሲልቪያ ኪቤት ነሐስ ታገኛለች፡፡

በኦሳካው የዓለም ሻምፒዮና በ10,000 ሜትር ሦስተኛ የወጣችው አሜሪካዊቷ ካራ ጉቻር ወደ ብር ሜዳሊያ ከፍ ስትል፣ እንግሊዛዊቷ ጆ ፓቬይ ሦስተኛ ሆናለች፡፡ በወቅቱ 7ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያዊቷ እጅጋየሁ ዲባባ ወደ 6ኛ ከፍ ብላለች፡፡

ከ10 ዓመታት በፊት የተገናኙት ጥነሩሽና ፓቬይ በሚያዝያ ወር በሚካሄደው የዘንድሮው የለንደን ማራቶን እንደሚፎካከሩ ቢቢሲ ሳይዘግብ አላለፈም፡፡

የዓለም አትሌቲክስን የሚመራው ኢአፌማ ባወጣው መግለጫ፣ የ34 ዓመቷ ዐቢይ ከነሐሴ 19 ቀን 1999 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 19 ቀን 2001 ዓ.ም. (ከኦገስት 25፣ 2007 እስከ ኦገስት 25፣ 2009) ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች በሙሉ መሠረዙን አውስቶ፣ አትሌቷን ከመስከረም 19 ቀን 2008 ዓ.ም. እስከ መስከረም 18 ቀን 2010 ዓ.ም. (ከሴፕቴምበር 29፣ 2015 እስከ ሴፕቴምበር 28፣ 2017) ድረስ ማገዱን ይፋ አድርጓል፡፡ ዐቢይ ከዓመት በፊት ስሟ ከዶፒንግ ጋር ተያይዞ በመጠርጠሯ ከውድድር ራሷን ማግለሏም ይታወሳል፡፡  

በሌላ በኩል በለንደን ኦሊምፒክ በ1,500 ሜትር ወርቅና ብር ያገኙት ሁለቱ ቱርካውያት አስሊ ካኪርና ጋምዜ ቡሉት ዶፒንግ መውሰዳቸው በመረጋገጡ ውጤታቸው ተሰርዟል፡፡

በመሆኑም በውድድሩ በሦስተኛነት ነሐስ አግኝታ የነበረችው የባህሬኗ ትውልደ ኢትዮጵያዊት መርያም ዩሱፍ ጀማል ወርቁን፣ ሩሲያዊቷ ታትያና ቶማሾቫ ብር ሜዳሊያውን ሲያገኙ፣ አምስተኛ ወጥታ የነበረችው የወቅቱ ኢትዮጵያዊት አበባ አረጋዊ (አሁን ስዊድናዊት) የነሐስ ሜዳሊያውን ታገኛለች፡፡

አበባ፣ ከአምስት ዓመታት በፊት ለንደን ባስተናገደችው 30ኛው ኦሊምፒያድ፣ በ1,500 ሜትር በአስተማማኝ አቋም የመጀመሪያውን (በ4 ደቂቃ 01.03 ሰከንድ) እና የፍጻሜ ግማሹን (በ4 ደቂቃ 04.55 ሰከንድ) ውድድሮች በአንደኝነት ማሸነፏና በፍጻሜው ፉክክር በቦታ አያያዝ ስህተት፣ አምስተኛ ሆና በማጠናቀቋ አሳዛኝ ተሸናፊ እንደነበረች ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ በቤጂንግ ኦሊምፒክ 4 ወርቅ፣ 1 ብር እና 2 ነሐስ በማግኘት በሜዳሊያ ሠንጠረዡ የነበረችበትን 18ኛነት የመሠረት ነሐስ ወደ ብር በማደጉ ደረጃዋ በአንድ ይሻሻላል፡፡ 17ኛ የነበረችው ሮማንያ ያስመዘገበችው 4 ወርቅ 1 ብርና 4 ነሐስ ነበር፡፡ በለንደን ኦሊምፒክ ያገኘችው በ3 ወርቅ፣ 2 ብርና 2 ነሐስ ላይ አንድ ነሐስ የአበባ አረጋዊ ቢታከልም የ22ኛነት ደረጃዋን የሚያስለውጥ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ በቤጂንግ ኦሊምፒክ (እ.ኤ.አ. 2008) ሴቶች በጥሩነሽ ዲባባና በመሠረት ደፋር የወርቅና ብር ሜዳሊያ መገኘቱ፣ ከውድድሩ ስምንት ዓመታት በፊት በሲድኒ ኦሊምፒክ (እ.ኤ.አ. 2000) ደራርቱ ቱሉና ጌጤ ዋሚ ያገኙትን የወርቅና ብር ታሪክ ተደጋሚ አድርጎታል፡፡

በለንደን ኦሊምፒክ በ3,000 ሜትር መሠናክል ነሐስ አግኝታ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷን ሶፊያ አሰፋ በአንደኛነት ቀድማት የነበረችው ሩሲያዊቷ ዮሊያ ዛራፖቫ ዶፒንግ መውሰዷ በመረጋገጡ፣ ከሁለት ወራት በፊት የሶፊያ ሽልማት ወደ ብር መለወጡ ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...