አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በ2009 ዓ.ም. ከታክስ በፊት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን በ2008 ዓ.ም. ካስዘመገበው ጋር ሲነጻጸር የአንድ ሚሊዮን ብር ብቻ ብልጫ የታየበት አነስተኛ የትርፍ ዕድገት በማስመዝገብ ዓመቱን እንዳሳለፈ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ባንኩ የ2009 ዓ.ም. የሥራ ክንውኑን በማስመልከት ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ከታክስ በፊት ያገኘው የትርፍ መጠን 351 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ግን በ2008 ዓ.ም. ካገኘው የ350 ሚሊዮን ብር ትርፍ ጋር ሲነፃፀር በአንድ ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ባንኩ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ሲያስመዘግብ የነበረው የትርፍ መጠን ዕድገት እስከ 110 በመቶ ደርሶ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ይሁንና የዓምና የትርፍ ዕድገቱ በአንድ ሚሊዮን ብር ላይ ተወስኗል፡፡ አንበሳ ባንክ ካቻምና 350 ሚሊዮን ብር ሲያተርፍ፣ በ2007 ዓ.ም. አስመዝግቦት ከነበረው ትርፍ አኳያም የ75 ሚሊዮን ብር ብልጫ ነበረው፡፡ በተለይ በ2007 ዓ.ም. የ275 ሚሊዮን ብር ትርፍ ሲያገኝ፣ ይህ መጠን ከ2006 ትርፍ አኳያ የ110 በመቶ ዕድገት በማሳየት ከግል ባንኮች ትልቁ የትርፍ ዕድገት መጠን እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዓምና ያስመዘገበው የትርፍ መጠን ከካቻምናው ብዙም ያልጨመረበት ምክንያት በመግለጫው ወቅት አልተገለጸም፡፡ የትርፍ ክፍፍል ድርሻውም ቢሆን በ2007 ዓ.ም. ከነበረበት የ12 በመቶ ወደ 7.9 በመቶ ዝቅ እንዳለ ከባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከትርፍ ዕድገቱ አነስተኛነት ባሻገር የ2009 ዓ.ም. አፈጻጸሙን የተመለከቱ አገልግሎቶች ግን ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ ውጤት እንደታየባቸው አሳይተዋል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 10.97 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የ35 በመቶ ወይም የ1.87 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉም 938.23 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ ተገልጿል፡፡
በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከ2.66 ቢሊዮን ብር በላይ ለተበዳሪ ደንበኞች አዲስ ብድር የሰጠ መሆኑን የሚገልጸው የባንኩ መረጃ፣ 2.51 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ሰብስቧል፡፡
ከተመሠረተ አሥር ዓመታት ያስቆጠረው ባንኩ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ውስጥ 30 አዳዲስ ቅርንጫፎች በክልሎች በመክፈት ጠቅላላ የባንኩን ቅርንጫፎች ወደ 150 ከፍ እንዳደረገ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም በሞባይልና በወኪል ባንኪንግ አገልግሎቶች መስክ 1,400 ወኪሎችን በመላው አገሪቱ መልምሎ የተደራሽነት አድማሱን እያስፋፋ እንደመጣም ተገልጿል፡፡
የአንበሳ ባንክ ሄሎካሽ ደንበኞች ሒሳብ ከመቀበልና ከመላክ በተጨማሪ ለሞባይል ካርድ (የአየር ሰዓት) መሙላት፣ ለመዝናኛ የሲኒማ ትኬት መቁረጥና ቦታ ማስያዝ፣ ለየብስ ትራንስፖርት የባስ ትኬት መቁረጥና ለአየር ትራንስፖርት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትኬት የመቁረጥ አገልግሎቶችን ከ74 ሺሕ በላይ ለሆኑ ደንበኞች በመስጠት ከ69 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እንዳንቀሳቀሰም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የካርድ ባንኪንግ አገልግሎትን በተመለከተም ከ‹‹ኢትስዊች›› የክፍያ ሥርዓት ጋር በመጣመር ባንኩ ‹‹ላየን ካርድ›› በሚል ስያሜ ገበያውን ከተቀላቀለ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ከ11 ሺሕ በላይ ደንበኞችን ተጠቃሚ በማድረግ 36.6 ሚሊዮን ብር አንቀሳቅሷል፡፡
እንደ ባንኩ መረጃ በእንግሊዙ አማካሪ ኩባንያ ዲሎይት አማካይነት በተደረገ ጥናት፣ አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ‹‹ለሠራተኞቹ ምቹ የሥራ ቦታ›› መፍጠር በመቻል የአንደኛ ደረጃ ማዕረግን ለሁለተኛ ጊዜ አግኝቷል፡፡