የኢትዮጵያ ናይል ዲስኮርስ ፎረም ከፌዴራል በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ሕጋዊ ዕውቅና ባለማግኘቱ በዑጋንዳ ኢንቴቤ ካለው የናይል ዲስኮርስ ፎረም ዋና ቢሮ ከአባልነት ሊሠረዝ እንደሚችል ዛሬ ጥቅምት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ተገለጸ፡፡
የፎረሙ አባል ከሆኑ አሥር አገሮች ዘጠኙ በየአገራቸው ሕግ መሠረት በመመዝገባቸው ተጠቃሚ እየሆኑ ሲሆን፣ የኢትዮጵያው ግን ሕጋዊ ዕውቅና ባለማግኘቱ በፎረም ድምፅ ከመስጠትም ሊከለከል እንደሚችል አቶ አየነው ተሠራ በዑጋንዳ ኢንቴቤ የሚገኘው የናይል ዲስኮርስ ፎረም ሪጅናል ሞኒተሪንግ ኤንድ ኢቫሉዬሽን ኦፊሰር ተናግረዋል፡፡ ኦፊሰሩ ይህን የተናገሩት የኢትዮጵያ ናይል ዲስኮርስ ፎረም በደሳለኝ ሆቴል ባዘጋጀውና የተፋሰሱ አገሮች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚገጥማቸውን ችግር እንዴት መቋቋም ይችላሉ በሚለው ላይ በመከረበት ወቅት ነው፡፡