Monday, March 20, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት የገንዘብ ተመን ለውጡ ያመጣውን የገበያ ቀውስ ለማብረድ ቁጥጥር ላይ ትኩረት አድርጓል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብር ከዶላር ጋር ያለው የውጭ ምንዛሪ ተመን 15 በመቶ እንዲዳከም ከተደረገ በኋላ የተፈጠረውን የገበያ ዋጋ ቀውስ ለመቆጣጠር መንግሥት ዘግይቶ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ተወያየ፡፡ መንግሥታዊው የንግድ ኩባንያ አለ በጅምላ የውጭ ምንዛሪ በልዩ ሁኔታ እንዲፈቀድለት ጠየቀ፡፡

ሰኞ ጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ማዕከል በተካሄደ ምክክር የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰድ ዛይድ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አማካሪ አቶ አብዱል ለጡፍ የሱፍ፣ እንዲሁም ከንግዱ ማኅበረሰብ ደግሞ ላኪዎች፣ አስመጪዎችና አምራቾች ተገኝተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት ከጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በግብርናና በኢንዱስሪ ምርቶች፣ እንዲሁም በካፒታል ዕቃዎች ላይ ያልተገባ ጭማሪ መከሰቱን ገልጿል፡፡

በግብርና ምርቶች በተለይም ጤፍ፣ ሽንኩርትና ቲማቲም ቀላል የማይባል የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል፡፡ ከኢንዱስትሪ ምርቶች ደግሞ በተለይም ፓስታ፣ ስንዴ፣ ዱቄትና ዘይት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል ሲል የቢሮው ጥናት ያመለክታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለመሠረተ ልማት ግንባታ ዋነኛ ግብይት በሆኑት የካፒታል ዕቃዎች ብረት፣ ጀሶና ቆርቆሮ በመሳሰሉ ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉ ተመልክቷል፡፡

በአዲስ አበባ መርካቶ፣ ተክለ ሃይማኖትና መገናኛ አካባቢ 18 ትልልቅ የንግድ መደብሮች ጥፋት ተገኝቶባቸዋል ተብለው እንዲታሸጉ ተደርጓል፡፡ በአማራ ክልልም 70 የሚጠጉ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ መውሰዱ ተገልጿል፡፡   

ከዋጋ ጭማሪ ባሻገርም ቀደም ሲል የተትረፈረፈ ምርት በገበያው ውስጥ ባይኖርም፣ ከገንዘብ ተመን ለውጡ በኋላ ምርት የመደበቅ አዝማሚያ መታየቱ ተመልክቷል፡፡

የንግድ ሚኒስቴር ሬጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰድ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፣ ይህንን የዋጋ ተመን ለውጥ ምክንያት በማድረግ፣ የዋጋ ጭማሪም ሆነ ምርት ማከማቸት ፍፁም የተከለከለ ነው፡፡

‹‹ምርት በሚያከማቹም ሆነ ዋጋ በሚያንሩ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ ይወሰዳልም፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ አሰድ፣ ‹‹ይህን ሕገወጥ ተግባር የሚያከናውኑ ነጋዴዎች መደብራቸው ይታሸጋል፣ የንግድ ፈቃዳቸውም ይሰረዛል፤›› ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡

የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት መካከል ለሪፖርተር ሐሳባቸውን ያካፈሉ ነጋዴዎች እንደሚሉት፣ ውይይቱ መግባባት ላይ ያተኮረ ሳይሆን ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ያለመ ነው፡፡ ምንያቱም የንግዱ ማኅበረሰብ በገንዘብ ተመኑ ያጋጠመውን ችግር ለመረዳት የሞከረ ባለመኖሩ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት የተጠና መድረክ ሆኗል ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ይጠበቅ በነበረው ደረጃ ሐሳብ መንሸራሸር ባይቻልም የተወሰኑ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት እንደገለጹት፣ የዋጋ ጭማሪው የመጣው ከምንዛሪ ለውጡ በፊት በጥሬ ዕቃዎች ዋጋ ላይ ከ25 በመቶ በላይ ጭማሪ በመደረጉ መሆኑን፣ በአገሪቱ የምንዛሪ አቅርቦት ችግር በመኖሩ ለዋጋ ጭማሪው አሳማኝ ማስረጃዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት መንግሥት የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ ችግሩን ለመፍታት ቢሞክር የተሻለ ነው ሲሉ አሳስበዋል፡፡  

ነገር ግን የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ የብር የመግዛት አቅም ተዳከመ ማለት፣ በአገር ውስጥ የሚደረግ ግብይት አቅሙ ያንሳል ማለት አይደለም ብለዋል፡፡ አቶ አሰድም እንዲሁ ዋጋ መጨመርም ሆነ ምርት ማከማቸት አይፈቀድም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ይሁንና በገበያ ውስጥ ዋጋ የመጨመርም ሆነ ምርት የመያዝ አዝማሚያዎች በሰፊው እየታዩ ነው፡፡ በ2006 ዓ.ም. የተቋቋመው አለ በጅምላ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚመለክተው፣ በተቋሙ የተመን ለውጡ ከመደረጉ በፊት ቢያንስ በሁለት ሳምንት ውስጥ ከአገር ውስጥ አምራቾች አሥር ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ምርቶችን ይገዛ ነበር፡፡ ከተመኑ በኋላ ግን መግዛት የቻለው ከ700 ሺሕ ብር ያነሰ ምርት ብቻ ነው፡፡ ከአለ በጅምላ ምርት እየወሰዱ የሚቸረችሩ ነጋዴዎች ደግሞ ምርት በብዛት እየጠየቁ መሆኑን አመልክቷል፡፡

አለ በጅምላ ለንግድ ሚኒስቴር ባቀረበው ዋጋ ማረጋጊያ አዲስ ዕቅድ አቅርቧል፡፡ የዕቅዱ ማጠንጠኛ በአሁኑ ወቅት የገንዘብ ተመን ለውጥ በመደረጉ በምርት ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ክፍተት ተፈጥሯል የሚል ነው፡፡

ይህንን ክፍተት ለመሙላት ኩባንያው ቀደም ሲል ያስገባ የነበረው እስከ ሦስት ወራት ድረስ የሚያስፈልግ ምርት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ገበያው ለውጥ እያደረገ በመሆኑ ለስድስት ወራት የሚሆን ዕቃ ለማስገባት አዲስ ዕቅድ ተቀርፆ ለንግድ ሚኒስቴር ቀርቧል፡፡

አቶ አሰድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አለ በጅምላ ዕቅዱን አቅርቧል፡፡ ዕቅዱ ገና እየታየ ነው፡፡ ውሳኔ አልተሰጠውም ብለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች