አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ
ዋና ጸሐፊና የካፍ ፕሬዚዳንት አማካሪ
አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ የተወለዱት በአዲስ አበባ ውስጥ በ1927 ዓ.ም. ነበር፡፡ አባታቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ የነበሩ ሲሆን፣ የክለቡን ተጫዋቾች ከትምህርት ቤት ወደ ስታዲየም ይወስዱ ነበር፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ከአባታቸው ጋር የመሆን ዕድል የነበራቸው አቶ ፍቅሩ በኋላ የስፖርት አስተማሪ ሆኑ፡፡ ከዚያም በ1949 ዓ.ም. በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኛ ሆኑ፡፡ ከስታዲየም የስፖርት ፕሮግራምችን ማሠራጨት የጀመሩትም እሳቸው ናቸው፡፡ ከዚያም በኢትዮጵያ ሬዲዮ የስፖርት ፕሮግራም ጀመሩ፡፡ በጊዜው ምንም እንኳ ለስፖርት ጽሑፎች የነበረው ፍላጎት ዝቅተኛ የነበረ ቢሆንም፣ ኤዲተሮችን በማሳመን ስፖርት ተኮር የሆኑ የተለያዩ ጽሑፎችን የተለያዩ ጋዜጦች ላይ ይጽፉ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. የ1960 የሮም የኦሊምፒክ ጨዋታዎች አጋጣሚ የኦሊምፒክ ታሪክን አሳታሙ፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ወደ ኮንጎ ተልከው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ ከዚያም የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽኖችን መርዳት ጀመሩ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሕዝብ ግንኙነት፣ የቴኒስና የእግር ኳስ ሊግ ዋና ጸሐፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ መርሕ መሠረት በ1960 ዓ.ም. ዳግም ሲደራጅ በዋና ጸሐፊነት ሠርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በ1960 እና በ1968 ዓ.ም. የ6ኛውና 10ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታን በማዘጋጀት ረገድ በልዩ ልዩ ኮሚቴዎች አባልነት ብዙ እገዛዎችን አድርገዋል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት አማካሪ የሆኑት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔን ከ39ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጋር በተያያዘ ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለውጭ አገር የጋዜጠኝነት ሙያዎ ይነግሩኛል?
አቶ ፍቅሩ፡- ከኢትዮጵያ ወደ ፈረንሳይ ፓሪስ ነበር የሄድኩት፡፡ እዚያም ለፍራንስ ፉትቦልና ኢኮፔ ጋዜጦች ሠርቻለሁ፡፡ በኋላ ግን በሁለት ቋንቋዎች እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ይታተም የነበረውን የራሴን ወርኃዊ መጽሔት ‹‹ኮንቲኔንታል ስፖርት›› ጀመርኩ፡፡ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚያሳትመው ኦሊምፒክ ሪቪው ዋና አዘጋጅ ነበርኩ፡፡ ለቢቢሲ፣ ለቪኦኤ፣ ለጀርመን ሬዲዮ እንዲሁም ለፍራንስ ኢንተርናሽናል ሬዲዮ ሠርቻለሁ፡፡ እንግዲህ የጋዜጠኝነት ሙያዬ ይኼን ይመስል ነበር፡፡ መጀመሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስፖርት ላይ የመጻፍ ፍላጎት አደረብኝ፡፡ በዚህ መልኩ የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን፣ እግር ኳስ ጨዋታዎችን፣ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ሊግን ላለፉት 14 እና 15 ዓመታት ዘግቤያለሁ፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ በዓለም አቀፉ ስፖርት ትልልቅና ዋና ዋና ውድድሮችን ዘግቤያለሁ ማለት እችላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የካፍ ልዑክ በመሆን ከአሥር ዓመታት በላይ ሠርተዋል፡፡ በካፍ የነበረዎ ጊዜ ምን ይመስል ነበር?
አቶ ፍቅሩ፡- በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ አማካይነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በመወከል በካፍ ልዑክ ወይም ኮሚሽነር ነበርኩ፡፡ ከዚያ ደግሞ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ሆንኩ፡፡ በዚህ የአፍሪካ እግር ኳስ እንዲተዋወቅ ተንቀሳቅሻለሁ፣ በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥም በበጎ ፈቃደኝነት ሠርቻለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- 39ኛውን የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ እንዴት ተመለከቱት?
አቶ ፍቅሩ፡- እንደሚታወቀው እንደ ግብፅ፣ ሞሮኮና ፊፋ ያሉ የውጭ ኃይሎች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ደግሞ የወቅቱን የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖን አልደገፉም ነበር፡፡ ስለዚህ በቅስቀሳው ወቅት የአፍሪካ አገሮችን ዞረው ነበር፡፡ ሒርዘን አዲስ አርፈው የነበሩት የአፍሪካ ልዑካን አብዛኞቹ በሙስና የተጨማለቁ ነበሩ፡፡ ያው አፍሪካ በሙስና የታወቀች ናት፡፡ ሁሌም ምርጫ ሲኖር ገንዘብ ሲሰጣቸው ድምጻቸውን ይሰጣሉ፡፡ እኔ በጣም የምጠላው ነገር ደግሞ የውጭ ኃይል መሣሪያ፤ መጠቀሚያ መሆንን ነው፡፡ ማርኬቲንግ ኤጀንሲው ለቴሌቪዥን ባለመብትነት የሚያስከፍለው ከፍተኛ ነው በማለት ግብፃውያን እንኳን በካፍ ላይ ተነስተው ነበር፡፡ ይህ የቲቪ ማሠራጨት መብት ያለጨረታ የተሰጠው ለኳታር ኩባንያ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም ግብፅ፣ ሞሮኮና ፊፋ ጉዳዩን ከምርጫ ጋር አገናኙት፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደግሞ የራሱን ፍላጎት ለማራመድ ሲል በሌላኛው ቡድን ነበር የቆመው፡፡ ኢትዮጵያ ሁሌም የምትደግፈው በብዙኃን አፍሪካ አገሮች የሚያዝ አቋምን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ምርጫው ፍትሐዊ ነበር ብለው ያስባሉ?
አቶ ፍቅሩ፡- በእውነት ዴሞክራሲያዊ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በሙስና ድምፅ ማግኘት የተቻለበት ነበርና፡፡ ስለማዳጋስካር፣ ላይቤሪያ፣ ጂቡቲና ሴራሊዮን እግር ኳስ ሰምተህ ታውቃለህ? ስለዚህ በፖለቲካዊ ሁኔታዎች በተወሰኑ ውሳኔዎች ላይ ልትተማመን አትችልም፡፡ በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ በአንድ ላይ አንድን ተወዳዳሪ በመደገፍ ድምፅ ለመስጠት ከስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ በመጨረሻው ሰዓት ግን ግማሽ የሚያህለው አፍሪካ ድምፁን ለሌላኛው ለመስጠት ወሰነ፡፡ ስለዚህ ማንንም መቆጣጠር አትችልም፡፡ ድምፃቸውን የሰጡት ለአንተ እንደሆነ ይነግሩኃል፣ እውነታው ግን በተቃራኒው ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- አፍሪካ አንድ ተወዳዳሪ ብቻ ሊኖራት የቻለው በምን ምክንያት ነው?
አቶ ፍቅሩ፡- ችግሩ አዲሱን ትውልድ የማሳደግ ሥራ ስለማይሠሩ ነው፡፡ አሁንም በኃላፊነት ላይ ያሉ ብዙ ያረጁ ሰዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ምርጫችን ሰፊ አይደለም፡፡ እዚህ የተመረጡት ሰዎች በሙሉ ጥሩ የሚባሉ አይደሉም፡፡
ሪፖርተር፡- የቀድሞውን ካፍ ፕሬዚዳንት ኢሳ ሃያቱን ከአዲሱ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ጋር እንዴት ያነፃፅሯቸዋል?
አቶ ፍቅሩ፡- የቀድሞው ፕሬዚዳንት በአካል ብቃት ትምህርት ላይ ልዩ ሥልጠና ያላቸው ናቸው፡፡ በስፖርት ሚኒስቴር ውስጥ ሠርተዋል፡፡ በካሜሮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊና ፕሬዚዳንት በመሆንም አገልግለዋል፡፡ የካሜሮን እግር ኳስ ቡድን አፍሪካን በዓለም ዋንጫ እንዲወክል ብቻም ሳይሆን የአፍሪካ ሻምፒዮን እንዲሆንም አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው፡፡ ኃላፊነቱን ከአቶ ይድነቃቸው ተሰማ የተቀበሉና የካበተ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ ሁሌም የአፍሪካ ፍላጎትን ሲያስቀድሙ የኖሩ ሰው ናቸው፡፡ በሌላ በኩል አዲሱ ፕሬዚዳንት የማዳጋስካር ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የነበሩ ናቸው፡፡ እንዲሁ የታጩና በሌሎች ዘመቻ መመረጥ የቻሉ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኢሳ ሃያቱ ለተጨማሪ ጊዜ ማገልገል ይችሉ ነበር፡፡ እየተባለ ስለሚነሳው ቅሬታ አስተያየትዎ ምንድን ነው?
አቶ ፍቅሩ፡- ሚዛናዊ ያልሆኑ መለኪያዎች አሉ፡፡ በአውሮፓ ተቀባይነት ያለው ነገር ለምን በአፍሪካ ተቀባይነት አይኖረውም? ለምሳሌ የሴፕ ብላተርን ጉዳይ ብንመለከት ለመጨረሻ ጊዜ ሲመረጡ 79 ዓመታቸው ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- የካፍን አቅም እንዴት ይገመግሙታል? ስለ ኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽኖችስ ወቅታዊ አቋም ምን ያስባሉ?
አቶ ፍቅሩ፡- በርግጥም ብዙ መሻሻሎች አሉ፡፡ በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ጊዜ ገንዘብ አልነበረም፡፡ አሁን ግን የቴሌቪዥን ሥርጭት መብት ገቢ ማስገኘት ችሏል፡፡ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ገንዘብ የሚሰጡ ቢሆንም፣ አሁን ፊፋም ካፍም ጥሩ ገቢ ያላቸው ተቋሞች ናቸው፡፡ ስለዚህም ከገንዘብ አንፃር አሁን ያለው ነገር የተሻለ ነው፡፡ ይኼ በመሆኑ እንደ ዳኞች ሥልጠና፣ የአሠልጣኞች ሥልጠናና መሰል ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ይደግፋሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስን ማስተዋወቅ ማሳደግ፣ ከተፈለገ በተለያዩ ቋንቋዎች የኢንተርኔት መረጃዎችን ማንበብ የሚችሉ አሠልጣኞችን ማሠልጠን ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በዚህ ረገድ የተዘጋጁ መጻሕፍትን ማግኘት የሚቻልባቸው መደብሮች የሉም፡፡ ስለዚህ እንደ እግር ኳስና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያሉ ቤተ መጻሕፍት ሊገነቡ ይገባል፡፡ ስፖርትን የሚያሳድጉና የሚያስተዋውቁ ብዙ ብቁ ባለሙያዎች ያስፈልጉናል፡፡ በማናጀሮች ደረጃ ስለ አትሌቲክስ የሚያውቁ ሰዎች ካሉበት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተለየ መልኩ ብዙዎቹ ፌዴሬሽኖች ብቃታቸው እስከዚህም በሆነ ሰዎች የሚመሩ ናቸው፡፡ ያለ ብቁ ባለሙያዎች ስፖርቱን ማሳደግ አይቻልም፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያዊው ይድነቃቸው ተሰማ ለ30 ዓመታት ያህል የካፍ ጥንካሬ የሆኑ ሰው ነበሩ፡፡ ስለ አቶ ይድነቃቸው አሻራ ሊነግሩን ይችላሉ?
አቶ ፍቅሩ፡- እሱ አሠልጣኜ ነበር፡፡ ብዙ ነገር የተማርኩት ከእሱ ነው፡፡ በጣም ጎበዝ የኢትዮጵያም የአፍሪካም ስፖርት አባት የነበረ ነው፡፡ የአፍሪካ ስፖርት ተቋማትን ይደግፍም ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- የእርሶ ዘመንና የአሁኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃ በንፅፅር ይንገሩን?
አቶ ፍቅሩ፡- በእኔ ጊዜ ብዙ ተጫዋቾች ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወጡ ነበሩ፡፡ እነ መንግሥቱ ወርቁ፣ አዋድ መሐመድ፣ ፍሥሐ ወልደ አማኑኤልና ሌሎችም ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተገኙ ነበሩ፡፡ ለኦሜድላ (ፖሊስ) እና ለንብ (አየር ኃይል) ይጫወቱ የነበሩ ልጆች ሁሉ ከትምህርት ቤት የተገኙ ነበሩ፡፡ ትልቅ ተሰጥኦ የነበራቸው ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ አሁን ግን በትምህርት ቤት ያለው ስፖርት እንደ ቀድሞው አይደለም፡፡ ትምህርት ቤቶችም ለስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የተመቹ አይደሉም፡፡ ልጆች እንኳ የሚጫወቱት መንገድ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች ሳይሟሉ ስፖርት በኢትዮጵያ እያደገ ነው ልንል አንችልም፡፡
ሪፖርተር፡- ታዲያ መፍትሔ የሚሆነው ምንድነው?
አቶ ፍቅሩ፡- የትምህርት ቤት ስፖርትን ማሳደግ ይኖርብናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዙ ፍላጎትና ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች መንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን ቦታ አላገኙም፡፡ ትምህርት ቤቶች የስፖርት ሜዳዎች ላይ ክፍሎችን እየገነቡ ነው፡፡ እግር ኳስ መጫወቻ፣ ሌሎችንም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ማዘውተሪያ ቦታ በትምህርት ቤቶች ሊኖር ይገባል፡፡ በአመራር ደረጃ የሚሳተፉ የስፖርት ባለሥልጣናት አስፈላጊው ዕውቀት ያላቸው አይደሉም፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለስፖርት ቦታ እንዲመድብ መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ስፖርትን ማዘውተር የሚቻልበት ቦታ ሳይኖር እንዴት ስፖርትን ማሳደግ ይቻላል?
ሪፖርተር፡- ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃና ምን መደረግ እንዳለበት አስተያየት ይኖርዎታል?
አቶ ፍቅሩ፡- የመጀመሪያው ነገር ስለ እግር ኳስ የሚያውቁ ሰዎችን ማምጣት ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ የወጣቶች ውድድሮች ማዘጋጀት ነው፡፡ ከ15 ዓመት በታች፣ ከ17 ዓመት በታችና ከ20 ዓመት በታች፣ እንዲህ ካልሆነ ሄደው ተጫዋቾችን የሚገዙበት ማምረቻ የለም፡፡ ወጣት ተጫዋቾችን መኮትኮት ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶችን ዝግጁ ለማድረግ የትምህርት ቤቶች ውድድር ማድረግም ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ቀጣዩ ዕርምጃዎ የሚሆነው ምንድነው?
አቶ ፍቅሩ፡- አሁን ዕድሜዬ ከ80 በላይ ነው፡፡ በቅርቡ ለኅትመት ይበቃሉ ብዬ ተስፋ ያደረግኩባቸው ሁለት መጻሕፍት ላይ እየሠራሁኝ ነው፡፡ ሁሌም ስለኢትዮጵያና አፍሪካ ስፖርት ደረጃ አስባለሁኝ፡፡ በመሠረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት በጣም ወደ ኋላ ቀርተናል፡፡ ስለዚህ ኳሱ እንዲያድግ ሁሉም በሚገባ የሚችለውን ማበርከት ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ ሊግ ያሉት ጠንካራ ክለቦች ሦስት ብቻ ናቸው፡፡ ደጋፊዎች ደግሞ እርስ በርስ የሚሰዳደቡ ናቸው፡፡ ይኼ የኢትዮጵያ ባህል ባለመሆኑ በመከባበር አብረን ልንጓዝ ይገባል፡፡