Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኢትዮጵያ ናይል ዲስኮርስ ፎረም የገጠመው ፈተና

የኢትዮጵያ ናይል ዲስኮርስ ፎረም የገጠመው ፈተና

ቀን:

በናይል ተፋሰስ አባል አገሮች ለጥቁር ዓባይና ነጭ ዓባይ በሚገብሩ ወንዞች አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለሚመጣ ችግርና ለድህነት የተጋለጡ ናቸው፡፡

86 በመቶ የሚሆነውን ውኃ ለዓባይ ወንዝ በምትገብረው ኢትዮጵያም ለዓባይ በሚገብሩ ወንዞች አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች ከዚህ የተለዩ አይደሉም፡፡ ከየአካባቢያቸው ለም አፈር ታጥቦ ይሄዳል፣ ከመሠረተ ልማትም እምብዛም ተጠቃሚ አይደሉም፡፡

በ11ዱ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ለዓባይ በሚገድቡ ወንዞች አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን ሕይወት ለመለወጥ፣ ግንዛቤ ለመፍጠርና የባለቤትነት ስሜት ተሰምቷቸው አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ ለማስቻል፣ እ.ኤ.አ. በ2003 በኡጋንዳ ኢንቴቤ የናይል ቤዚን ዲስኮርስ ፎረም የተቋቋመ ሲሆን፣ ከኤርትራ በስተቀር የተፋሰሱ አሥር አባል አገሮችም በየአገራቸው ፎረም መሥርተው ሕዝባቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ፎረሙ በ2003 በኡጋንዳ ኢንቴቤ ከተመሠረተ በኋላ የኢትዮጵያው ናይል ዲስኮርስ ፎረም እ.ኤ.አ. በ2005 መንቀሳቀስ የጀመረ ቢሆንም፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ሕጋዊ ዕውቅና ባለማግኘቱ እክል እየገጠመው መሆኑን የኢትዮጵያው ናይል ዲስኮርስ ፎረም ጥቅምት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. የፎረሙ አባላት ከሆኑ ሲቪል ማኅበራትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር፤ የአየር ንብረት ለውጥ በተፋሰሱ እያደረሰ ስላለው ጉዳትና መወሰድ ስላለበት ዕርምጃ በመከረበት ወቅት ተገልጿል፡፡

በኡጋንዳ ኢንቴቤ የሚገኘው የናይል ዲስኮርስ ፎረም ሪጅናል ሞኒተሪንግና ኢቫሉዌሽን ኦፊሰር አቶ አየነው ተሠራ እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያው ናይል ዲስኮርስ ፎረም በአገር ውስጥ ሕግ መሠረት ሕጋዊ ዕውቅና ባለማግኘቱ በሥራው ላይ እክል ተፈጥሮበታል፡፡

ፎረሙ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2005 ሥራ በጀመረበት ወቅት የኢትዮጵያ ናይል ዲስኮርስ ፎረም አስተባባሪ ሆነው መሥራታቸውን በማስታወስ፣ ፎረሙ ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት በወቅቱ ለነበረው ፍትሕ ሚኒስቴር አስገብተው እንደነበር፣ በወቅቱ ከውኃ ሀብት ሚኒስቴር ለፍትሕ ሚኒስቴር አስተያየት እንዲሰጥ መደረጉንም ይናገራሉ፡፡ ሆኖም በፍትሕ ሚኒስቴር የሥራ ሽግሽግ ሲመጣ፣ አዲስ የመጣው አካል ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተያየት ጠይቆ ምላሽ ሳያገኝ የማኅበራትና በጎ አድራጎት ኤጀንሲ በመቋቋሙ ማመልከቻቸውን ወደ ኤጀንሲው አስገብተዋል፡፡ ሆኖም ፎረሙ ከሚሠራው አንፃር በምን መልኩ መመዝገብ እንደሚችል ሕጉ ላይ ግልጽ ባለመሆኑ መመዝገብ አልቻለም፡፡

በተፋሰስና በውጭ ግንኙነት ዙሪያ የሚሠሩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ፎረሙ ሥራውን እንዲሠራና እንዲጠናከር እያበረታቱ ሲሆን፣ ፎረሙም ሕዝቡን በማስተማርና በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ ላይ ያላትን ‹‹በፍትሐዊነት የመጠቀም›› አቋም በሄደበት ሁሉ በማስረዳት ረገድ የፎረሙ አባላት እንዲረባረቡም ድጋፍ ይሰጣል፡፡

ወደ አመዘጋገብ ሲመጣ ግን እስካሁንም ሕጋዊ ዕውቅና አላገኘም፡፡ የኢትዮጵያው ፎረም በክርስቲያን በጎ አድራጎትና የልማት ማኅበራት ኅብረት ሞግዚትነት እየተዳደረ ነው፡፡ ኅብረቱ በሰጠው ቢሮ እየተጠቀመም ሲሆን፣ ውል ሲፈራረምም በኅብረቱ ሥር ነው፡፡ ሕጋዊ ሥራዎችን የሚሠራውም በኅብረቱ ጥላ ሥር ሆኖ ነው፡፡

የኢትዮጵያው ፎረም በአገር ውስጥ በሕግ አግባብ ስላልተመዘገበም ከሌሎች አቻ አካላት ጋር ውልም ሆነ ስምምነት ማድረግ አልቻለም፡፡ ይኼ በፎረሙ ሥራ ላይ የፈጠረውን አሉታዊ ተፅዕኖ አስመልክቶ ላነሳነው ጥያቄ አቶ አየነው እንደመለሱት፣ ገንዘብ የሚሰጥ አካል በሕጋዊ መንገድ ካልተመዘገበና ሰርተፍኬት ከሌለው ድርጅት ጋር መሥራት የማይፈለግ መሆኑን እንደ አንኳር ጉዳይ ያነሱታል፡፡

ዕርዳታ ሰጪዎች ማንኛውም ድርጅት ዕርዳታ ሲጠይቅ በአገር ውሰጥ የተመዘገበበትን ሰነድ እንዲያቀርብ የሚጠይቁ ሲሆን፣ ፎረሙ ይኼንን ባለማሟላቱ ረጂ ወገናት ሸሽተውታል፡፡ ሞግዚት ቢኖርም ረጂው እንደዚህ ዓይነቱን አሠራር ስለማይፈልግ ከመስጠት ይቆጠባል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ገንዘብ ካልተገኘ ሠራተኛ መቅጠርም ሆነ ሥራውን አጠናክሮ መሄድ አይቻልም፡፡ ይኼም በሥራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡

የናይል ዲስኮርስ ፎረም በኡጋንዳ ከተቋቋመ በኋላ የዚህ ፎረም አባል የሆኑት ብሩንዲ፣ ዴሞክራክቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ በየአገራቸው ለመሰረቱት ፎረም ከየአገራቸው መንግሥት ሕጋዊ እውቅና ያገኙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በመንግሥቷ በኩል ሕጋዊ እውቅና አለማግኘቷን በመጥቀስ በኡጋንዳ ኢንቴቤ የሚገኘው  ሴክሬታሪያት ኢትዮጵያን ከአባልነት እንሰርዛለን እስከማለትም እየደረሰ ነው፡፡

አቶ አየነው፣ ‹‹የኡጋንዳው ቢሮ እንደ አቻ ፎረሞች ተመዝገቡና ሕጋዊ ሰነድ አምጡ፡፡ ካለበለዚያ ሕጋዊ ስላልሆናችሁ በምርጫም አትሳተፉም የሚል ሐሳብ እያንፀባረቀ ነው፤›› ብለዋል፡፡

86 በመቶ ያህሉን የዓባይ ውኃ የምትገብረው ኢትዮጵያ በፎረሙ ድምፅ አልባ ብትሆንም አዋጭ አይሆንም፡፡ 12 ዓመት ያህል ለመመዝገብ ጥረት ተደርጎ ባይሳካም፣ በምዝገባ ሒደት ላይ ያለ በሚልም እስካሁን በተከናወኑ ሥራዎች ላይ ድምፅ ከመስጠት የኢትዮጵያው ፎረም አልተከለከለም፡፡ ሆኖም በአገር ውስጥ ሕጋዊ እውቅና ቢያገኝ ኖሮ አሁን ከሚያከናውናቸው ሥራዎች በተሻለ ሊንቀሳቀስ ይችል እንደነበረም ያክላሉ፡፡

ሥራው በ2005 ሲጀመር ጽሕፈት ቤቱን አዲስ አበባ አድርጎ ዓባይን በሚገብሩ በአምስቱ ክልሎች ማለትም ትግራይ ተከዜ፣ አማራ ዓባይ፣ ዓባይንና ባሮ አኮቦን  በሚጋራው ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ ባሮ አኮቦ፣ ከኦሮሚያ ክልል የሚነሱት ከፊል የባሮ አኮቦ ገባሮች በሚገኙበት ስፍራ አምስት ጽሕፈት ቤት ይኖራል ተብሎም ነበር፡፡

ጽሕፈት ቤቶቹም ዋና ሥራቸው መሬት ላይ ያለውን ኅብረተሰብ በማስተባበር ወንዞቹን እንዲንከባከቡ፣ የተፋሰስ ልማት እንዲያመጡ፣ በተፋሰሱ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች ጠቃሚ ሐሳብ እንዲያመነጩ ኅብረተሰብን ያማከለ ልማት እንዲኖር ለማድረግ እስከታች ወርደው ኅብረተሰቡን በማሳተፍ መሥራትም ዓላማቸው ነበር፡፡ ሆኖም አዲስ አበባ ያለው ጽሕፈት ቤት እንኳን በደንብ እየሠራ አይደለም፡፡

የግብፅና የሱዳን ተሞክሮን በማንሳትም፣ ሁለቱ አገሮች ከዋናው ከተማቸው ካለው ጽሕፈት ቤት በተጨማሪ እስከታች ኅብረተሰቡ ድረስ ወርደው ከፍተዋል፡፡ ፎረሙም ከኅብረተሰቡ ጋር የተሳሰረ ሲሆን፣ ያገባኛል የሚልና ጠያቂ ማኅበረሰብ እየፈጠሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያው ፎረም አባላትም፣ መንግሥት ፎረሙን ሕጋዊ እንዲያደርገው እንዲጠይቁ፣ መንግሥትም የፎረሙን አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ተረድቶ እስካሁን በትብብር ከሚሠራው በተጨማሪ ሕጋዊ እውቅና እንዲሰጠውና ፎረሙ በተመቻቸ ሁኔታ እንዲሠራም አቶ አየነው ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የናይል ዲስኮርስ ፎረም ምክትል የቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ አማረ ከበደ፣ በፎረሙ በዓባይ ተፋሰስ ያሉ አገሮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች ባለሙያዎች ተሰባስበው ስለ ዓባይ ‹‹አንድ ወንዝ አንድ ሕዝብ›› የሚል መፈክር ይዘው መነሳታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይህንን አስመልክቶ በግብፅ፣ በካርቱም፣ በኡጋንዳ፣ በታንዛኒያ፣ በኬንያና በኢትዮጵያም ስብሰባዎች ተካሂደዋል፡፡

የኢትዮጵያው ፎረሙም በአገር ውስጥ በክልል ደረጃ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ተፋሰሱ በሚነካቸው አካባቢዎች ካሉ ነዋሪዎች ጋር ውይይቶች አካሂዷል፡፡ በተለይ ከአየር ፀባይ ለውጥና ከአፈር መከላት ጋር ተያይዞ የሚሠሩ ሥራዎች ሕዝቡን የሚመለከቱና የመንግሥትም ፕሮግራም ስለሆነ በዚህ ዙሪያ ተረባርቦ ለመሥራት መክረዋል፡፡ በተግባርም እየታየ ነው፡፡ በፎረሙ አባላት አማካይነት በአማራ ክልል በተፋሰሱ ውስጥ የአፈርና የውኃ ጥበቃ ሥራዎችና ዛፍ ተከላ እየተከናወነ ነው፡፡ በትግራይና በኦሮሚያም እንዲሁ የፎረሙ አባል ድርጅቶች ብዙ ሥራ እያከናወኑ መሆኑንም አቶ አማረ ይናገራሉ፡፡

ወደ መሬት የሚወርደውን የፎረሙ አባላት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሲሠሩ፣ ፎረሙ ደግሞ ግንዛቤ ማስጨበጥና ሥልጠና ላይ ይሠራል፡፡ ሆኖም አቶ አማረም በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ሕጋዊ ሆነው አለመመዝገባቸው ዕርዳታ በበቂ ለማግኘት እንቅፋት መሆኑን ይስማሙበታል፡፡ ሠርተፊኬት ስለሌለውም ችግሩን ለመቅረፍ ከክርስቲያን በጎ አድራጎት የልማት ማኅበራት ኅብረትና ከሲትዝን ሶሊዳሪቲ ፎር ፉድ ሴኪዩሪቲ ኤንድ ኢንቫይሮመንታል ፕሮቴክሽን ጋር እየሠሩ ነው፡፡

ፎረሙ ውኃን፣ ግብርናን፣ ውጭ ጉዳይን የሚነካ በመሆኑ በምን ሥር ይመዝገብ የሚለው ችግር የፈጠረበት ሲሆን፣ ይህም የተሻሉ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል የውጭ ዕርዳታ ለማግኘትም አላስቻለም፡፡ 

በበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ በኩል ‹‹አልመዘግብም›› የተባሉት ግን በኤጀንሲው በኩል እምቢታ ኖሮ ሳይሆን ከመመሪያው አኳያ እንደሆነ አቶ አማረ ይገልጻሉ፡፡ ፎረሙ አገር ውስጥም እየሠራ ድንበር የሚሻገር በመሆኑ የአገር ውስጥ ብሎ ለመመዝገብም ሆነ ዓለም አቀፍ ለማለት ችግር ሆኗል፡፡

ናይል ቤዚን ዲስኮርስ አሥር አባላት ያሉት ሲሆን፣ (ኤርትራ እየተሳተፈች ቢሆን 11 አባላት ይሆኑ ነበር) ሥራውም ከእነዚህ ጋር እየተቀናጀ ይሠራል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ያሰኘዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከኢትዮጵያው ፎረም ጋር በውጭ ሆኖ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ድርጅት ያስፈልገዋል፡፡ በኡጋንዳ ያለው ፎረም ግን የዚህ ዓይነት አደረጃጀት የለውም፡፡ የአገር ውስጥ ሆኖ ለመመዝገብም የኢትዮጵያው ፎረም አብዛኛው ሥራውን የሚያከናወነው ውጭ ካሉ ፎረሞች ጋር ሆኖ በኢትዮጵያ ተፋሰሶች ላይ መሆኑ ነው፡፡

ኡጋንዳ ኢንቴቤ ካለው ፎረም ጋር በጉዳዩ ላይ ቢወያዩም ኡጋንዳ ያለው ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሳይሆን ፎረም ሆኖ በመመዝገቡ የኢትዮጵያውን ችግር ሊፈታ አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያው ፎረም የኡጋንዳው ፎረም አባል እንጂ ኡጋንዳ የሚገኘው ቢሮ ቅርንጫፍም አይደለም፡፡ በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት በአገር ዕውቅና አግኝቶ መመዝገብ ዋናው መፍትሔ ነው፡፡ እስካሁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እያገዛቸው ሲሆን፣ አዲስ የተቋቋመው የደንና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ከሥራው ጋር አቀናጅቶ እንዲረዳቸውም ተስፋ ጥለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የማኅበራትና በጎ አድራጎት ኤጀንሲ የምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክተር አቶ ኃይለሥላሴ ገብረሚካኤል፣ በሕጉ በተቀመጠው መሠረት የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅት ለመሆን መስፈርት ካሟሉ ባንዱ መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ሆኖም የአገር ውስጥም የውጭውንም ቀላቅሎ መሥራት የሚችሉበት አግባብ የለም፡፡ በሌላ በኩል ቅርንጫፍ ከፍቶ መሥራት የሚቻልበት አግባብ አለ ብለዋል፡፡

በኤጀንሲው በኩል ለአገር ደኅንነትና ልማት የሚጠቅም ሥራ ሲመጣ፣ ድጋፍ የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩን የገለጹት ደግሞ የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ መስፍን ታደሰ ናቸው፡፡ አቶ መስፍን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በራሷ ሕግ የምትገዛ በመሆኗ ፎረሙም ሆነ ሌሎች ማኅበራት በሕጉ መሠረት ሥራቸውን አደራጅተው እንደ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ሊሠሩ ይችላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ናይል ዲስኮርስ ፎረም 86 በመቶ ውኃዋን ለዓባይ በምትገብረው ኢትዮጵያ ለሚኖሩ ዜጎች ግንዛቤ በመፍጠር፣ የተፋሰሱን ልማትና የአገሪቱን አየር ንብረት በመጠበቅ የሚሠራ ከሆነ ኤጀንሲው የሚደግፈው መሆኑን በመግለጽም፣ ሥራቸው ከልማት ጋር የተሳሰረ እስከሆነ ድረስ በአገር ውስጥ በጎ አድራጎት ተመዝግበው ቢሠሩና፣ ከናይል ተፋሰስ አገሮች ፎረም ጋር ለሚሠሩት ሥራ ደግሞ ውጭ ካሉት ፎረሞች ጋር ቢመክሩ ይሻላልም ብለዋል፡፡

በአገር ውስጥ የሚገኙ ተፋሰሶች ልማት ጋር አስተሳስረው ለሚሠሩት ሥራም ከውጭ ገንዘብ አግኝተው መሥራት የሚችሉበት አግባብ መኖሩን፣ ከዚህ ባለፈ ደግሞ አሉብን የሚሏቸውን ችግሮችና ሐሳቦች ይዘው ከኤጀንሲው ጋር በመመካከር መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡ የኤጀንሲው በር ለምክክርና ለመፍትሔ ክፍት መሆኑንም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...