Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአደይ አበባ ስታዲየም ዙሪያ የሚካሄዱ ግንባታዎችን የሚያስተባብር ኮሚቴ ተቋቋመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌዴራል መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ እያስገነባ ያለው ‹‹አደይ አበባ ስታዲየም›› የግንባታ ሒደት ፈጣን ቢሆንም፣ መንገድን ጨምሮ በአካባቢው የሚያስፈልጉ መሠረት ልማቶች ግንባታ እስካሁን ባለመጀመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ኮሚቴ አቋቋሙ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ያቋቁሙትን ኮሚቴ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ እርስቱ ይርዳው የሚመሩት ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማና የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም አባል እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በስታዲየሙ ዙሪያ ሊካሄዱ የሚገባቸውን ልማቶች የተቋቋመው ኮሜቴ ይመራል፡፡

በአጠቃላይ 62 ሔክታር የሚሸፍነው ይኼ ግዙፍ ፕሮጀክት ባለፈው ዓመት የተጀመረ ቢሆንም፣ የግንባታ ሒደቱ ፈጣን በመሆኑ 58 በመቶ መድረሱ ተመልክቷል፡፡

ስታዲየሙ 60 ሺሕ ተመልቾች የሚይዝ ከመሆኑም በተጨማሪ 400 መደብሮች የሚኖሩት ስለሆነ፣ ጨዋታ ባለበት ቀን ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አዘቦት ቀን ትልቅ የገበያ ሥፍራ እንዲሆን ተደርጎ እየተገነባ ነው፡፡

ነገር ግን ከ22 ማዞሪያ እስከ ቦሌ መድኃኔዓለም ያለው መንገድ ጠባብና የተጨናነቀ በመሆኑ፣ ከመገናኛ እስከ ኢምፔሪያል ሆቴል ድረስ ያለውም የቀለበት መንገድ አደባባዩ ከፈረሰ በኋላ መጠነኛ መሻሻል ያሳየ ቢሆንም ከመጨናነቅ ያላመለጠ በመሆኑ፣ አዲሱ ስታዲየም ሥራ ሲጀምር ከፍተኛ የትራንስፖርት መጨናነቅ ሊፈጠር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

አቶ ተስፋዬ እንደገለጹት፣ ሚኒስቴሩ ይህንን ታሳቢ በማድረግ አካባቢውን የተሻለ ማዕከል ለማድረግ ከወዲሁ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራ ጀምሯል፡፡

‹‹በእርግጥ ሥራው ከስታዲየም ግንባታው ጋር እኩል አልሄደም፤›› ሲሉ አቶ ተስፋዬ ገልጸው፣ ‹‹የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ሕዝቡን እንዲያደርስ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡ የተሸከርካሪ ማቆሚያ ሥፍራ ግንባታ ይካሄዳል፡፡ አካባቢው የአረንጓዴና የመዝናኛ ማዕከል ዓደዋ ፓርክ ጋር ተቀናጅቶ ይገነባል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከስታዲየሙ ወደ ፓርኩ የሚፈሰውን አነስተኛ ወንዝ በተሻለ በማሳደግ፣ አካባቢው ማራኪ ገጽታ እንዲያደርገው እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ የመጀመርያውን ዙር ግንባታ በ2.4 ቢሊዮን ብር እያካሄደ የሚገኘው የቻይናው ሲኤስሲኢሲ ኩባንያ እስካሁን ላካሄደው ግንባታ አንድ ቢሊዮን ብር ተከፍሏል፡፡

በዚህ ዓመት እስከ ሰኔ ወር ድረስ የመጀመርያውን ምዕራፍ ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሁለተኛውና ሦስተኛው  ምዕራፍ ግንባታ በቀጣይ የሚካሄድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ምዕራፍ የስታዲየም ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ የተመልካቾች እንቅስቃሴ በቁጥጥር ሥር የሚውልበት ሲሆን፣ የሚፈጠሩ ረብሻዎችን እንዲቀነስ ያደርጋል ተብሏል፡፡

የስታዲየም ቴክኖሎጂውና የስታዲየሙ አስተዳደሩ ምን መምሰል አለበት የሚለው ከደቡብ ኮሪያ ኩባንያ ጋር እየተሠራ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

የመጀመርያው ምዕራፍ ግንባታ ሲጠናቀቅ ስታዲየሙ ሥራ ሊጀምር እንደሚችል አቶ ተስፋዬ አክለዋል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች