Monday, March 20, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሆቴሎችንና የሬስቶራንቶችን ነገር

በአገራችን በተለይም በአዲስ አበባ የሆቴል ኢንዱስትሪ እያደገ በመሄዱ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል ከማስገኘቱም በላይ፣ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ለባለሀብቱም ለመንግሥትም እጀግ ጠቃሚ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሆቴልና ቱሪዝም ገቢ በኩል ገና ጀማሪዎች እንደ መሆናችን ጉድለታችን ብዙ ነው፡፡ ለአንድ አገር የቱሪዝም ገቢ ወሳኝ የሆነ ድርሻ ከሚኖራቸው ውስጥ ዋነኛው የሆቴሎች አገልግሎት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህም ጋር የሆቴል ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማትም መስፋፋታቸው ሁለት ዋና ዋና ጥቅሞች ሲኖሩት፣ አንደኛው ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ማቅረብ ሲሆን፣ ሁለተኛው መንግሥትም ባለሀብቱም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል ነው፡፡ እነዚህ ተመጋጋቢ የሆኑ የሥራ ዘርፎች እስካሁን ድረስ በአገራችን ይበልጡንም በአዲስ አበባ በጉልህ የሚታይ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማስገኘታቸው ግልጽ ነው፡፡ በደርግ የመጨረሻዎቹ የሥልጣን ዓመታት ላይ በታወጀው የቅይጥ ኢኮኖሚ ፖሊሲን ተከትሎ አነስተኛ ሆቴሎች በግል ባለሀብቶች መገንባት ከጀመሩ በኋላ፣ ተስፋፍቶና እያደገ የመጣው ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በኋላ አገራችን በተከተለችው የነፃ ኢኮኖሚ ሥርዓት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተቋቋሙትን ሆቴሎች በቁጥር ማስቀመጥ ባይቻልም፣ በደፈናው ግን በርካታ ሆቴሎች እንደተሠሩ ለማወቅ ከተማችንን ተዟዙሮ ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡

ይሁንና የሆቴሎች መብዛትና ቁጥራቸው መጨመሩ ብቻ በራሱ ጥቅምና ዋጋ እንደሌለው አንዳንድ ባለሀብቶችንና ሆቴሎቻቸውን በማየት መገንዘብ ይቻላል፡፡ አዲስ አበባ እስካሁን ድረስ ከተከፈቱት ሆቴሎች ውስጥ ምናልባትም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አገልግሎታቸው ሲከፈቱ በነበረበት ደረጃ ላይ አይደሉም፡፡ አንዳንዶቹ ጭራሹንም እንኳን ሆቴላቸውን ሊያሻሽሉ፣ ሊያሳምሩና ጊዜው ከሚጠይቀው የአገልግሎትና የፋሲሊቲ ደረጃ ላይ ሊያደርሱት ይቅርና ሆቴላቸው ሲከፈት የነበረበትን የንፅህና የአገልግሎትና የሠራተኛ አያያዝ ማስቀጠል ባለመቻላቸው፣ ጥቂት የማይባሉ ሆቴሎች ከእነስማቸውና መፈጠራቸው እስከ መዘንጋት የደረሱ አሉ፡፡ ሆቴላቸው በተከፈተበት ዕለት ግን ለሚዲያ የሚሰጡት አስተያየት የሚያስጎመጅና የት ይደርሳል? የሚያስብል መሆኑን ወደኋላ መለስ ብሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንዱ ሆቴል ከሌላው ሆቴል የተለየ አገልግሎትና ፋሲሊቲ ለእንግዶቹ ወይም ለደንበኞች ይዞ እንደ መጣ ማውራት የተለመደ ነው፡፡ ይሁንና ከዓመት በኋላ ያ የተባለው ያ ጋዜጣ ላይ የተወራው ሁሉ ያልሆነ መሆኑን መታዘብ ይቻላል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ምን ይሆን? ለምንስ ወረተኞች እንባላለን? እንዴትስ የዛሬን ብቻ በመመልከት ለነገ መልካም ስምን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ ይሳነናል? በጣም የሚደንቅ ነገር ነው፡፡

ዛሬ በዓለም ላይ ገናና ስም ያላቸውና ከዘመን ወደ ዘመን የሚተላለፉ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ብራንዳቸውን በዓለም ዙሪያ ለማስፋፋትና ስማቸውን ለመትከልና ታዋቂ ለመሆን የበቁበት ሚስጥር ምንድነው? የሚለውን ማጥናትና ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ የአሜሪካኖችም ሆነ የአውሮፓ ምርጥ ሆቴሎች አሁን የደረሱበት ተመራጭ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያላሰለሰ ጥረትና የብዙ ዓመታት ልፋትና ኪሳራ ጠይቆ ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንስ የእኛ የአገራችን ሆቴሎች የራሳቸው ብራንድ ኖሯቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ የማይተላለፉበት ምክንያት ምን ይሆን? እላለሁ፡፡ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅፋቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ ይኼ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን መሰናክሎችን ሁሉ በመቋቋም ለትውልድ የሚተላለፍ የሆቴል ስምና ዝና ማትረፍ ይቻላል ብሎ መነሳሳት ያስፈልጋል፡፡ አሁን የሚከፈቱ ሆቴሎችን በምናስተውልበት ጊዜ ምን ያህል የዕለት ጥቅምን ብቻ በማሰላሰል እንደተጠመዱ መናገር ይቻላል፡፡ ብዙዎች ባለሀብቶች የሚገነቧቸው ሆቴሎች ምንም እንኳን እጅግ በርካታ ገንዘብ የፈሰሰባቸው ቢሆንም፣ ትርፋቸውንና ገቢያቸውን ወዲያውኑ በአንድ ጀንበር ካልመለሱ የማይደራደሩ፣ ሆቴላቸው በተከፈተ ወራት ወይም ዓመት ጊዜ ውስጥ ዶላር በዶላር ገቢ ካላገኙ የማይዋጥላቸው ብዙ ናቸው፡፡ አሳዛኝና የተሳሳተ የስግብግብነት ግምት፡፡ የነገን መልካም ስምና ዝና ለማግኘት ዛሬ ላይ ያሉ ጥቅሞችንና ገንዘብ ችላ ማለት ብልኃት ባይሆንም፣ በወረት የሆቴል ቢዝነስ መስገብገብ ግን የትም አያደርስም፡፡

በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሆቴል አመሠራረትና ማስፋፋት ግንባር ቀደም ሊባሉ የቻሉት በቀለ ሞላ ዛሬ ያንን ትጋታቸውንና ጥረታቸውን፣ እንዲሁም ወርቃማ ስማቸውን ያስቀጠለ ትውልድ እንዴት ሳያፈሩ ቀሩ? እላለሁ፡፡ በቀለ ሞላ ማለት እኮ እንደ ዛሬዎቹ ሒልተን ወይም ሸራተን ስያሜዎች ብራንድ ሊሆን የሚገባው ስም ነበር፡፡ አለመታደል ሆነብን እንጂ እነ ደሴ ሆቴል፣ ምዕራብ ሆቴል፣ ለም ሆቴል፣ ቃኘው ሻለቃ ሆቴል፣ አስፋወሰን ሆቴል፣ ወዘተ. . . ሁሉም ተስፋፍተውና አድገው ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ ብራንድ ስሞች ሊሆኑ ይገባ ነበር፡፡ እነዚያ ሆቴሎች ግን አሁን ምናልባትም ከሠፈር መጠሪያነት ወይም አቅጣጫ ከማመላከቻነት ውጪ የሆቴል አገልግሎታቸውም ሆነ ዕድገታቸው ተከድኖ ይብሰል ያሰኛል፡፡ የትናንቶቹን ትተን የዛሬዎቹን ሆቴሎች ስንቃኝም ነገን፣ ከነገ ወዲያን ወይም ትውልድን የተመለከተ ስምና ዝና ወይም ብራንድ ሳይሆን የዛሬን የራሳቸውን ጥቅምና ትርፍ ብቻ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ይህንን ትዝብትና አስተያየት ያሠፈርኩት እኔም አንድ ተራ የሆቴል ሠራተኛ በመሆኔ፣ በተለያዩ ሬስቶራንቶችና ሆቴሎች ላለፉት ሃያና ከዚያ በላይ ዓመታት በመቆየቴ ትረካዬን አለፍ አለፍ እያልኩ ለመቀጠል ልሞክር፡፡ ሐሳቤ የማንንም የሆቴል ባለቤት ለማንኳሰስ ወይም ለመንቀፍ ወይም ለማስደሰት ብዬ ሳይሆን፣ ብዙ የሆቴል ሠራተኞች ለምንድነው ወደ ብራንድ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ውስጥ ለመሥራት የሚሽቀዳደሙት? የእኛ ሆቴሎችና አሠሪዎችስ ችግር ምን ይሆን? እኛስ የሆቴል ሠራተኞች ምን ዓይነት ችግሮች ይስተዋሉብናል? የሚለውን ለማየትና ለመተራረም እንዲረዳን በማሰብ በቅንነት የተሰጠ አስተያየት መሆኑ በቅድሚያ ይታወቅልኝ፡፡ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለጥናቴ እንዲረዳኝ ያህል አንዳንድ የታዘብኳቸውን ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ስማቸውን የምጠቅሰው ምናልባትም ዛሬ ከገበያው ውጪ የሆኑትን ቢሆንም፣ የማልጠቅሳቸው ደግሞ አሁንም እንደ ነገሩ በእንቅስቃሴ ላይ ቢመስሉም መልካም ያልሆነ ስማቸውን የበለጠ መልካም እንዳይሆን እንዳያደርግባቸው በሚል ነው፡፡ አራት  ሬስቶራንቶችን ግን ስማቸውን በመጥቀሴ የበለጠ እንዲተዋወቁ ያግዛቸው ይሆናል፡፡ በአዲስ አበባ በአሁኑ ጊዜ ከስምንት ያላነሱ ብራንድ ያላቸው ወይም ዓለም አቀፍ ስያሜ ያላቸው ሆቴሎች ይገኛሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ሆቴሎች ውስጥ ተቀጥሮ ለመሥራት እንደ ማንኛውም ዜጋ ተጋፍቻለሁ፣ ተሽቀዳድሜአለሁ፣ ተወዳድሬአለሁ፡፡ ቢሆንም ግን አንዳቸውም ጋ ለመቀጠር አልተሳካልኝም፡፡ ይሁንና ወደ እነዚህ ሆቴሎች ለመቀጠር ያጋፋኝና ያሠለፈኝ ዋናው ምክንያት የተሻለ ክፍያቸውና ለሠራተኞቻቸው የሚያቀርቡት ፋሲሊቲ ነው፡፡

ብዙ ሠራተኞች ብራንድ ሆቴሎች መሥራት ለምን እንደሚፈልጉና ለምን እንደሚሽቀዳደሙ በምነጋገርበት ጊዜ የመጀመርያ መልሳቸው የሚሆነው፣ ‹‹እንዴ ሰርቪስ ቻርጁ ነዋ፤›› የሚል ነው፡፡ እርግጥ ነው ሁላችንም ለምንሠራው ሥራ ጥሩ ክፍያ ካጋጠመን ያለጥርጥር ምርታማ እንሆናለን፡፡ ታማኝ እንሆናለን፡፡ ሥራና የሥራ ሰዓታችንን በሚገባ እናከብራለን፡፡ ይኼ ምንም አያጠያይቅም፡፡ በአንፃሩ የእኛ አሠሪዎች ግን በተለይም ከአራት ኮከብ በታች ያሉት አብዛኛዎቹ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚንቀሳቀሱ ሆቴሎች፣ ሰርቪስ ቻርጅ ግማሽ በግማሽ ያህል እንዲያውም ከዚያ በላይም ጭምር የሚሆነውን ለሠራተኞቻቸው አይከፍሉም ማለት ይቻላል፡፡ በመሠረቱ ሰርቪስ ቻርጅ ማለት አሥርም ሆነ አምስት በመቶ የሚሰበስበው ከደንበኛው ላይ ለሠራተኛው እንዲሆን ተብሎ ነው እንጂ፣ አሠሪው ወይም ባለሆቴሉ ከዚያ ላይ ግማሽ በግማሽ ይውሰድ ወይም ይካፈል ማለት አይደለም፡፡ እርግጥ ሆቴሉ ለሚያወጣቸው ወይም ለሚተካቸው ተሰባሪም ሆነ ተለዋጭ ዕቃዎች መተኪያ የሚሆን ከአንድ እስከ ሦስት በመቶ ባልበለጠ ከሰርቪስ ቻርጅ ገቢ ላይ ተቀናሽ ማድረጉ ተገቢ ነው ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ከሠራተኛው እኩል ወይም ከዚያ በላይ ከሰርቪስ ቻርጅ ገቢ ላይ ባለሆቴሉ ከወሰደ ግን ከምስኪኑ ሠራተኛ ላይ እንደ መዝረፍ ይቆጠራል፡፡

እናም በዚህ የተነሳ ይመስለኛል ከስግብግብ ባለሆቴሎች ለመሸሽ ሲባል ሁልጊዜም ብራንድ ሆቴሎች በተከፈቱ ቁጥር እጅግ በርካታ ሠራተኞች ለመቀጠር የምንግተለተለው፡፡ እንዲያም ሆኖ እጅግ በጣም ጥቂት የሚባሉ ሆቴሎች የሠራተኛን አሥር በመቶ ሰርቪስ ቻርጅ ገቢን ሙሉ በሙሉ በሚያሰኝ ደረጃ ለሠራተኞቻቸው የሚያከፋፍሉ የተመሰገኑ ባለሀብቶች መኖራቸውንም መመስከር ይገባል፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ኃይሌ ገብረሥላሴ ጎዳና ላይ የሚገኝ ባለሦስት ኮከብ ሆቴል፣ አንድ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ያለ ባለአራት ኮከብ ሆቴል፣ አንድ ካዛንችስ አካባቢ የሚገኝ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ለሠራተኞቻቸው ታማኝ በመሆናቸው ምንጊዜም በመልካም ስም በመነሳታቸው የተነሳ፣ ክፍት የሥራ ቦታ በሚኖራቸው ጊዜ በከተማችን ውስጥ እንዳሉ ብራንድ ሆቴሎች ግፊያና ሠልፍ የማያጣቸው እነዚህ ሦስት ሆቴሎች የመልካም ስምና ዝና ምሳሌ ናቸው ማለት እችላለሁ፡፡ ስለዚህ በርቱ ለማለት እደፍራለሁ፡፡ ሆቴሎቹ ራሳቸውን ያውቃሉ፡፡ ምሳሌነታቸው ለሠራተኞቻቸው በሚከፍሉት ሰርቪስ ቻርጅ ብቻ አይደለም፡፡ በሆቴል ንፅህና፣ በሠራተኞች ዩኒፎርም፣ በተከታታይ ሥልጠና፣ በሠራተኞች ሕክምና፣ በመስተንግዶና በሌሎችም ቢሆን በተከፈቱበት ጊዜ የነበራቸው ሞራልና ጥንካሬ በታማኝነት የጠበቁ ናቸው ማለት ያስደፍራል፡፡

ስለዚህ ሌሎች ሆቴሎች እባካችሁ የሠራተኞቻችሁን ጥቅምና መብት አክብሩ እላለሁ፡፡ ምናልባትም መልካም ስምና ዝና ከመቃብር በላይ መዋሉንም አስቡበት፡፡ ወደ ሬስቶራንቶች ትዝብትና ምልከታ ስሄድ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ስምና ዕድሜ ጠገብ የሆኑ ሦስት ሬስቶራንቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሎምባርዲያ፣ ካስቴሊና አዲስ አበባ ሬስቶራንት ናቸው፡፡ እነዚህ ምግብ ቤቶች ለከተማችን ቀደምትና ብራንድ የሚሰኙ ሬስቶራንቶች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ሬስቶራንት ከአራዳ ጊዮርጊስ ማዶ የሚገኝ ታሪካዊ በሆነ የደጃዝማች ውቤ ቤት ውስጥ ከሃምሳ ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጠ ነው፡፡ በባህላዊና በታሪካዊ ቁሳቁሶችና ጌጣጌጦች የተዋበ፣ ባህላዊ ምግቦቻችን ለበርካታ ዓመታት ያስተዋወቀና መልካም ስም ያለው በመሆኑ ግንባር ቀደም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባት ሠራተኞቹ በምንና እንዴት ባለሁኔታ የተያዙ መሆናቸውን ባላውቅም፣ ከአንድ ሁለቴ ሦስቴ በተለያዩ ጊዜያት ከሰዎች ጋር በመሄድ ጣፋጭ ምግባቸውንና በጣም ጥሩ የሆነ መስተንግዶአቸውን ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ ትንሽ ቆየት ስላለ አሁን ያሉበትን ደረጃ ለመግለጽ ግን ያስቸግረኛል፡፡

ሎምባርዲያም እንዲሁ ከሃምሳ ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጠ ሜክሲኮ አደባባይ ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎን የሚገኝ ጥንታዊና ዝነኛ ሬስቶራንት ነው፡፡ የአውሮፓንም ሆነ ባህላዊው ምግቦችን የሚያዘጋጅ የከተማችን ብራንድ ምግብ ቤት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለመፍረስ አደጋ እያንዣበበት ነው መሰለኝ፤ የቀድሞው ዝነኛ ምግቡና መስተንግዶው እየቀነሰ የመጣ ይመስለኛል፡፡ በፊት ግን የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ሁሉ ይመገቡበት የነበረ የተመሰገነ ሬስቶራንት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስሙ ግን እስካሁን ድረስ የዘለቀ በመሆኑ ብራንድ ሬስቶራንት ሊሰኝ ይችላል፡፡ ሌላው እንደ አብነት የሚጠቀሰውና የራሱ ብራንድ ያለው ምናልባትም በአውሮፓውያን ዘንድ በጣም የሚታወቀው መሀል ፒያሳ መሐሙድ ሙዚቃ ቤት አጠገብ የሚገኘው ካስቴሊ ሬስቶራንት ነው፡፡ ይህ ስም ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ፣ ከሃምሳ ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጠ፣ በኢጣሊያን ኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚተዳደር ነው፡፡ ይህን የብዙ ዓመት ልምድ ያለውን ሬስቶራንት ውስጡ ገብቼ የመስተናገድ ወይም የማስተናገድ ዕድል ባይኖረኝም፣ ከሃያ ዓመት በፊት ተከፍቶ ከአሥር ዓመት አገልግሎት በኋላ ለመዘጋት የታደለው በጊዜው ዝነኛ የነበረው የጣሊያኑ ካናፔ ሬስቶራንት ውስጥ ስሠራ የተዋወኳቸው አንድ የቀዝቃዛ ምግቦች ባለሙያ የሆኑ ግለሰብ ያጫወቱኝን ማንሳት መረጥኩ፡፡ የምስክር ምስክር ሆኜ ማለት ነው፡፡

እኝህን ባለሙያ ከካስቴሊ ሬስቶራንት ያመጣቸው በ1988 ዓ.ም. ታኅሣሥ ወር ላይ ጣሊያናዊ ሰው ዓድዋ ድልድይ አካባቢ ‹‹ካናፔ ሬስቶራንት›› ሲከፍት ካስቴሊ ሬስቶራንት ውስጥ ያውቃቸው ስለነበር በጣሊያንኛ አግባብቶ፣ ጥሩ ደመወዝ ቆርጦላቸው አሸፈታቸው፡፡ ታዲያ የዚያን ጊዜ እንደነገሩኝ ከሆነ ሠላሳ ዓመታት ያህል የሠሩበትን ካስቴሊ ሬስቶራንት ትተው መምጣታቸውን ነው፡፡ ካስቴሊም እስካሁን ድረስ ከሃምሳ ዓመታት በላይ ዘልቆ እንደቆየ ማወቅ ይቻላል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ብራንድ ሬስቶራንት ሊያሰኘው ይችላል የምለው ለዚህ ነው፡፡ እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ ካስቴሊን የሚያስተዳድሩት የመሥራቾቹ ልጆች (ልጅ) ናት ተብያለሁ፡፡ አሁን ያሉበትን ደረጃ አላውቅም፡፡ ሬስቶራንቱ ውስጥ የሚሠሩት ሠራተኞች የቆዩና በልምድ የዳበሩ ጣሊያንኛ የሚናገሩ በመሆናቸው፣ ምናልባትም ከሬስቶራንቱ የሚያገኙት ጥቅም የማይጓደልባቸው ሊሆንም ይችላል፡፡ ለማንኛውም ካስቴሊ ሬስቶራንት፣ እንደነ ሸራተን፣ ራዲሰን ብሉ. . . ወዘተ ብራንድ ሬስቶራንት ነው ማለት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ የአሁን ዘመን ባለሀብቶች ሆቴላቸውን ከጊዜያዊ ጥቅምና ታይታ በማሳለፍ ለትውልድ የሚቆይ ስምና ዝና እንዲኖራቸው በመመኘት ከላይ ያነሳኋቸውን ምሳሌዎች ቢከተሉ ተመኘሁ፡፡ ብራንድ ሆቴል ማለት የግለሰብ ስሞች ሳይቋረጥና ሳይደለዝ አገልግቱንና አቅርቦቱን እያሻሻለና እያሳደገ ለትውልድ ማስተላለፍ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የእኛ የሆቴል ባለቤቶች ሠራኞቻቸውንና ደንበኞቻቸውን በመንከባከብ ብዙ ጊዜ አብረዋቸው እንዲቆዩ ማድረግ መልካም ነው፡፡ አሁን በያዝነው 2010 ዓ.ም. ብዙ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች በመዲናችን የመኖራቸው ያህል ወደፊትም ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸውና በአገራችን ባለሀብቶች የሚከፈቱ በርካታ ሆቴሎች ይኖራሉ ብለን እንጠብቃን፡፡፡ ስለዚህ መጪውን የውድድር ፈተና ለማለፍ የሆቴል ባለቤቶች ለሠራተኞቻቸው ጥቅምና መብት መሥራት አለባቸው፡፡ አይ ካሉ ሆቴላቸው ሕንፃው ብቻ ቀርቶ የአይጥና የነፍሳት መጫወቻ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ማስረጃ የሚሆኑት ቀደም ብለው የተከፈቱትን ሆቴሎች ተዟዙሮ ማየትና ደረጃቸውን መገምገም በቂ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ወደ ሻይ ቤት ደረጃ የወረዱ አሉ ማለት ይቻላል፡፡

በአይጥና በነፍሳት የተወረሩ ሆቴሎችን ማየት ብርቅ ላይሆንም ይችላል፡፡ ከጊዮርጊስ በላይ ያለ አንድ ስም ያለው ሆቴል በቂ ምስክር ይሆናል፡፡ ባለፈው የሆቴሎችና ቱሪዝም ግምገማ ወደ አንድ ኮከብ የወረደው ይህ ሆቴል ሕንፃው ብቻና ስሙ ብቻ ነው የቀረው፡፡ የአይጥና የበረሮ መንጋ ቢወረውም ሆቴሉ አሁንም ሥራውን ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን ያ ሆቴል የሥራ ማስታወቂያ ባወጣ ቁጥር አንድም ሠራተኛ ለውድድር የማይቀርብበት መሆኑ፣ ባለቤቶቹንም ሆነ የሆቴሉን ሥራ መሪዎች አሳስቧቸው አያውቅም፡፡ ያሳዝናል፡፡ መልካም ስም ከሌለ ምናልባትም ሆቴሉ ቢዘጋ እንኳን ሕንፃውን ለሌላ ቢዝነስ ማዋል ከታሰበም ባይመከርም ሊያወጣ ይችል ይሆናል፡፡ ስለዚህ እባካችሁ የሆቴል ባለንብረቶች ሆይ ገበያውን በማሸነፍ መልካም ስም በመገንባት ብራንድ የሆነ ስያሜ ይኑረን፤ በሠራተኞች በኩልም ቢሆን፣ አዲስ ሆቴል በተከፈተ ቁጥር ሲቪ (CV) አንጠልጥሎ መሄድ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ሆቴል ውስጥ ተረጋግተን ለመሥራት እንሞክር እላለሁ አበቃሁ፡፡

በተክልዬ ጀማነህ

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

                    

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles