Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገርንና ሕዝብን የሚያተራምሱ ታሪክ ይፋረዳቸዋል!

እጅግ በጣም ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት አሁንም በከንቱ እየጠፋ ነው፡፡ ንፁኃን በሚያሳዝን ሁኔታ እየሞቱ ባሉበት በዚህ አሳዛኝ ጊዜ የሚያሳስበው ምን ያህል ሞቱ የሚለው አይደለም፡፡ ይልቁንም የአንድም ሰው ሕይወት ለምን ለአደጋ ይጋለጣል የሚለው ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊያሳስብ ይገባል፡፡ በከንቱ የሚፈሰው የንፁኃን ደም ያሳምማል፡፡ እያንዳንዱ ቀን መሽቶ እስኪነጋ ድረስ ለሰላም ወዳዱና ለአርቆ አስተዋዩ ሕዝብ እየከበደው ነው፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚለቀቁ መረጃዎች ሰላምና መረጋጋትን ሳይሆን የዋይታ ድምፅ ያዘሉ ናቸው፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ በተለያዩ ጎራዎች የተሠለፉ ኃይሎች የዜጎችን ሞት ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲያውሉት በስፋት ይታያል፡፡ ዘርና ቋንቋን መሠረት ያደረጉ እሰጥ አገባዎች ትልቁን የኢትዮጵያዊነት ምሥል እየጋረዱት ነው፡፡ በፍቅርና በመተሳሰብ የተገነባውን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚንዱና በጥላቻ የተሞሉ ንግግሮች እየበዙ ነው፡፡ ሰብዓዊ ፍጡርነትን ማዕከል ያላደረጉ ጽንፈኝነት የተጠናወታቸው፣ በብሔርተኝነት ካባ ውስጥ አገር ለማፍረስ ያሰፈሰፉና ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ብቻ ተግተው የሚሠሩ በትውልድና በታሪክ የሚያስጠይቅ ድርጊት እየፈጸሙ ነው፡፡

ዘወትር እንደምንለው ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ መከበር አለበት፡፡ የዛሬው ድርጊታችንና ንግግራችን መታረም ካልቻለ ነገ በታሪክ ፊት የሚያስጠይቀን ይሆናል፡፡ ትውልድና ታሪክ ይፋረዱናል፡፡ ይህችን የተከበረችና የታፈረች አገር ያስረከቡ የትናንት ትውልዶች ከፈጸሙዋቸው አኩሪ ተግባራት በተቃራኒ አገርን ለማፍረስና ሕዝብን ለሰቆቃ ለመዳረግ መንቀሳቀስ፣ በመጪው ትውልድ አገር አጥፊ አስብሎ ያስወግዛል፡፡ አገርን የሚመራው ገዥው ፓርቲ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ፍለጋ ዘለቄታዊ ጥፋት ከመፈጸም መቆጠብ ይገባቸዋል፡፡ ይህችን የተከበረች ታሪካዊ አገርና ይህንን አስተዋይ ሕዝብ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ኃይሎች ሴራ አሳልፎ መስጠት፣ መቼም ቢሆን ከማይወጡት ፀፀት ውስጥ ይከታል፡፡ በምላስ ወለምታም ሆነ ሆን ብለው በእሳት ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ ላይ የተጠመዱ ወገኖች ይታቀቡ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት አብሮ የዘለቀው ከልዩነቶቹ ይልቅ አንድነቱ የበለጠ ዋጋ ስለነበረው ነው፡፡ በተዛቡ ግንኙነቶች የተፈጠሩ ችግሮችን አርሞና አስተካክሎ ይህንን የተከበረ ሕዝብ በሰላምና በፍቅሩ ማኖር ሲገባ፣ ለጊዜያዊ ትርፍ ሲባል ቀውስ መፍጠር መቆም አለበት፡፡ ይህንን ዓይነቱን ጎዳና የሞከሩት አገር ከማፍረስና ሕዝብን ለፍጅት ከመዳረግ ውጪ ያተረፉት የለም፡፡ አገርን አቃጥሎ እሳቱን ለመሞቅ ማሰብ አያዋጣም፡፡ ለእነ ሶሪያም አልበጀም፡፡

በአራቱም ማዕዘናት የሚኖረው ጨዋውና አስተዋዩ ሕዝባችን የሚከፋፍሉትንና አገሩን ለማጥፋት የሚነሱ ኃይሎችን በፍፁም አይፈልግም፡፡ ከአኗኗሩ ጀምሮ እስከ ሥነ ልቦናው ድረስ እጅግ ተቀራራቢ፣ ያገኘውን ሳይሰስት ተካፍሎ በሰላምና በፍቅር የሚኖረውን ይህንን ተምሳሌታዊ ሕዝብ ማክበር ይገባል፡፡ ይህ ኩሩ ሕዝብ ከአገሩ በላይ የሚያስቀድመው የለም፡፡ የሚፈልገው ሰላም፣ ዴሞክራሲና በእኩልነት ተደጋግፎ መኖር ነው፡፡ ሰብዓዊ መብቶቹ ተከብረውለት በአገሩ ጉዳይ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖረው ነው ምኞቱ፡፡ ጉልበተኛ እየተነሳ እንዲጨፍርበት ሳይሆን የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ነው የሚፈልገው፡፡ በገዛ አገሩ ባይተዋር መሆን ሳይሆን የአገሩ ሕጋዊና ሉዓላዊ ባለቤትነቱ እንዲረጋገጥለት ነው የሚሻው፡፡ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህልና በመሳሰሉት ልዩነቶች ተገድቦ መኖር ሳይሆን እነዚህን ልዩነቶች ተቀብሎ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን ማጠናከር ነው ዓላማው፡፡ ሕገወጥነት፣ ሌብነት፣ ከፋፋይነት፣ የሞራልና የሥነ ምግባር አልባነት፣ ወዘተ. ተወግደው ልጆቹ በሥርዓት ታንፀው እንዲያድጉለት ነው ፍላጎቱ፡፡ ይህንን የመሰለ የተከበረ ሕዝብ ሰላሙን መንሳትና ሕይወቱን ለአደጋ ማጋለጥ፣ አገሩንም የማትወጣው ችግር ውስጥ መክተት በታሪክና በትውልድ ያስጠይቃል፡፡

ኢትዮጵያዊነትን የሚቀናቀኑ ድርጊቶች እየበዙ በአንድነት መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ ሰላምን የሚያናጉና የዕለት ተዕለት ሕይወትን የሚያመሰቃቅሉ ሁከቶች የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት መንጠቃቸውን ቀጥለዋል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፀር የሆኑ ተንከባላይ ችግሮች በዓይነታቸውና በመጠናቸው ጨምረዋል፡፡ የተዘጋጋው የፖለቲካ ምኅዳር ጠንካራና ተደማጭ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማጥፋቱ ችግሮች በርትተዋል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አሳሳቢ ወቅት ከምክንያታዊነት ይልቅ በስሜታዊነት መነዳት በብዛት ይታያል፡፡ ለታሪክ ፍርድ በሚቀርበው የእዚህ ዘመን ድርጊት ውስጥ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ ከጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ በላይ የአገር ዘለቄታዊ ህልውና የማያሳስባቸው ወገኖችም መሰሪ ተግባራቸውን ቀጥለውበታል፡፡ ይህ አካሄድ የት ያደርሳል? መንግሥት የአገሪቱን ውሎና አዳር በግልጽ ለሕዝብ ከማሳወቅ ይልቅ ዝምታ ውጦታል፡፡ በገዥው ፓርቲ ሠፈር ውስጥ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ጎራ ለይተው የሚተናነቁ ኃይሎች ይታያሉ፡፡ በመሀል የንፁኃን ሕይወት በከንቱ እየጠፋ ግድ የማይሰጣቸው በርክተዋል፡፡ በታሪክ የሚያስጠይቁ ክፉ ድርጊቶች እየበዙ ነው፡፡

መሰንበቻውን በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን ውስጥ በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ተጠርጣሪ ግለሰቦች በክልሉ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል፡፡ ከ1,500 በላይ ወገኖች መኖሪያቸውን ጥለው በፍርኃት በሌሎች ሥፍራዎች ተጠልለዋል፡፡ ይህንን ዓይነቱን አሳዛኝ መረጃ የሚሰሙ ቅን ዜጎች ልባቸው ይሰበራል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት የዘለቀው ተቃውሞና ሁከት ለጊዜው በአስቸኳይ አዋጁ ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም ብሶበት በመቀጠል የሰው ክቡር ሕይወት እየቀጠፈ ነው፡፡ ይህንን ችግር መፍታት ለምን አልተቻለም? የሕዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡ አዳምጦ ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት እንዴት ያቅታል? ለወራት ዘለቀ የተባለው ጥልቅ ተሃድሶ ፋይዳው ምን ነበር? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት እየተነገረለት ያለው የገዥው ፓርቲ ጎራ ክፍፍል ወይም ውስጣዊ ትግል በግልጽ ለምን አይታወቅም? በማኅበራዊ ሚዲያ አጋፋሪዎች አማካይነት የውስጥ ሽኩቻዎች ማሳያ የሆኑ እሰጥ አገባዎች ምን ዓይነት ምልክት እያሳዩ ነው? ወዘተ. ጥያቄዎችን በድፍረት ለመመለስ አልተቻለም፡፡ ነገር ግን የሽኩቻዎቹ ጡዘት ሕዝብ ዘንድ ደርሰው አደጋ ሲፈጥሩ ግን እየታየ ነው፡፡ በታሪክ የሚያስጠይቁ አደጋዎች ናቸው፡፡

አገሪቱንና ሕዝቡን ከገቡበት ማጥ ውስጥ ማውጣት የሚቻለው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወይም የፀጥታ ኃይሎችን በማሠለፍ አይደለም፡፡ ትክክለኛው የችግሩ ቁልፍ የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ መልሱ ደግሞ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ለሕግ የበላይነት ተገዝቶ የተዘጋጋውን የፖለቲካ ምኅዳር በሩን ወለል አድርጎ መክፈት፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ በነፃነት የሚንቀሳቀስበት የፖለቲካ ዓውድ ሲኖር፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትክክለኛ ዕርምጃ ይሆናል፡፡ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ሕጋዊውን መንገድ ተከትለው በሰላም የፖለቲካ ተሳትፎ ሲያደርጉ፣ ፓርቲዎች በነፃነት ሲንቀሳቀሱ፣ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ከሕዝብ በታች ሆነው በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ያገኙ መሠረታዊ መብቶችን ሲያከብሩ ድንጋይ መወርወር፣ ንብረት ማውደምና ነጋ ጠባ መሞት ይቆማል፡፡ በስሜታዊነት ከመነዳት በምክንያታዊነት መነጋገር ይቻላል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ግልጽና ተጠያቂነት ያለበትና ማንኛውም ባለሥልጣን ሥልጣኑ ልጓም የተበጀለት ሲሆን፣ የሕግ የበላይነት በተግባር ይረጋገጣል፡፡ በሌላ በኩል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ አለን የሚሉ ወገኖች ሕጋዊውንና ዴሞክራሲያዊውን መንገድ ይከተላሉ፡፡ ይህንን ጎዳና አንከተልም የሚሉ ደግሞ በሕዝብ ወንፊት ይንገዋለላሉ፡፡ ሕዝቡም ሆነ አገሪቱ የሚፈልጉት ሥልጡን ፖለቲካ ነው፡፡ አገርን እያመሱ መቀጠል ስለማይቻል፡፡ አገርንና ሕዝብን የሚያተራምሱ ታሪክ ይፋረዳቸዋል!

 

 

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...