Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልና የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አማካሪ የነበሩ ግለሰብ ተከሰሱ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልና የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አማካሪ የነበሩ ግለሰብ ተከሰሱ

ቀን:

በሶማሌ ክልል በተለያዩ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ በተለይም የፕሬዚዳንቱ አማካሪ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልና የሊበን ዞን መስተዳድር ምክትልና ዋና ኃላፊ በመሆን ይሠሩ የነበሩት አቶ መሐመድ መሐሙድ አደን ኢልሚ ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተከሳሹ ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ በሶማሌ ክልል የሊበን ዞን መስተዳድር ምክትልና ዋና ኃላፊ፣ ከ2002 እስከ 2006 ዓ.ም. የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል፣ ከ2006 እስከ 2007 ዓ.ም. ደግሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት አማካሪ ሆነው ይሠሩ እንደነበር ጥቅምት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ክስ የመሠረተባቸው፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አስታውሷል፡፡

ግለሰቡ በወቅቱ የነበራቸውን ሥልጣን በመጠቀምና የተጣለባቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው በሶማሌ የሚኖሩ ጎሳዎች አንዱ በሌላው ላይ ጦርነት እንዲከፍት ትዕዛዝ በመስጠትና በመቀስቀስ፣ በርካታ ዜጎች ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

- Advertisement -

አቶ መሐመድ በተለይ በጥር ወር 2004 ዓ.ም. የራሳቸው ጎሳ የሆነውን የደጎድያ ጎሳ አባላትን በሊበን ዞን ፊልቱ ከተማ አቡር ገበያና አስቤ አይደሌ ቀበሌዎች ውስጥ በመሰብሰብና የጎሳዎቹን ሽማግሌዎች በማግኘት ቅስቀሳ እንዲያደርጉ መምከራቸውን ዓቃቤ ሕግ አስረድቷል፡፡ ዲኮሶፋቱ የተባለችው ከተማ ወደ ወረዳነት ልታድግ ስለሆነ መሬቷን የመረሃን ጎሳዎች ስለሚወስዱ ሽማግሌዎቹ አስቀድመው የአካባቢው ነዋሪዎች የጦር መሣሪያ እንዲታጠቁና ጦርነት እንዲከፍቱ ተከሳሹ ምክር በመስጠታቸው በተደረገ የጦርነት ቅስቀሳ፣ በጥር ወር 2004 ዓ.ም. ሁለቱ ጎሳዎች ግጭት ውስጥ በመግባታቸው ማንነታቸው በውል ያልታወቁ ከ13 በላይ ዜጎች ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡

ከታኅሳስ ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በሊበን ዞንና ደዋ ዞን የሚኖሩ የድጎድያን ጎሳ አባላት መሬታቸው በጎሬ ጎሳዎች ስለተወሰደ በጎሳዎቹ ላይ ጦርነት በመክፈት መሬታቸውን ማስመለስ እንዳለባቸው በመንገርና በመንቀሳቀስ፣ በየካቲት ወር 2009 ዓ.ም. የድጎድያን ጎሳ በጎሬ ጎሳ ላይ ጦርነት እንዲያነሳ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ ከሁለቱም ጎሳዎች ዘጠኝ ዜጎች ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጋቸውንና በሕዝቡ ደኅንነትና ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ እንዲከሰት ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡

ተከሳሹ በ1993 ዓ.ም. የራሳቸው ጎሳ የሆነውን የድጎድያን ጎሳ በመሰብሰብ፣ ‹‹የቦረና ኦሮሞዎች የእኛን ጎሳን የሚያጠቁት የእኛው ጎሳ አባል የሆነው ግለሰብ ሚስጥር አሳልፎ በመስጠቱ ስለሆነ መገደል አለበት፤›› በማለት ባስተላለፉት ትዕዛዝ፣ አራት የጎሳው አባላት ተደራጅተው ሁሴን አህመድ የተባለ ግለሰብ በጦር መሣሪያ ደጋግመው በመምታት ሕይወቱ እንዲያልፍ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ ተከሳሹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ (1ሀና ለ)፣ አንቀጽ 240 (2)  አንቀጽ 522 (ሀ)ን መተላለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ ጠቅሶ፣ የእርስ በርስ ጦርነት በማነሳሳትና ከባድ የግፍ አገዳደል ወንጀል ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት መሥርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሹ ክሱ ከተሰጣቸውና ከተነበበላቸው በኋላ በክሱ ላይ ተቃውሞ እንዳላቸው ተጠይቀው ከጠበቃ ጋር ተመካክረው ምላሽ እንደሚሰጡ በመግለጻቸው፣ ለጥቅምት 21 ቀነ 2010 ዓ.ም. ተቀጥረው ወደ ማረሚያ ቤት ወርደዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...