Wednesday, March 22, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በሴራ ፖለቲካ አገር አይታመስ!

ግልጽነት በሌለበት አገር በርካታ ብሔራዊ ጉዳዮች ሚስጥር ይሆናሉ፡፡ ሚስጥራዊነት በበዛ ቁጥር እውነቱን ከሐሰት፣ ተጨባጩን ከምናባዊው መለየት ስለማይቻል መላምቶች ይበዛሉ፡፡ የመረጃ ፍሰቱ የተገደበ ስለሚሆንም ሐሜትና አሉባልታ የበላይነቱን ይይዛሉ፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የተንሠራፋው ችግር ይህ ነው፡፡ አገር የሚያስተዳድረው ገዥው ፓርቲ ግልጽነት ስለሚጎድለው፣ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ አይደለም፡፡ በመንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ ግልጽነት በመጥፋቱ ሳቢያ ብቻ የተጣራ መረጃ ማግኘት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ በዚህ ምክንያት ተጠያቂነት እየጠፋ በርካታ ጉዳቶች ይደርሳሉ፡፡ የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው ዜጎች የአገራቸውን ውሎና አዳር ለማወቅ ቢማስኑም፣ እውነትና ሐሰት ተደባልቀው ግራ ያጋባሉ፡፡ በዚህ ላይ ከየአቅጣጫው የሚሠራጩ የሴራ ንድፈ ሐሳቦች (Conspiracy Theories) አየሩን እየቀዘፉት ነው፡፡ አገር በሕግ የማትተዳደር ይመስል የሴራ ፖለቲካ በርትቷል፡፡ በግራና ቀኝ የተፋጠጡ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎችም የእዚሁ የሴራ ፖለቲካ ተዋናይ ሆነዋል፡፡ ወደ ፊት ከመራመድ ይልቅ ወደ ኋላ መንሸራተት የብዙዎቹ ፖለቲከኞች ባህሪ ሆኖ አገር ትታመሳለች፡፡

መሰንበቻቸውን በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች የተቃውሞ ሠልፎች ሲካሄዱ ሰንብተዋል፡፡ በብዙ ሥፍራዎች አንዳችም ጉዳት ሳይደርስ በሰላም ተጠናቀዋል፡፡ ነገር ግን በሰሜን ሸዋ ዞን ገብረ ጉራቻ አካባቢ ተሽከርካሪዎችና የተለያዩ ንብረቶች በቃጠሎ ወድመዋል፡፡ የሰው ሕይወት አልፏል፡፡ ይህንን የጥፋት ድርጊት የፈጸሙ ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰምቷል፡፡ ማንነታቸው ግን በወቅቱ መገለጽ ሲገባው ምንም አልተባለም፡፡ ለማኅበራዊ ሚዲያ ተዋናዮች ግን መልካም ግብዓት ሆኖላቸው በሴራ ትንተና ተጠምደዋል፡፡ ያሳዝናል፡፡ ባለፈው ሳምንት የኦሮሚያ ክልል የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ እየሠራ መሆኑን፣ ከሕዝብም ድጋፍ እየተደረገለት እንደሆነ አስታውቆ የክልሉ ነዋሪዎች በሕገወጦች የሚጠሩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዳይሳተፉ ማሳሰቢያ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ በሌላ በኩል የተጠሩት ሠልፎች ባለቤት እንደሌላቸውና ተሳታፊዎቹ በስማ በለው የተሰባሰቡ እንደሆኑ ሲነገርም ተሰምቷል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ቢናበቡ ኖሮ አላስፈላጊ ድርጊቶች እየተፈጸሙ የሰው ክቡር ሕይወት አይጠፋም ነበር፡፡ የአገር ሀብትም በከንቱ አይወድምም ነበር፡፡ ነገር ግን አገሪቱን እንደ ቁራኛ የያዛት የሴራ ፖለቲካ ግን መደበቂያ እያገኘ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ የመፍትሔ ያለህ ሲባል የሚያገረሽ ነውጥ እየተፈጠረ ሕዝብን እያሳቀቀ ነው፡፡ በድጋፍና በተቃውሞ ስም የጥላቻ ቅስቀሳ ውስጥ የተዘፈቁ ደግሞ ችግሩን እያባባሱ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እስከ መቼ ይቀጠላል?

በማናቸውም ጊዜያት ከሕዝብ ለመንግሥት ጥያቄዎች ይቀርባሉ፡፡ መንግሥትም ሕግና ሥርዓቱን ጠብቆ ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ የጥያቄዎቹ አቀራረብ ሕጋዊና ሰላማዊ እንዲሆን ደግሞ መንግሥት ምኅዳሩን የማመቻቸት ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያገኙ መሠረታዊ መብቶች በተግባር ሲረጋገጡ ለሴራ ፖለቲካ መጋለጥ አይኖርም፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉት ተቃውሞችና ነውጦች መፍትሔ ያልተገኘላቸው፣ በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩ መብቶች ሥራ ላይ መዋል ስላቃተቸው መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ እነዚህ መብቶች ሲገደቡ ለአመፅና ለሁከት በሮች ይከፈታሉ፡፡ ነገር ግን በሕጉ መሠረት መንቀሳቀስ ቢቻል ኖሮ፣ ጥያቄ ያለው ማንኛውም ወገን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ያቀርባል፡፡ ምላሹም ሕግና ሥርዓትን የተከተለ ይሆናል፡፡ ሕዝብና መንግሥት መደማመጥ ካቆሙ ግን የሰው ክቡር ሕይወት ይቀጠፋል፡፡ በአካልና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል፡፡ የሰላማዊ ዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባት መብት ይደፈጠጣል፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ሥራዎች ይደናቀፋሉ፡፡ በላባቸው ያፈሩትን ሀብት ሥራ ላይ ያዋሉ ዜጎች ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ከድህነት ጋር የተፋጠጠው ሕዝብ ለበለጠ መከራ ይዳረጋል፡፡  የሴራ ፖለቲካ ውጤቱ ይኼ ብቻ ነው፡፡

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዳልነው አርቆ አስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር አንዱ በሌላው ላይ ለመነሳት አስቦ አያውቅም፡፡ ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ ያገኘውን ተካፍሎ ከመብላትና ከመተሳሰብ አልፎ ተጋብቶና ተዋልዶ የሚኖር ነው፡፡ ይህንን የመሰለ አርዓያነት ያለው አስተዋይ ሕዝብ ለማይረባ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል ብቻ ማተራመስና የሚወዳትን አገሩን ህልውና ለመናድ መሞከር ኃጢያት ነው፡፡ ግራና ቀኝ ተሠልፎ በነገር መወጋጋትና የተለመደውንና አሰልቺውን ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ንትርክ ከማስቀጠል አልፎ፣ የንፁኃን ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ለአደጋ መዳረግ መወገዝ አለበት፡፡ ይልቁንም እስካሁን ድረስ የዘለቀው የተበለሻሸ የፖለቲካ ምኅዳር ተስተካክሎ፣ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች በእኩልነት የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ምዕራፍ እንዲከፈትና ለብሔራዊ መግባባት የሚረዳ ማዕቀፍ እንዲፈጠር መታገል ይገባል፡፡ ዴሞክራሲ ከሕጋዊነትና ከሰላማዊነት ጋር እንጂ ከጉልበት ጋር ዝምድና የለውም፡፡ ከአሁን በኋላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ነፃ እንዲሆን በተባበረ ድምፅ በማስተጋባት ተፅዕኖ ለመፍጠር መታገል የግድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ አገርና ሕዝብን እያተራመሱ የሶሪያንና የየመንን መንገድ መያዝ ጤንነት አይደለም፡፡ አመፅና ብጥብጥ አገር ሲያፈርስ እንጂ ዴሞክራሲ ሲያመጣ ታይቶ አይታወቅም፡፡ የሴራ ፖለቲካ ውጤቱ ጥፋት ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳላት ይገመታል፡፡ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ታዳጊዎችና ወጣቶች ናቸው፡፡ 30 ሚሊዮን የሚገመቱት በትምህርት ገበታ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ግርድፍ መረጃ የሚያሳየው በዚህ ትውልድ አማካይነት መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ነው፡፡ ይህ ለውጥ በውይይት፣ በክርክርና በድርድር ታግዞ መሠረት እንዲይዝ የሚያዋጣው መንገድ መጀመሪያ ለሕግ የበላይነት መገዛት ነው፡፡ ሁለተኛው የሕዝቡን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍላጎቶች በፍትሐዊ መንገድ ማስተናገድ ነው፡፡ ሦስተኛው በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ያገኙ መሠረታዊ መብቶች ያላንዳች መሸራረፍ ሥራ ላይ እንዲውሉ በማድረግ ለሐሳብ ነፃነት መደላድሉን ማመቻቸት ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ከፖለቲካ ወገንተኝነት በመላቀቅ፣ ዴሞክራሲያዊው ሒደት ፈር እንዲይዝ እገዛ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ገዥው ፓርቲና መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ለአገራቸው የሚያስቡ ዜጎች፣ ወዘተ. ከሴራ ፖለቲካ በመላቀቅ አገር ቀናውን ጎዳና እንድትይዝ ድጋፍ ያድርጉ፡፡ የአገር ጉዳይ ሁሉንም በጋራ ማስተሳሰር መቻል አለበት፡፡ ግትርነት፣ ጨለምተኝነትና ራስ ወዳድነት ይብቃ፡፡

የሴራ ፖለቲካ ትርፉ አንዱን ከሌላው ጋር በማጋጨት ለአገር ፋይዳ የሌለው ድርጊት መፈጸም ነው፡፡ በዚህ የተካኑት የአገሪቱ ፖለቲከኛ ነን ባዮችና በስመ ተንታኝነት ማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ መሽገው የተኮፈሱ አገርን የሚያጠፉ እንኩቶ ወሬዎች ላይ ተጠምደዋል፡፡ በመርዝ ምላሳቸው ያገኙትን እየሸነቆጡ በኢትዮጵያውያን መካከል መጠራጠርና መፈራራት በመፍጠር የአገርን ህልውና እየተፈታተኑ ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከመታገል ይልቅ ኢትዮጵያውያንን በዘር፣ በሃይማኖትና በመሳሰሉት በመለያየት የጠላት ዒላማ ለማድረግ እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ፡፡ በዚህ መሀል ንፁኃን ይሞታሉ፣ አካላቸው ይጎድላል፣ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለመከራ ይዳረጋሉ፣ የአገር አንጡራ ሀብት ይወድማል፡፡ እንዲህ ዓይነት አሳፋሪ ድርጊት ለኩሩ ኢትዮጵያውያን አይመጥንም፡፡ ይህ ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ በመሰሪዎችና በሴረኞች የሚደርስበት ግፍ ይበቃዋል፡፡ ይህች የአፍሪካውያንና የመላው ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት አገር ከሴራ ፖለቲካ ተላቃ ወደ ታላቅነቷ መመለስ አለባት፡፡ በአገርና በሕዝብ ላይ መቀለድ ይብቃ፡፡ በሴራ ፖለቲካ አገር አይታመስ!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሥጋቶች

ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ‹‹What Next for Ethiopia and its...

በትግራይ 28 አባላት የሚኖሩት የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት ተወሰነ

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ከሕወሓት ይሰየማል በትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ለማቋቋም...

ብልጽግና ፈተና ሆነውብኛል ያላቸውን አምስት ተግዳሮቶች ይፋ አድርጎ የአግዙኝ ጥሪ አቀረበ

ብልፅግና በነፃነት ስም በሚፈጸም ወንጀል ምክንያት በትግሉ ያገኘውን ነፃነት...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...

ዘምዘም ባንክ ለሴቶችና ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ

ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትን በማስተዋወቅ ቀዳሚ የሆነው...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...

የዜጎች ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ ጥበቃ ያስፈልገዋል!

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው ዘግናኝና አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቢገታም፣ በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የዜጎች ሰቆቃዎች በስፋት ይሰማሉ፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር...