Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኦሮሞ ወጣቶች ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ከወጣው ጋር ሁሉ መንቀሳቀስ እንደሌለባቸው የክልሉ ፕሬዚዳንት...

የኦሮሞ ወጣቶች ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ከወጣው ጋር ሁሉ መንቀሳቀስ እንደሌለባቸው የክልሉ ፕሬዚዳንት አሳሰቡ

ቀን:

  • 14 ሰዎች የሞቱበትና በሺሕ የሚቆጠሩ የተፈናቀሉበት ግጭት መቆሙ ተገልጿል

የኦሮሞ ወጣቶች የተለያዩ ሰንደቅ ዓላማዎችን አንግቦ ከሚንቀሳቀሰው ጋር ሁሉ መንቀሳቀስ እንደሌለባቸው፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ አሳሰቡ፡፡

ፕሬዚዳንቱ በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ጥቅምት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ነው ይኼንን የተናገሩት፡፡

‹‹የኦሮሞ ወጣት ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ከሚንቀሳቀሱት ሁሉ ጋር መንቀሳቀስ የለበትም፡፡ ነገሮችን ማገናዘብ ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡

ሰንደቅ ዓላማ የማንነት መገለጫ መሆኑ ግልጽ እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹እንደ አፍሪካ ኅብረት ከ10 እስከ 15 ሰንደቅ ዓላማ ይዞ መውጣት ትርጉም የለውም፤›› ብለዋል፡፡

የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ አሁን የሚያንገበግብ አጀንዳ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹በሰንደቅ ዓላማው ላይ ጥያቄ ካለ ዋናውን ችግራችንን ከፈታን በኋላ ሁላችንንም የሚያግባባ ሰንደቅ ዓላማ ሊኖረን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች ግጭት አዘል ሰላማዊ ሠልፎች ላለፉት ሁለት ሳምንታት እየተካሄዱ ሲሆን፣ ሰላማዊ ሠልፎቹን ማን እንደሚያስተባብርና ዓላማው ምን እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

አቶ ለማ ሰላማዊ ሠልፎቹን የሚያንቀሳቅሱት ጠላቶቻችን ናቸው ቢሉም፣ የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ደግሞ ‹‹ኪራይ  ሰብሳቢዎች›› ናቸው ይሏቸዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ባለፈው ቅዳሜ በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን በተካሄደ የተቃውሞ ሠልፍ በተቀሰቀስ ግጭት ከ1,500 በላይ ሰዎች ሲፈናቀሉ የ14 ሰዎች ሕይወትም ጠፍቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ሰላም መስፈኑን ለተፈናቀሉ ሰዎችም ዕርዳታ እየተደረገ መሆኑን አቶ አዲሱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

 ግጭቱ የብሔር ግጭት እንደሆነ ለማስመሰል የሚደረገውን ጥረትም አውግዘዋል፡፡

እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ፣ በዞን ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎች ነዋሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የክልሉ የፀጥታ አካላት አንድ ላይ በመሆን በተደረገ ርብርብ በአካባቢው መረጋጋት ተፈጥሯል፡፡ በተፈጠረው ሁከት የተሳተፉት፣ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ፖሊስ ምርመራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የተጠርጣሪዎቹ ብዛትና ማንነት ግን አልተገለጸም፡፡

‹‹የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአካባቢው ዘላቂ መረጋጋት እንዲፈጠርና ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ለማድረግ ጠንክሮ በመሥራት ላይ ይገኛል፤›› ሲሉ አቶ አዲሱ ወቅታዊውን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በቡኖ በደሌ ዞን ለ12 ንፁኃን ሕይወት መጥፋትና ለ665 አባወራዎች/እማወራዎች መፈናቀል ምክንያት የሆነ ግጭት ሲከሰት፣ በኡሉባቦራ ዞን ደግሞ የሁለት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ ለ835 ሰዎች መፈናቀል ምክንያት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በጅማ ከተማ ደግሞ ግጭት ያልተስተናገደ ትዕይንተ ሕዝብ ታይቷል፡፡

የቡኖ በደሌ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ሻፊ ሁሴን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ጊዜ ግጭቱ በቁጥጥር ሥር ውሎ የሟች ቤተሰቦችን ማፅናናት፣ ተፈናቃዮችንም መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

ግጭቱ ከኢሉባቦር ዞን ተነስቶ አጎራባች ወደ ሆነው ቡኖ በደሌ ዞን አራት ወረዳዎች በመዛመቱ፣ ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡

አቶ ሻፊ እንዳሉት፣ ሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. የአካባቢው ወጣቶች በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ ቅሬታቸውን ለማሰማት አደባባይ ወጥተው ነበር፡፡ ወጣቶቹ፣ ‹‹የኦሮሚያ ድንበር ይከበር!፣ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀዬቸው ይመለሱ!› የፌዴራል መንግሥት ለተፈጠረው ችግር ዕልባት ይስጥ የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ሠልፍ መውጣት ጀምረው ነበር፤›› ሲሉ አቶ ሻፊ ገልጸው፣ ‹‹ነገር ግን ሌላ ዓላማ ያላቸው ኃይሎች ይህንን ጥያቄ ሌላ ገጽታ በማስያዝ አብረው በኖሩ ሕዝቦች ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ብለዋል፡፡

በቡኖ በደሌ አራት ወረዳዎች ገጭ፣ ጮራ፣ ቤጋና በደሌ ዙሪያ በተቀሰቀሰው ግጭት በርካታ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ 665 አባወራዎችና እማወራዎች ተፈናቅለዋል ብለው፣ ‹‹ይህ ክስተት ላለፉት አርባ ዓመታት አብረው በኖሩና በጋብቻ በተሳሰሩ ሕዝቦች መካከል ሊፈጠር የማይገባው ነው፤›› ሲሉ አቶ ሻፊ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሁለት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑንም አቶ ሻፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የመጀመርያው ችግሩንና አጥፊዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሐዘን የደረሰባቸውንና የተፈናቀሉትን ማፅናናትና በድጋሚ ማቋቋም ናቸው፡፡

አቶ ሻፊ እንዳሉት፣ የአካባቢው ኅብረተሰብ ገንዘብና ምግብ ከማቅረብ ጀምሮ የተለያዩ ርብርቦችን እያካሄደ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል የአደጋ ሥጋት አመራር ኤጀንሲ ደግሞ የተለያዩ ምግቦችንና ቁሳቁሶችን በማቅረብ ላይ ነው ብለዋል፡፡

በተለይ በቡኖ በደሌና በኢሉአባቦር ዞኖች የተፈጠረውን ግጭት ለማብረድ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው፣ ሰኞ ጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. 800 ከሚጠጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በበደሌ ከተማ ውይይት አድርገዋል፡፡

አቶ አሰግድን አግኝቶ ለማነጋገር ባይቻልም፣ አቶ አሰግድ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹በበደሌ ከተማ በተካሄደው ውይይት፣ አገር ሽማግሌዎች የኦሮሞ ሕዝብ ከአማራ ጋር በጋብቻና በደም የተሳሰረ መሆኑን፣ ይህ ክስተት እጅግ እንዳሳዘናቸውና ሊከሰት የማይገባው እንደነበር መግለጻቸውን፤›› አቶ አሰግድ መናገራቸው ተገልጿል፡፡

የተፈናቀሉትን መልሶ ማቋቋምና የወደመባቸውን ንብረት መልሰው እንደሚተኩ ጭምር የአገር ሽማግሌዎች መናገራቸውን አቶ አሰግድ ለአማራ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡ ከሁለቱም ዞኖች የተፈናቀሉ አባወራዎችና እማወራዎች ቁጥር 1,500 ሲሆን፣ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ደግሞ 14 መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ዞኖች የተከሰተው ደም አፋሳሽ ግጭት በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተመልክቷል፡፡

በዮሐንስ አንበርብርና በውድነህ ዘነበ   

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...