Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በጃክሮስ ኢንዱስትሪ አካባቢ የሚገኝ የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ የእሳት ቃጠሎ ከባድ ጉዳት አደረሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 በተለምዶ ጃክሮስ የኢንዱስትሪ መንደር በሚባለው አካባቢ የሚገኘው በዳና ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተገነባው፣ ዳና የጥጥ ፋብሪካ ላይ በደረሰ ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ ከባድ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ፡፡

ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ንጋት ላይ የፋብሪካው ሠራተኞች ወደ ሥራ ሲገቡ የፋብሪካው መጋዘን በጢስ ታፍኖ በመመልከታቸው መጋዘኑ ሲከፈት፣ 1,500 ኩንታል ጥጥ በእሳት መያያዙን እንደነገሯቸው የፋብሪካው ባለንብረት ሐጂ ሰሩር አህመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በ16 ሚሊዮን ብር የተገነባው ዳና የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ በ1996 ዓ.ም. ሥራ መጀመሩን የገለጹት ባለቤቱ፣ በአሁኑ ጊዜ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት እንደያዘ ጠቁመው፣ ባልታወቀ ምክንያት በተነሳው እሳት ግምቱ ለጊዜው ባይታወቅም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት አስረድተዋል፡፡

በመጋዘኑ ውስጥ 1,500 ኩንታል የሚሆን ለመዳመጥ የቀረበ ጥሬ ጥጥና የጥጥ መባዘቻ ማሽኖች እንደነበሩ የገለጹት ባለቤቱ፣ ሁሉም ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ምስጋናዬ ለእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ቁጥጥር ባለሥልጣን ማቅረብ እፈልጋለሁ፤›› ያሉት ሐጂ ሰሩር፣ እነሱ ፈጥነው ባይደርሱ ኖሮ ጉዳቱ ከፋብሪካውም አልፎ በሌሎች ንብረት ላይ ጉዳት ያደርስ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ከመጋዘኑ በተወሰነ ርቀት ላይ ለቦይለርና ለጀኔሬተር የሚውል 3,500 ሊትር ናፍጣ እንደነበር የጠቆሙት ባለ ሀብቱ፣ እሳቱ ወደዚያ ሳይዛመት የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን በመድረሱ ሊተርፍ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

መጋዘኑ ለሁለት ቀናት ሳይከፈት ዝግ ስለነበር ምናልባት በሙቀት ሳቢያ በራሱ ጊዜ እሳት ሊፈጥር ይችል ይሆናል ከሚል ትንበያ ባለፈ፣ አሁን ለጊዜው የአደጋውን መነሻ መናገር እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የባለሥልጣኑ የአደጋ ጊዜ ባለሙያዎችና የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎች ፈጥነው በመድረሳቸው ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ለማዳን ተችሏል፡፡ ሙሉ በሙሉ የተቃጠለውንና የተረፈውን የንብረት ግምት ለጊዜው መናገር ባይቻልም፣ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት ሳይቃጠል እንዳልቀረ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለሥልጣኑ አደጋውን ለመቆጣጠር 210 ሺሕ ሊትር ውኃና 80 ባለሙያዎች በማሰማራት በ11 ተሽከርካሪዎች በመጠቀም አደጋውን ለመከላከል መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡   

ዳና የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ 130 ሠራተኞች እንዳሉት የፋብሪካው ባለቤት ሐጂ ሰሩር ተናግረዋል፡፡ ተመሳሳይ ፋብሪካዎችም በጎንደር ከተማና በአዊ ዞን ቻግኒ ከተማ እንዳላቸውም አክለዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ ጥጥ በመዳመጥ ለበርካታ ዓመታት ወደ ውጭ ሲልኩ የቆዩ ቢሆኑም፣ በአሁኑ ጊዜ ግን አገር ውስጥ ለሚገኙ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ሐጂ ሰሩር አስረድተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች