Tuesday, November 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሕዝብ ተሳትፎ ሲገደብ መንግሥት የሚናገረው አይደመጥም!

መንግሥት አገሪቱ በሁለት አኃዝ ስለማደጓ፣ በዴሞክራሲ ሒደት ውስጥ መሆኗን፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበሩን፣ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ የፌዴራል ሥርዓት መፈጠሩን፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መኖሩን፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ሽግግር መጀመሩን፣ ወዘተ ለሕዝብ ሲያስረዳ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ስለማይጣጣም የመደመጥ ደረጃው ዝቅ ያለ ነው፡፡ የሕዝብ ቀጥታ ተሳትፎ ወይም ውክልና በበቂ ሁኔታ ስለማይታይ መተማመኑ በጣም የደከመ ነው፡፡ አንድ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ የከተማ ነዋሪ ወይም አርሶ አደር አገሩ በየዓመቱ 11 በመቶ እያደገች መሆኗ ሲነገረው፣ ከቢጤዎቹና ከራሱ አኗኗር ጋር እያነፃፀረ አለ የሚባለውን ዕድገት ለመቀበል ያዳግተዋል፡፡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ልሂቃን በሚግባቡበት ቋንቋ የሚቀርበው መረጃ ብዙ ትንታኔና ዝርዝር ማገናዘቢያ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከአንድ ዜጋ አኗኗር ጋር የማይገጥም መረጃ በመገናኛ ብዙኃን ተደጋግሞ ሲለቀቅ ቀልድ ይመስላል፡፡ ሕዝብ በአግባቡ የሚሳተፍበትና የሚወስንበት ሲሆን ግን የሚባለው ይገባዋል፡፡ ለጉዳዩም ባለቤትነት ይሰማዋል፡፡

የሕዝብ ተሳትፎ መገደብ የሚፈጥረው ሌላው ችግር፣ በተለያዩ አደረጃጀቶችና ኔትወርኮች ላይ ብቻ በመንጠልጠል ውሳኔ የሚደረስባቸው አገራዊ ጉዳዮች መፋለስ ሲያስከትሉ ነው፡፡ ከሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም ጋር የሚቃረኑ ውሳኔዎች የራሳቸው አጀንዳ ባላቸው ግለሰቦች፣ ባለሥልጣናት፣ ተቋማትና ኩባንያዎች የግል ወይም የቡድን ጥቅም ማስጠበቂያ ሲሆኑ ሕዝብ መንግሥትን ማዳመጥ አይፈልግም፡፡ የተወሰነ ቡድን አባላትንና ደጋፊዎችን ፍላጎት ብቻ የሚያስከብሩ ውሳኔዎች የሚወሰኑት፣ የሕዝብን ተሳትፎ በመገደብ ስለሆነ መደማመጥ ይጠፋል፡፡ ሕዝብ ከዕለት ተዕለት ኑሮው ጀምሮ እስከ አጠቃላይ አገራዊ ጉዳዩ ድረስ የባለቤትነት መብቱ ሲገፈፍ ቁጣ ይቀሰቀስበታል፡፡ አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ ይከሰታል፡፡ ነገር ግን ተሳትፎው ሁለንተናዊ ሆኖ የአገሪቱን ውሎና አዳር በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ከምንጩ ሲቀርብለት የባለቤትነት መንፈስ ይሰማዋል፡፡ ሕዝብ በመንግሥት የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቶች ላይ በየደረጃው ተሳትፎ ሲኖረው፣ ከመንግሥት ጋር የሚኖረው ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሠረተ ይሆናል፡፡ ሕዝብ ቀጣሪ፣ መንግሥት ተቀጣሪ መሆናቸው ይረጋገጣል፡፡

የአገሪቱን ኢኮኖሚ መንግሥት ለሕዝብ የሚተነትንበት መንገድና ሕዝብ ደግሞ የሚረዳበት አግባብ ለየቅል ናቸው፡፡ በድህነት ውስጥ የሚማቅቅ ሕዝብ አገሪቱ እያደገች ነው ሲባል፣ ይህንን ዕድገት የሚተረጉመው ጥቂቶች እንደሚቀማጠሉበት አድርጎ ነው፡፡ ከድሮ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ከተማው ውስጥ የተገጠገጡ ሕንፃዎችን እየተመለከቱ የጥቂቶች መክበሪያ እንደሆኑ ይሰማቸዋል፡፡ የከተሞች ዕድገት ቁሳዊ ነገሮች ላይ አተኩሮ ሰብዓዊው ጉዳይ ሲዘነጋ ሕዝብና መንግሥት አይጣጣሙም፡፡ ከነባር ይዞታቸው ላይ የተነሱ ዜጎች ከነቤተሰቦቻቸው የማይረባ ቦታ ሲጣሉና እዚህ ግባ የሚባል ካሳ ሳያገኙ ሲቀሩ፣ ዕድገት የሚባለው ነገር ይጎመዝዛቸዋል፡፡ መንግሥት ቢሮክራሲ ውስጥ በተሰገሰጉ አልጠገብ ባዮች አማካይነት በወከባና በትርምስ ከኖሩበት ቀዬ ሲፈናቀሉና የመደመጥ መብታቸው ሲገደብ፣ ለአገርም ሆነ ለልማቱ የባለቤትነት ስሜት አይኖራቸውም፡፡ የአንዲት አገር ልማትና ብልፅግና ባለቤት ሕዝብ መሆን ሲገባው፣ ተሳትፎው በመገደቡ ብቻ በርካታ ጥፋቶች ደርሰዋል፡፡ መኖሪያ ያጡ ዜጎች ክፍት ቦታዎች ላይ ከጊዜያዊ እስከ ቋሚ መጠለያዎች ሠርተው ለዓመታት ሲኖሩ ጉቦ ሲሰበስቡ የቆዩ ሹማምንት ዝም ተብለው፣ ምስኪኖቹ በዘመቻ መኖሪያቸው ፈርሶ ሜዳ ላይ ሲበተኑ ሕዝብና መንግሥት እንዴት ይግባባሉ? እንዴትስ መደማመጥ ይኖራል?

ላለፉት 25 ዓመታት የፌዴራል ሥርዓቱ በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ እንደተገነባ  ሲነገር ይሰማል፡፡ በእርግጥ ክልሎች የራሳቸውን መስተዳድር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤና የመሳሰሉትን በሚፈልጉት መንገድ እየተጠቀሙ ነው፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው በነፃ ፍላጎታቸው፣ በሕግ የበላይነትና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠው መነሳታቸውን ይገልጻል፡፡ ይህ የጋራ ጥቅምን፣ መብትንና ነፃነትን በተደጋጋፊነት ለማሳደግ የሚረዳ ሐሳብ ከወረቀት በዘለለ በተግባር አለ ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ሕዝብም በተደጋጋሚ ይጠይቃል፡፡ በመላ አገሪቱ ተዘዋውሮ መሥራት፣ መኖር፣ ሀብት ማፍራትና የመሳሰሉት መብቶች እክል ሲገጥማቸው በተለያዩ ጊዜያት ታይቷል፡፡  ከኖሩበት አካባቢ በግድ ከመፈናቀል ጀምሮ እስከ ሕይወት ማጣት ድረስ በተደጋጋሚ ተከስተዋል፡፡ የጠባብነት መንፈስ የተጠናወታቸው ኃይሎች ዜጎችን በገዛ አገራቸው ባይተዋር አድርገዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት የሚያሳምሙ ድርጊቶች በተከሰቱበት አገር ውስጥ መንግሥት በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን ዕርምጃ ሳይወስድ ከሕዝብ ጋር የሚኖረው ንግግር እንዴት አሳማኝ ይሆናል? እንዴትስ መደማመጥ ይቻላል?

ያለፉት 15 ዓመታት ውጣ ውረዶች በጥልቅ ተሃድሶው ሲገመገሙ፣ መንግሥትን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በጥልቀት ራሱን መመልከት አለበት፡፡ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጣቸው መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እየተጣሱ ዜጎች በተለያዩ መንገዶች ተንገላተዋል፡፡ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በስደስት ከአገራቸው ወጥተዋል፡፡ የድህነት መጫወቻ ሆነዋል፡፡ ሕዝብ የሚፈልገውን ባለማግኘቱ ለምሬት ተዳርጓል፡፡ የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳይሆኑ ሆነዋል፡፡ ብዙኃኑን ማዕከል ያላደረጉ ውሳኔዎች የቅራኔ መነሻ ሆነዋል፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን የሕዝብ ብሶት ማስተጋባት እንዲሳናቸው ተደርገዋል፡፡ አሰልቺ ፕሮፓጋንዳ እየታጨቁ ጥላቻ አትርፈዋል፡፡ የእኩል ተጠቃሚነት መብት ተንዶ ጥቂቶች ያበጡበት ምኅዳር ተፈጥሯል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የሀብት መቆናጠጫ መሣሪያ ተደርጎ ጥቂቶች ራሳቸውንና ቢጤዎቻቸውን ያላግባብ አበልፅገዋል፡፡ ከመንግሥት ግዥ ሌብነት፣ ከሕገወጥ መሬት ወረራ ዝርፊያ፣ ከግብርና ከቀረጥ ሥወራ፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ጀምሮ እስከ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ድረስ ሙስና የሕዝብና የአገር ጠላት ሆኗል፡፡ ይህንን በኔትወርክ የተሳሰረ ሙስና ከላይ እስከ ታች የማይበጣጥስ ተሃድሶ ፋይዳው ምን ይሆን? ካሁን በኋላስ ሕዝብን በቃላት ለመሸንገል ይሞከራል? ወይስ መራራውን እውነታ ተጋፍጦ የሕዝብን አመኔታ ማግኘት ይሻላል? ሕዝብ እያንዳንዱን ነገር በሚገባ ያውቃል፡፡ ተሳትፎው ቢገደብም ማን ምን እያደረገ እንደሆነ ያውቃል፡፡ የሚያውቀውን ሲዋሹት ደግሞ ማዳመጥ አይፈልግም፡፡

የሕዝብ ተሳትፎ ሲባል በአዳራሽ ስብሰባ በስመ ሕዝብ ተወካይነት የሚለፈፍ የታይታ ዲስኩር ማለት አይደለም፡፡ ሕዝብ ትክክለኛ ወኪሎቹ ሊሳተፉበት ከሚገባው ፓርላማ ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ድምፁ በአግባቡ መደመጡ ነው፡፡ በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሚወከሉባቸው ማኅበራት፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የአርሶ አደሮች፣ የነጋዴዎች ትክክለኛ ወኪሎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወዘተ በሚገባ ተሳትፏቸው ሲረጋገጥ የሕዝቡ ተሳትፎ ዕውን ይሆናል፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ከመሆኑም በላይ፣ ለአገር አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ይጠቅማል፡፡ ሕዝብና መንግሥት የሚደማመጡበት ሥርዓት የሚፈጠረው የሕግ የበላይነት ሲከበር ብቻ ነው፡፡ ሕግ ሁሉንም በአግባቡ የሚዳኝ ሲሆን ነው፡፡ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡ ጉልበተኛው ደካማውን የማያጠቃበት ሥርዓት እንዲፈጠር መደላድሉ የሚመቻቸው በሕግ የበላይነት ሥር ነው፡፡ ግለሰቦች ከሕግ በላይ ከሚሆኑበት ሥርዓት የሚገኘው አመፃ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብን ማዕከል ያላደረጉ ውሳኔዎች ለሕግ የበላይነት የማይገዙ ናቸው፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ የሚበለፅገው በሕግ የበላይነት ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ በዓይኑ የሚያየውና የሚነገረው አልጣጣም ሲሉት ጀርባውን ይሰጣል፡፡ እውነተኛው ነገር አፍጥጦ እየታየ ለመሸፋፈን ሲሞከር ተዓማኒነት ይጠፋል፡፡ ሕዝብ ባልተሳተፈበት እንዳለበት ሲነገር መተማመን አይቻልም፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ በሌለበት መንግሥት የሚናገረውን የሚያዳምጥ አይኖርም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...

ከድህነት ወለል በታች ከሆኑት አፍሪካዊያን ውስጥ 36 በመቶው በኢትዮጵያ ናይጄሪያና ኮንጎ እንደሚገኙ ተጠቆመ

‹‹ለሺሕ ዓመት በድህነት ውስጥ የነበረች አገርን በአሥር ዓመት ልንቀይር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...

አስጨናቂውን የኑሮ ውድነት የማርገብ ኃላፊነት የመንግሥት ነው!

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አንደኛው የኑሮ ውድነትን በተመለከተ ነበር፡፡...