Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየህዳሴ ግድቡን ተፅዕኖና የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ የሚያጠናው ድርጅት መመርያ ተዘጋጀለት

የህዳሴ ግድቡን ተፅዕኖና የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ የሚያጠናው ድርጅት መመርያ ተዘጋጀለት

ቀን:

የህዳሴ ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖ፣ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ለማስጠናት በድርድር ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ፣ በአዲስ አበባ ለ16ኛ ጊዜ ተገናኝተው ጥቅምት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. መከሩ፡፡ የጥናቱ አማካሪ ድርጅት አሠራሩን የሚመራ ረቂቅ መመርያ ላይ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

 ግብፅ የተፅዕኖ ግምገማው ሲጠና እ.ኤ.አ. የ1959 የውኃ ስምምነት አካል እንዲደረግ ጠይቃለች፡፡ ይህን ጉዳይ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ የምትቃወመው ነው፡፡ ግብፅና ሱዳን እ.ኤ.አ. በ1959 የዓባይን ወንዝ ለመጠቀም አድርገውት በነበረው ስምምነት ለግብፅ 56 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የሚፈቅድ ሲሆን፣ ለሱዳን ደግሞ 18 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የሚፈቅድ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ቀሪው ውኃ ደግሞ የወንዙን ፍሰት ለማስቀጠል ታስቦ የተደረገ ስምምነት ነበር፡፡

የሦስቱም አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ የተገኙበት ዋነኛ ዓላማ፣ ጥናቶቹን ለማከናወን የቀጠሩት አማካሪ ድርጅት ቢአርኤልአይ ሥራውን እንዲያከናውን ያስችለው ዘንድ ረቂቅ የመመርያ ሰነድ ለማዘጋጀት ነው፡፡  

ኢትዮጵያ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አጠቃቀም በተመለከተ በጋራ ተጠቃሚነት፣ ፍትሐዊነት፣ ምክንያታዊነትና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርህ ላይ በመመሥረት ከ70 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውኃ በላይ መያዝ የሚችል የታላቁን የህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ ነች፡፡

የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኢሊሊ ሆቴል በዝግ ስብሰባ አድርገዋል፡፡ በመክፈቻው ፕሮግራም ላይ የሦስቱም አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ንግግር አድርገው ነበር፡፡

የግብፅ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ አብደል አቲ (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው፣ የታላቁን የህዳሴ ግድቡ መጎብኘታቸው ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹የዓለም አቀፉ የአጥኝዎች ቡድን እንዲጠኑ ብሎ የለያቸው ሁለት ጉዳዮች በመዘግየታቸው አሳስቦናል፤›› ብለዋል፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ የግድቡ ውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው ግድቡ ድንበር ተሻጋሪ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖ ጥናት ነው፡፡ ሚኒስትሩ እ.ኤ.አ. በ2015 የሦስቱ አገሮች መሪዎች ካርቱም አካሂደውት በነበረው ስብሰባ በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ ጥናቱ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ መሥራት አለብን ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ጊዜያት ተካሂደው የነበሩ የሦስትዮሽ የብሔራዊ ኮሚቴ ጉባዔዎችን ሲከታተሉ እንደነበር የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ እስከ ዛሬ ድረስ ያልተቋጩና ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ጉዳዮቹ ምን እንደሆኑ ይፋ ባያደርጉም፣ ካርቱም ተካሂዶ በነበረው 15ኛው የሦስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ስምምነት አለመደረሱን ተናግረዋል፡፡

‹‹የታላቁ የህዳሴ ግድብ በታችኖቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ ያለውን ተፅዕኖ በተመለከተ በሦስታችንም ስምምነት መሠረት እ.ኤ.አ. በየካቲት 2016 አማካሪ ድርጅት ብንቀጥርም፣ በመነሻ ረቂቅ ሐሳቡ ላይ ሙሉ በሙሉ ስምምነት ላይ ባለመድረሳችን ወደ ሥራ መግባት አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡

የሱዳን የውኃና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር አምባሳደር ሙታዝ አብደላ ሳሊም በበኩላቸው፣ ‹‹ጥቁር ዓባይ የአንድነትና ተባብሮ የማደግ ተምሳሌት እንጂ የጥላቻ መንስዔ መሆን የለበትም፤›› ብለዋል፡፡ በጋራ በመተባበርና በመፈቃቀር ላይ ተመሥርቶ ውኃውን መጠቀም እንደሚቻል የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ይህ በሚኒስትሮች ደረጃ አዲስ አበባ የሚካሄደው የሦስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ጉባዔ ከዚህ በፊት ካርቱምና ካይሮ ሳይፈቱ የቀሩ ጉዳዮችን እንደሚፈታና ወደ ትክክለኛው መንገድ እንደሚያመጣ ተስፋ አለኝ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

 የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የሁለቱም አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ግድቡን እንዲጎበኙ ያደረገችው በመካከላቸው ግልጽ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ለማስቻል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ አገሮች ትብብር መጠንከር እንዳለበት ፍላጎት አላት፡፡ በወንዙ አጠቃቀም ላይ ግልጽ የሆነ አሠራር መዘርጋት ለሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ግንኙነት ከፍ ያለ ጠቀሜታ አለው፤›› ብለዋል፡፡

የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ማክሰኞ ጥቅምት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. የህዳሴ ግድቡን ጎብኝተው ነበር፡፡ የግብፅ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትር ግድቡን ጉባ ድረስ ሄደው በጎበኙበት ወቅት የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከጥያቄዎች መካከልም ኢትዮጵያ ኃይል ማመንጨት የምትጀምርበትን ጊዜና ሰው ሠራሽ ሐይቁ ስለሚፈጥረው ተፅዕኖ የተመለከቱት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ለእነዚህ ጥያቄዎችም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ስመኘው በቀለ (ኢንጂነር) አርኪ ምላሽ እንደሰጧቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ተናግረዋል፡፡

የሦስቱ ሚኒስትሮች ውይይት ካለቀ በኋላ ሦስቱም አገሮች የኮሚቴ አባሎቻቸውን ይዘው ለየብቻ ውይይት አድርገዋል፡፡ በሱዳንና በግብፅ በኩል የተካሄደው ውይይት አጭር ጊዜ የፈጀ ሲሆን፣ በኢትዮጵያውያን በኩል የነበረው ውይይት ረጅም ጊዜ ወስዷል፡፡ የሦስቱ አገሮች የተናጠል ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላም የግብፅ ብሔራዊ ኮሚቴ አባላት ለብቻቸው ከቆዩ በኋላ ስብሰባውን አጠናቀው ተመልሰዋል፡፡

የሦስቱ አገሮች ጉባዔ ከተጠናቀቀ በኋላም ዶ/ር ስለሺ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫው ላይ ‹‹የግብፅ፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ህዳሴ ግድብ በሄድንበት ጊዜ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ንግግር በማድረግ የማግባባት ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ በጉብኝቱም ሁሉም ሰው ደስተኛ ነው፡፡ ብዙ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች ሊብራሩ ችለዋል፡፡ የተሻለ መረዳትን ፈጥረናል፡፡ በተለይም የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴዎችና አማካሪዎች ለተቀጠረው አማካሪ ድርጅት ድጋፍ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ በዚህ መሀል ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ውሳኔና የሚኒስትሮችን ዕይታ የሚፈልጉ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ እነዚያን ጉዳዮች እንዴት መታየት እንዳለባቸውና በአጠቃላይ አማካሪው ስለሚሠራበት ረቂቅ የመመርያ ሰነድ አዘጋጅተናል፡፡ ይኼ ረቂቅ የመመርያ ሰነድ በቅርቡ ተጠናቆ አማካሪው በዚህ መሠረት እንዲሠራ ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ መመርያው ላይ ውይይታችንን ስናጠናቅቅ በቅርቡ ይፋ ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡

ግብፅ የህዳሴ ግዱቡን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ ያለ ተቃውሞዋን ስታሰማ የቆየች ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሁለቱ አገሮች ጋር ድርድሩን በማስቀጠልና የግንባታ ሒደቱን ከማስቀጠል ወደ ኋላ እንዳላለ በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል፡፡

 

   

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...