Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሬዚዳንቱ ንግግርና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለፓርላማ ማብራሪያ ሊሰጡ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሬዚዳንቱ ንግግርና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለፓርላማ ማብራሪያ ሊሰጡ ነው

ቀን:

  • የአፈ ጉባዔ ምርጫ እንደሚካሄድ ይጠበቃል

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግርን አስመልክቶ፣ እንዲሁም በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ምላሽ እንደሚሰጡ ታወቀ፡፡

ሪፖርተር ከምክር ቤቱ ባገኘው መረጃ መሠረት፣ የምክር ቤቱ አባላት የፕሬዚዳንት ሙላቱን የመክፈቻ ንግግር ሙሉ በሙሉ ተቀብለውታል፡፡

የፕሬዚዳንቱ የመክፈቻ ንግግር መንግሥት በዓመቱ ሊያከናውናቸው የሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዮችን ያካተተ በመሆኑ፣ ‹‹የተደሰትንበትና የተቀበልነው›› ነው በማለት መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በቀረበ ሞሽን እንደደገፉት ይታወሳል፡፡

- Advertisement -

ይሁን እንጂ ጥቅል የሆኑ የፕሬዚዳንቱ የንግግር ይዘቶች እንዲብራሩላቸውና በወቅታዊ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የፓርላማ አባላት የማብራሪያ ጥያቄዎችን እንደሚያነሱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለግጭቶች ምክንያት የሆኑ ያልተፈቱ የወሰን ማካለል ጉዳዮች ከሞላ ጎደል ለመፍታት የተቻለ ቢሆንም፣ አሁንም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አካባቢ ያልተስተካከሉ አፍራሽ አመለካከቶች የወለዷቸው ግጭቶች ተከስተው፣ የሰው ሕይወት ያለፈበት መሆኑን ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተናግረው ነበር፡፡

በዚህ ግጭት የሰው ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ያለፈበትና ንብረቶች የወደሙበት መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ይህ ሁኔታ በፍፁም መወገዝ ያለበትና መንግሥት ፀጥታውን ከማስከበር ባሻገር አጥፊዎችን ወደ ሕግ ለማቅረብ እየሠራ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

በማከልም እንደዚህ ዓይነት በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን አንድነት የሚያፈርስ አካሄድ በጭራሽ ሊፈቀድ የማይገባው ነው ብለው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ግጭቶች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመስፋፋት ላይ ናቸው፡፡ በሙስና ተግባር ላይ የተሰማሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተባባሪዎቻቸውን በሕግ እንዲጠየቁ ለማድረግ የተጀመረው ሥራም፣ በ2010 ዓ.ም. በጥናት ላይ ተመሥርቶ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር አውስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሐሙስ ማለዳ በፓርላማው ተገኝተው በፕሬዚዳንቱ ንግግርና በተጠቀሱት ወቅታዊ የአገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮችና ግጭቶች ላይ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡

በዕለቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሉበት ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በአፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ምትክ ሌላ አፈ ጉባዔ ከምክር ቤቱ እንደሚያስመርጥ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አዲስ አፈ ጉባዔ ምርጫ እንደሚካሄድ ተጠይቆ መረጃ እንደሌለው ገልጿል፡፡

አቶ አባዱላ ላለፉት ሰባት ዓመታት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፣ ‹‹የድርጅቴ (ኦሕዴድ) እና የኦሮሞ ሕዝብ ክብር ተነክቷል፤›› በማለት ከምክር ቤቱ አፈ ጉባዔነት ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...