Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከዛቻ ይልቅ ተግባር ይቅደም!

የምንዛሪ ለውጡ ይፋ ሲደረግ ሁሉም ሰው ሊከሰት ስለሚችለው የሸቀጦችና የአገልግሎት ዋጋ ጭማሪ የአቅሙን ሲተነብይ፣ ሥጋቱን ሲገልጽ ከርሟል፡፡ በምንዛሪ ለውጡ ማግሥት በዋጋ ግሽበት ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ አነስተኛ ነው ተብሎ ነበር፡፡  ያየነው ግን የተገላቢጦሹን ነው፡፡ የምንዛሪ ለወጡ ወሬ በተሰማ ቅጽበት ገበያው ተለወጠ፡፡ የዕቃዎች ዋጋ ናረ፡፡

 የውጭ ምርቶችን የሚያካፋፍሉ፣ የሚቸረችሩ ሁሉ ያሻቸውን ዋጋ ይጣሩ፣ ይለጥፉ ጀምረዋል፡፡ አንዳንዶቹ መሰንበቻውን በመደብራቸው ሲሸጡት የከረመውን ምርት ገበያተኛው በቆመበት እያወረዱ ሲሸሽጉ፣ ዓይኑ እያየ አልቋል፣ ተሽጧል እያሉ ሲመልሱት ታይተዋል፡፡ ይህ የሰሞኑን የተጠቃሚዎች ምሬት ያሳያል፡፡ የዋጋ ጭማሪው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ብቻ አልተገደበም፡፡ ከምንዛሪ ለውጡ ጋር  ግኙነት የሌላቸው የአገር ውስጥ ምርቶች ሳይቀሩ ዋጋቸው ጨምሮ ሲሸጡ በአደባባይ እያየን ነው፡፡

ከዚህ ሲብስም ቸርቻሪዎች ከጅምላ አከፋፋዎች ምርት እያለ እንኳ ሊያገኙ እንዳልቻሉ በየአደባባዩ መናገራቸው እየታየ መሆኑ የገበያውን ጡዘት የሚያሳይ ነው፡፡ ገሚስ አከፋፋዮች ለሚፈልጓቸውና ለሚመርጧቸው ቸርቻሪዎች ምርት በመስጠት የገበያውን ሥርዓት መፃረራቸው ታይቷል፡፡ እንዲህም እየተኮነ ይቀርቡ የነበሩ የታሸጉ የፍራፍሬ ጭማቂዎች ሳይቀሩ በደርዘን ከ70 እስከ 100 ብር ጭማሪ ስለተደረገባቸው፣ በዚህ ዋጋ የተረከበ ቸርቻሪ የራሱን ትርፍ ሲያክልበት የመጨረሻው ሸማች ላይ የሚያርፈው የዋጋ ጫና የመንግሥት ያለህ፣ የዳኛ ያለህ ያሰኘዋል፡፡

ችግሩ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የተንጋደደ የግብይት ሥርዓታችን ውጤት ነው፡፡ በስበብ አስባቡ ከገበያ ዋጋ ውጪ የሚጦዘውን ገበያ አደብ የሚያሲይዝ ሥልትና መንግሥት ባለመኖሩ ምክንያት በየጊዜው የሚመጣብን ጣጣ ስለመሆኑ እኛም አያሻውም፡፡ ማንም እንደሚገነዘበው የምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የዋጋ ለውጥ ይከሰታል፡፡ ከውጭ የሚገባው ዕቃ የዋጋ ጭማሪ ሊኖረው የሚገባው የምንዛሪ ለውጡ ባሳየው የ15 በመቶ ልክ እንደሚሆን ይታመናል፡፡

ይህም ቢሆን ግን በቀድሞ የምንዛሪ ዋጋ መሠረት ወደ አገር ውስጥ የገቡትን ምርቶች አይመለከትም፡፡ ሌላው ቀርቶ በቀድሞው የምንዛሪ ዋጋ ተገዝተው እየተጓጓዙና በመደብርና በተለያዩ መጋዘኖች የተከማቹ ምርቶችም ቢሆኑ፣ አዲሱ የምንዛሪ ለውጥ አይመለከታቸውም፡፡ ሲሆን፣ ሲደረግ የሚታየው ግን ይህ አይደለም፡፡ በአዲሱ የምንዛሪ ተመን ከውጭ ተገዝቶ የሚገባው ዕቃ ምናልባት ለፍጆታ ሊደርስ የሚችለው ከሁለት ወይም ከሦስት ወር በኋላ ከመሆኑ አኳያ፣ አሁን በየገበያው የታየው የዋጋ ጭማሪ ተገቢነት ይጎድለዋል፡፡ በየትኛውም መመዘኛ ትክክለኛ አሠራር ባለመሆኑ በዝምታ መታየት የለበትም፡፡

ዶላር ጨመረ ተብሎ በየአካባቢው የተደረገው የዋጋ ጭማሪ በመላምትና በዘፈቀደ የተደረገ ነው፡፡ 30 እና 40 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ስግብግብነታችን  ጣሪያ እንደነካ ያመለክታል፡፡ በአጋጣሚው መክበር፣ በአቋራጭ መጠቀም ልማድ ሆኖብን፣ በየምክንቱ የምንጨምረው ዋጋ ከሰሞኑ አጋጣሚ የተሻለ ማረጋገጫ ሊኖረው አይችልም፡፡

እንዲህ ያለው ተግባር በግልጽ መታየቱ ተሳስቦ የመኖር፣ በመርኅ የመመራት፣ በሥርዓት የመሥራትና በምክንያታዊነት የመሥራት አመል ያልፈጠረብን ደካሞች መሆናችንን ማሳየቱ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲህ ያለው ሚዛኑ የተሰበረ አስተሳሰብና አሠራር በንግዱ ኅብረተሰብ ላይ ብቻ የሚንጸባረቅ ሳይሆን፣ የመንግሥትም ጨምር ሆኖ መታየቱ አስፈሪ ያደርገዋል፡፡ የምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ ሊከሰቱ የሚችሉ የዋጋ መዋዠቆችን እና ሊፈጠር የሚችለውን የገበያ ትርምስ ቀድሞ በተገቢው ደረጃና መጠን አለመገመት ብቻ ሳይሆን፣ ለመከላከልም በቂ ዝግጅት አለመደረጉን ተመልክተናል፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎች ከሙያም ከኃላፊነትም የጎደለ አስተያየት ሰሲጡ ታዝበናል፡፡ ሊፈጠር የሚችለውን የዋጋ ትኩሳት አቃለውና በንድፈ ሐሳብ ላይ የተንጠለጠለ፣ የሕዝቡንና የነጋዴውን የቆየ ልማድ ከግምት ያላስገባ ሐሳብ ሲሰነዝሩ አድምጠናል፡፡

የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ላይ ጣት የሚቀሰርበት ሌላኛው ምክንያት ከሰሞኑ የተፈጠረውን የዋጋ ጭማሪ በመመልከት የሚያረጋጋ ዕርምጃ አለመወሰዱ ነው፡፡ በሕግ ኃላፊነት የተሰጣቸው መንግሥታዊ ተቋማት ሕጋዊ ዕርምጃ እንወስዳለን ከሚል ተከታታይ መግለጫዎቻቸው ባሻገር የገበያውን ጡዘት አላረገቡም፡፡ ሸማቹን አልታደጉም፡፡ እንደተለመደው ዛቻ ብቻ ሆነዋል፡፡ ይህ ደግሞ ችግሩን አባብሶታል፡፡ ማናለብኝነትን አንግሷል፡፡ በዘመናዊ መንገድ ይሠራሉ፣ ኃላፊነት ይሰማቸዋል የተባሉ ኩባንያዎች ሳይቀሩ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል፡፡ ቀድሞ መከላከል ባለመቻሉም በጥቂቶች የተጀመረው ድርጊት በመልካም የሚታሰቡትን ሁሉ አዳረሰ፡፡ የገበያውን ግለት ማርገብ ባለመቻሉም የአገሪቱ ሕዝብ ኑሮና የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ የሚፈጠረው ጫና ቀስ በቀስ እየተባባሰ እንደሚመጣ ይጠበቃል፡፡

 በአዲሱ የምንዛሪ ለውጥ የሚገቡት ዕቃዎች ከሰሞኑ ከታየውም ዋጋ በላይ እንዲሸጡ መንገድ ይከፍታል፡፡ ምክንያቱም ከአገራችን የግብይት ልማድ አኳያ አሁን የተደረገው ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ሳይቀንስ ቆይቶ በአዲሱ የምንዛሪ ተመን መሠረት የተገዛው ዕቃ ሲገባም ሌላ ጭማሪ ሊደረግ እንደሚችል ስለሚገመት ነው፡፡

ከዚሁ የምንዛሪ ተመን ለውጥ ጋር በተጓዳኝ ከሰሞኑ ያጠመኝ ጉዳይ ቢኖር ተከራዮቼ የምኖርበት ቤት ባለቤት ይደውሉና ‹‹ገንዘቡን ባንክ ከማስገባትህ በፊት እስቲ ተገናኝተን እናውራ፤›› ይሉኛል፡፡ ነገሩ ግልጽ ነበር፡፡ ዋጋ ለመጨመር ፈልገው እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ይልቁን ሥጋቴ ምን ያህል ይጭኑብኝ ይሆን የሚለው ነበር፡፡ የፈራሁት አልቀረልኝም፡፡ ኑሮ ተወዷል በሚል መንደርደሪያ የተጀመረው የአከራይ እንጉርጉሮ፣ የቤት ኪራይ ለመጨመር ያስገደዳቸው ግን በሰሞኑ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ሁሉ ነገር ስለተወደደባቸው እንደሆነ አስረግጠው የቤት ኪራይ ዋጋ ጨምረውብኛል፡፡

መንግሥት የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል ጠቁሙኝ፣ ንገሩኝ አሳያቸዋለሁ ከሚል ያፈጀ ጩኸት በመላቀቅ፣ የምርት አቀርቦትና ሥርጭትን በማሻሻል፣ እጥረት ሲፈጠር፣ ነጋዴው ሲደብቅ በእጥረቱና በተደበቀው ምርት ልክ ገበያው ውስጥ በመልቀቅ ዋጋ ማስተካከል የሚችልበት አሠራር እንዳለው በመገንዘብ እንዲህ ያሉትን አማራጮች ሊከተል ይገባዋል፡፡ ለነገሩ ምርቱ ከየት ተገኝቶ፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት