Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከ250 በላይ የፍሊንትስቶን ሆምስ ቤት ገዥዎች በውላቸው መሠረት መረከብ አልቻልንም አሉ

ከ250 በላይ የፍሊንትስቶን ሆምስ ቤት ገዥዎች በውላቸው መሠረት መረከብ አልቻልንም አሉ

ቀን:

‹‹የተባለው ሁሉ ትክክል ቢሆንም ችግሩ ግን የእኛ ብቻ አይደለም››

አቶ ፀደቀ ይሁኔ የፍሊንትስቶን ሆምስ ሥራ አስፈጻሚ

ከአራት ዓመታት በፊት ከፍሊንትስቶን ሆምስ ጋር በሁለት ዓመታት ውስጥ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ እንደሚረከቡ ስምምነት ፈጽመው የነበሩ ቤት ገዥዎች፣ ውል ከፈጸሙበት የመረከቢያ ጊዜ ሁለት ዓመታት አሳልፈው ቤቱን በአራተኛው ዓመት ቢረከቡም በኤሌክትሪክ ኃይልና ባልተጠናቀቁ ግንባታዎች እየተሰቃዩ መሆኑን ገለጹ፡፡

ቁጥራቸው ከ250 በላይ እንደሚሆኑ የሚገልጹት ቤት ገዥዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቤት ለመግዛት ከፍሊንትስቶን ሆምስ ጋር ውል የተዋዋሉት ከሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በጉርድ ሾላ ወደ ሲኤምሲ በሚወስደው መንገድ ኦይሲስ ሳይት ነው፡፡ ውሉን ሲፈጽሙ መሠረተ ልማቱ ተጠናቆ በሁለት ዓመት ውስጥ እንደሚረከቡና ካርታም እንደሚሰጣቸው መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡

የቤቱ ግንባታ አራት ዓመታት ወስዶ ከሁለት ዓመት በፊት ከቤት ኪራይ ችግር አንፃር 95 በመቶ ክፍያ ፈጽመው፣ ግንባታው ብቻ በተጠናቀቀው ቤት ውስጥ የገቡ ቢሆንም በጨለማ ውስጥ እየኖሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ ስንታየሁ ፍቅሬና ወ/ሮ ትዕግሥት በላቸው ቤት ገዥዎችን በመወከል ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከጎረቤት የኤሌክትሪክ መስመር ስበው ለመብራት ብቻ ሲጠቀሙ የከረሙ ቢሆንም፣ አሁን ግን የኤሌክትሪክ መስመር ከጎረቤት መሳብ (መቀጠል) አይቻልም በመባላቸው በጨለማ ውስጥ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ቤት ገንቢውን የፍሊንትስቶን ሆምስ ኃላፊዎችን ሲጠይቋቸው፣ ‹‹በቅርቡ እናስገባለን›› ከማለት ባለፈ ምንም ሊያደርጉላቸው እንዳልቻሉ የሚናገሩት ቤት ገዥዎቹ የባሰባቸውን ከኤሌክትሪክ ችግር በተጨማሪ ሌሎች ችግሮችም እንዳሉባቸው ጠቁመዋል፡፡

የቤት ግዥ ውል ሲዋዋሉ በግቢው ውስጥ የመኪና ማቆሚያና አረንጓዴ ቦታ እንደሚኖር የተገለጸላቸው ቢሆንም፣ በነበረው ክፍት ቦታ ላይ ሁለት ሕንፃዎች ተገንብተዋል ብለዋል፡፡ የጋራ መጠቀሚያ ቤት እንደሚሠራላቸው ቃል የተገባላቸው ቢሆንም፣ መሠረቱ ብቻ ወጥቶ በመቅረቱ በልጆች ላይ ጉዳት ያደርሳል የሚል ሥጋት ውስጥ መግባታቸውን አክለዋል፡፡ ሁለቱን ሕንፃዎች ከፕላን ውጭ ስለተገነቡ ይሁን ወይም በሌላ ጉዳይ ግልጽ ባይሆንም፣ ቤቱን ሲያስረክባቸው ካርታ መረከብ የነበረባቸው ቢሆንም ‹‹የሚስተካከል የዲዛይን ለውጥ አለ›› በማለት ሊያስረክቧቸው እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ካርታ ስላልተሰጣቸው የቤት ባለቤት ስለመሆናቸውም እርግጠኛ አይደለንም ብለዋል፡፡ በተደጋጋሚ ደብዳቤ ለድርጅቱ የጻፉ ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት ምላሽ ሊያገኙ አለመቻላቸውንም አስረድተዋል፡፡ የድርጅቱ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀደቀ ይሁኔን በብዙ ልፋት ሲያገኟቸውና ወደ ሳይቱ ሲመጡ፣ ሠራተኞቹ ኤክስካቫተርና ሌሎች ማሽኖችን ይዘው የሥራ እንቅስቃሴ ቢጀምሩም፣ እሳቸው ሲሄዱ ሁሉም ነገር እንደሚቆም ጠቁመዋል፡፡ ለሥራ አስፈጻሚው ተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያሰሙም ምንም ዓይነት ምላሽ ባለማግኘታቸው በችግር ውስጥ መሆናቸውን ገልጸው፣ ሌላ የሚመለከተው አካል ካለ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ከፍሊንትስቶን ሆምስ ቤት የገዙ ነዋሪዎች ያነሱዋቸውን ችግሮች በማንሳት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፍሊንትስቶን ሆምስ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀደቀ ይሁኔ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ቤት ገዢዎቹ ሁሉም ያሉት ነገር ትክክል ነው፤›› በማለት ምላሽ መስጠት የጀመሩት አቶ ፀደቀ ቤቱን እንዳስረከቡ፣ ነገር ግን በቤት ገዥዎች ሳይሆን በእነሱ ጥፋትና ስንፍና ካርታ አለማስረከባቸውን አምነዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ ስለሚበዛበት እነሱ እግር በእግር ተከታትለው የካርታ ሽንሻኖ ማስጨረስና ማስረከብ ሲገባቸው መዘግየቱ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመው፣ በቅርቡ ግን ጨርሰው እንደሚያስረክቡ አስረድተዋል፡፡

መሠረተ ልማትን ማለትም መንገድ፣ መብራትና ውኃን በሚመለከት ማሟላት ያለበት መንግሥት መሆኑን የገለጹት አቶ ፀደቀ፣ ቤት ከተረከቡትና ከድርጅቱ ተዋጥቶ ለመንግሥት መከፈል ካለበት አራት ሚሊዮን ብር ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን ማዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የቀረው 20 በመቶ መሸፈን ያለበት ቤት ባልተረከቡ በመሆኑ ማስገደድ እንደማይችሉ የገለጹት አቶ ፀደቀ፣ በኮንትራት ውላቸውም ላይ ስለመሠረተ ልማት የሚገልጽ ነገር ባለመኖሩ፣ መንግሥት ወይም የሚመለከተው አካል ኤሌክትሪክ ሲዘረጋ፣ የውስጥ መስመር ዝርጋታውን ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የጋራ መጠቀሚያ ሕንፃ የፍሊንትስቶን ሆምስ ንብረት ቢሆንም፣ በውሉ መሠረት እንደሚገነቡ ቃል በመግባታቸው ገንዘብ እንዳገኙ እንደሚገነቡ አክለዋል፡፡ በግቢው ውስጥ የተገነቡት ሁለት ሕንፃዎች ቤት ገዥዎችን የሚመለከቱ አለመሆኑን ጠቁመው፣ ቤት ገዥዎቹ እያንዳንዳቸው 75 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የመኪና ማቆሚያና አረንጓዴ ቦታ እንዳላቸውና ይህም ከስታንዳርዱ በላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ጉዳይ ግን የመንግሥት መሆኑን ደጋግመው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...